
12 ሚያዚያ 2024, 12:58 EAT
ከቀናት በፊት ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች መቂ ከተማ ከተገደሉት ከአቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ ጋር በተያያዘ የቤተሰብ አባላቸው እና ሌሎች ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የከተማው ፖሊስ እና ቤተሰባቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።
የአካባቢው ፖሊስ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ የአቶ በቴን ወንድም እና እህትን በቁጥጥር ስር አውሎ የነበረ ሲሆን፣ እህታቸው ግን በተያዘችበት ዕለት ሌሊት ተለቃ ወደቤት መመለሷ ተነግሯል።
በተመሳሳይ ባለፈው ረቡዕ ሚያዝያ 2/2016 ዓ.ም. ተገድለው ከተገኙት ፖለቲከኛ ግድያ ጋር በተያያዘ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ በበኩሉ 13 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የኦሮሚያ ክልል ቴሌቪዥን ጣቢያ አስታውቋል።
የአቶ በቴ ወንድም እና እህት በፖሊስ የተያዙት ሐሙስ ዕለት ከተከናወነው የአቶ በቴ ኦርጌሳ የቀብር ሥነ ሥርዓት በኋላ መሆኑን ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የቤተሰብ አባላት አረጋግጠዋል።
የቤተሰብ አባላቱ ሁለቱ ግለሰቦች ከመኖሪያ ቤታቸው ተይዘው የታሰሩ በአቶ በቴ ግድያ ተጠርጥረው ስለመሆኑ እንደማያውቁም ጭምረው ገልጸዋል።
ከሰዓታት የፖሊስ ጣቢያ ቆይታ በኋላ የአቶ በቴ እህት ሲምቦ ኡርጌሳ የተለቀቀች ሲሆን፣ ወንድማቸው ሚሎ ኡርጌሳ ግን አሁንም ድረስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኛል።
አቶ በቴ ተገድለው የተገኙባት የመቂ ከተማ ከንቲባ አቶ ዲልቦ ኡርጌሳ ከሁለት ቀናት በፊት ግድያው የተፈጸመው ምናልባት በቤተሰብ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ሊሆን ይችላል ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
የመቂ ከተማ ፖሊስ አዛዥ የሆነት ኮማንደር ሞሐመድ ሱፋ ደግሞ ከአቶ በቴ ግድያ ጋር ተያይዞ “በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሟች ከወንድማቸው ጋር ግጭት ውስጥ እንዳሉ ስለተወራ” ማጣራት በማስፈለጉ ወንድም እና አህታቸው መያዛቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የነበሩት አቶ በቴ ኡርጌሳ ማክሰኞ እኩለ ሌሊት ሚያዝያ 2/2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ውስጥ በምትገኘው የትውልድ ከተማቸው መቂ ውስጥ ነው የተገደሉት።
- ኢትዮጵያ ፆታዊ ጥቃት ፈጻሚዎችን ከሥራ እና ከማኅበራዊ ግልጋሎቶች የሚያገል ምዝገባ ልትጀምር ነው12 ሚያዚያ 2024
- አንድ ሠራተኛ በመቀለ አይደር ሆስፒታል ውስጥ በሚሊዮኖች የሚገመት ዋጋ ባላቸው የህክምና መሳሪያዎች ላይ ጉዳት አደረሰ11 ሚያዚያ 2024
- ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አባል ለመሆን ጥያቄ አላቀረብኩም አለች9 ሚያዚያ 2024
ሐሙስ ሚያዝያ 3/2016 ዓ.ም. የዞኑ ፖሊስ ከአቶ በቴ ግድያ ጋር በተያያዘ 13 ተጠርጣሪዎችን መያዙን አስታውቋል።
የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ አዛዥ የሆኑት ምክትል ኮሚሽነር ታሪኩ ዲርባባ ለክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲናገሩ ወንጀሉን የሚመረምር ቡድን ተቋቋሞ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።
የክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ በዘገባው በግድያ ወንጀሉ ተጠርጥረው ከታሰሩት 13 ሰዎች መካከል የአቶ በቴ ወንድም እና እህት ስለመገኘታቸው ያለው ነገር የለም።
አሁን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከሚገኙት ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው ሚሎ የታላቅ ወንድሙን ግድያ በተመለከተ ቢቢሲን ጨምሮ ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በሚሰጣቸው ቃለ መጠይቆች ለአቶ በቴ ግድያ የመንግሥት ኃይሎችን ተጠያቂ ሲያደርግ ነበር።
የመቂ ከተማ ከንቲባ የአቶ በቴ ግድያ ከቤተሰብ ግጭት ጋር ሊያያዝ ይችላል ማለታቸውንም ሚሎ አጥብቆ ተችቶ መንግሥት ይህን እንደምክንያት እያነሳ ያለው ወንጀሉን ለመሸፋፈን ስለፈለገ ነው በማለት ሲናገር ነበር።
ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ለአቶ በቴ ግድያ መንግሥትን ተጠያቂ የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን ተከትሎ የክልሉ መንግሥት ባወጣው መግለጫ፣ በአንዳንድ ወገኖች ለግድያው መንግሥት ተጠያቂ መደረጉ ተቀባይነት የለውም ሲል አጥብቆ አውግዟል።
በኦሮሞ የተቃውሞ ፖለቲካ እና በኦነግ ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንደነበሩ የሚነገርላቸው የአቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ በርካቶች ዘንድ ጥያቄን አስነስቷል።
አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ የተለያዩ አገራት የግድያ ወንጀሉ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ የጠየቁ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ደግሞ ግድያውን የሚያጣራ ቡድን ወደ ስፍራው መላኩን ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር የተገደሉት በበርካታ ጥይት ጭንቅላታቸውን ተመትተው መሆኑ አስክሬን የመረመሩ ባለሙያ እና የቤተሰብ አባል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ስሜ አይጠቀስ ያሉ የሕክምና ባለሙያ የአቶ በቴ ጭንቅላት ላይ አምስት በጥይት ምት የተፈጠሩ ጉዳቶችን መመልከታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቁት እና በፓርቲያቸው ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የነበሩት አቶ በቴ ከዚህ ከቀደምም ለተደጋጋሚ እስር ሲዳረጉ ቆይተዋል።
በ2013 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ በኦሮሚያ ክልል ቡራዩ ከተማ በቁጥጥር ስር የሚገኙ የኦነግ ከፍተኛ አመራሮችን ለመጠየቅ በሄዱበት ተይዘው ረዘም ላለ ጊዜ በእስር መቆየታቸው ይታወሳል።
አቶ በቴ በቡራዩ በእስር በነበሩበት ወቅት አያያዛቸው የሰብዓዊ መብትን ያከበረ አይደለም በማለት ለቀናት የረሃብ አድማ በማድረጋቸው ከፍተኛ የጤና መቃወስ አጋጥሟቸው ነበር።