የመቶ ዓመት ሻማ

13 ሚያዚያ 2024, 07:55 EAT

ማርጋሪታ ልክ ጎህ ሲቀድ ትነቃለች። ቁርሷን ማልዳ ከበላች በኋላ ሰውነቷኝ ለማንቀሳቀስ ወጣ ትላለች። ከዚያ በኋላ ማንበብ ነው ልምዷ።

እንደሷ ፍላጎት ቢሆን ኖሮ ከዚህም ያለፈ እንቅስቃሴ ማድረግ በቻለች። ጂም መግባትም ትመኛለች።

ነገር ግን በ107 ዓመቷ እግሮቿ ይህን ማድረግ አንችልም ብለው እምቢኝ ቢሉ የሚደንቅ አይደለም።

“እርምጃዬን ጨምሬ እንዲለማመዱ አደርጋቸዋለሁ” ስትል ትቀልዳለች።

“እስቲ አረፍ በይ ይሉኛል። እኔም ማረፍ አልፈልግም። ሐሳቤን የሚይዘው የሆነ ነገር እፈልጋለሁ” ትላለች ማርጋሬታ ፍሎሬዝ።

ስትራመድ አትደነቃቀፍም። የምታወራው ነገር እንደ ንፁህ ምንጭ ፍስስ ሲል ይሰማል።

ጓደኞች አሏት። ልጇም ዘወትር አጠገቧ ናት።

“በዚህ ዕድሜዬ ብዙ ነገር መቀየር እፈልጋለሁ” ብላት ስትናገር በታላቅ መመሰጥ ነው።

100 ዓመት የደፈኑ የዕድሜ ባለፀጋዎች የሚጋሯቸውን ባሕርያት ለመቃኘት ማርጋሬት መልካም ምሳሌ ናት። አብዛኞቹ አሁንም ጤናማ ናቸው፤ ጥንካሬያቸው ያስቀናል፤ ከሰው ጋር ለማውራት ጉጉ ናቸው።

በእንግሊዝኛው ሴንቴናሪያንስ ይባላሉ። 100 ዓመት ያለፋቸው የዕድሜ ባለፀጋዎች ናቸው።

አብዛኞቹ ጭንቅላታቸው ሁሌም በእቅስቃሴ እንዲጠመድ ይፈልጋሉ። ለምሳሌ ስፖርት መሥራት አሊያም ጨዋታ መጫወት።

እንደ ማርጋሪታ ያሉ ሰዎች መብዛት ጀምረዋል።

የተባበሩት መንግሥት የሕዝብ ጥናት ክፍል እንደሚለው አሁን አሁን በርካታ ሰዎች የመቶ ዓመት ዕድሜያቸውን ለማክበር 100 ሻማ ሲለኩሱ መመልከት አዲስ ነገር አይደለም።

በአውሮፓውያኑ 1990 ይህን ፀጋ መጎናፀፍ የቻሉት 92 ሺህ ሰዎች ብቻ ነበሩ። በ2021 ይህ ቁጥር ወደ 621 ሺህ ተመንድጓል።

እርግጥ ይህ ቁጥር ለምን በዛ የሚለውን ለማወቅ ዘረ-መል እና የኑሮ ዘይቤን መመልከት ግድ ይለናል። ነገር ግን ሥነ-ልቦናዊ ባህሪያትን መዘንጋት የለብንም።

ማሪያ ዶሎረስ ሜሪኖ በማድሪድ ኮምፕሉተንስ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ልቦና ባለሙያ ናት። 100 ዓመት የደፈኑ የዕድሜ ባለፀጋዎችን ለዓመታት አጥንታለች።

ዘ ጆርናል ኦፍ ሀፒነስ ስተዲስ የተሰኘው መጽሔት ላይ በቅርቡ ባወጣችው አንድ ጥናት እነዚህ ሰዎች 19 ሥነ-ልቦናዊ ባህሪያትን ይጋራሉ ትላለች።

ማሪያ እነዚህን ባህሪያት በስምንት ከፋፍላ እንዲህ ታቀርባቸዋለች።

1. ጥንካሬ

እኒህ የዕድሜ ባለፀጋዎች ከሚጋሯቸው ባህሪያት አንዱ ጥንካሬ ነው። ለመኖር ያላቸው ጉጉት፣ ንቃታቸው እና ጉልበታቸው ከሌሎች ለየት ያደርጋቸዋል።

“በጣም የሚገርም ነው። ያናገርናቸው ሴንቴናሪያኖች የመኖር ፍላጎታቸው እጅግ ከፍ ያለ ነው” ስትል ማሪያ ዶሎረስ ሜሪኖ ለቢቢሲ ተናግራለች።

“ስታናግሪያቸው 100 ዓመት የደፈኑ አይመስሉም። በጠቅላላው በቃ በጣም ወጣት የሆነ ሰው የምትናጋሪ ነው የሚመስለው” ትላለች።

ማሪያ ለጥናቷ ካናገረቻቸው ሰዎች መካከል 98 ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ሥራ ይሠሩ የነበሩ ወንዶች እና ሴቶች ይገኙበታል።

የዕድሜ ባለፀጋዎቹ ጭንቅላታቸውንም ሆነ አካላቸውን የሚያንቀሳቅስ ሥራ ከመሥራት አይቦዝኑም። በየቀኑ ደረጃ ይወጣሉ፤ ይወርዳሉ፣ ካርታ ይጫወታሉ፣ ሶዱኩ የተሰኘው የቃላት ጨዋታንም ያዘወትራሉ።

ስቴሲ አንደርሰን የኒው ኢንግላንድ ሴንቴናሪያን ስተዲ ጥምር ዳይሬክተር ናት። ይህ መቀመጫውን በአሜሪካዋ ቦስተን ከተማ ያደረገ ማዕከል 100 ዓመት የደፈኑ የዕድሜ ባለፀጋዎችን ያጠናል።

ስቴሲ እነዚህን ሰዎች አንድ ከሚያደርጋቸው መለያ መካከል አንዱ ጥንካሬ መሆኑን ትስማማበታለች።

“አብዛኞቹ ሕይወትን በደንብ እንደሚያጣጥሙ ይናገራሉ። ይህ ለእኔ በጣም የሚደንቅ ነገር ነው” ብላለች ስቴሲ ለቢቢሲ።

በተለያዩ አካላዊ እና አእምሯዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ይሳተፋሉ
የምስሉ መግለጫ,በተለያዩ አካላዊ እና አእምሯዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ይሳተፋሉ

2. ከሰው ጋር ግንኘኑት

በማሪያ ዶሎረስ ሜሪኖ ጥናት መሠረት ዕድሜያቸው ከ100 የተሻገረ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት በጣም ጤናማ ነው።

“ከቤተሰቦቻቸው ከጓደኛና ከወዳጆቻቸው ጋር መልካም ግንኙነት አላቸው። ከቻሉ ሌሎችን ከመርዳት ወደኋላ አይሉም። ሰዎች እንደሚወዷቸው ይሰማቸዋል። ይህ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው” ትላለች።

ስቴሲ አንደርሰን እንደምትለው 100 ዓመት ያለፋቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ “ከቤት ወጣ ብለው አዳዲስ ሰዎችን መተዋወቅ የሚሹ ናቸው።”

“ነገር ግን 100 ዓመት የሞላው ሰው አብዛኞቹን ጓደኞቹን አሊያም ወዳጅ ዘመዶቹን በሞት ማጣቱ አይቀርም። ስለዚህ ወጣ ብሎ አዳዲስ ሰዎችን መተዋወቅ እጅግ አስፈላጊ ነው” ትላለች።

ማርጋሪታ ፍሎሬዝ ጓደኞች “በጣም ጠቃሚ ናቸው” ትላለች።

3. ቁርጠኝነት

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ሌላኛው 100 ዓመት የደፈኑ የዕድሜ ባለፀጋዎች የሚጋሩት ነገር ቁርጠኝነት ነው።

“በጠቅላላው ኃላፊነት የሚሰማቸው ናቸው። ተፎካካሪ እና ጠንካራ ሠራተኞች ናቸው። ያሰቡትን ነገር ከማሳካት ወደኋላ አይሉም” የምትለው ማሪያ ናት።

ዘ ኒው ኢንግላንድ ሴኔቴናሪያን ስተዲ የተሰኘው ማዕከል አንድ ክፍለ ዘመን የደፈኑ ሰዎች ልጆችንም ሲያጠና ቆይቷል።

ስቴሲ አንደርሰን እንደምትለው ልጆቹ በአብዛኛው “የወላጆቻቸውን ፈለግ የሚከተሉ ናቸው።”

“የዛሬ 20 ዓመትም ቢሆን ረዥም ዓመት መኖር እና የሕይወት ግብ የሚያይዛቸው ነገር አለ። ማሳካት የሚፈልጉት ግብ አላቸው። እያንዳንዷ ቀን ዓላማ አላት” ትላለች።

“ለምሳሌ ጃፓን የሚኖሩ የዕድሜ ባለፀጎች ‘ኢኪጋይ’ የሚባል ፅንሰ-ሐሳብ አላቸው። ይህ ማለት እያንዳንዷን ጥዋት ለመነሳት ምክንያት አላቸው ማለት ነው። ይህ በሌላ ቋንቋ የሕይወት ግብ ማለት ነው።”

ስቴሲ አክላ “እኔ እንደሚመስለኝ ሰዎች 100 ዓመት መኖር ከፈለጉ ይህ ትልቅ ሚና የሚጫወት ነው” ትላለች።

ጥናቱ እንደሚለው መከራን መሻገር መቻል ብዙ ዓመት ለመኖር አንዱ አስፈላጊ መሣሪያ ነው።

ከሌሎች ጋር ጊዜን ማሳለፍ እና በማኅበራዊ እንቅስቀሴዎች ላይ መሳተፍን ይመርጣሉ
የምስሉ መግለጫ,ከሌሎች ጋር ጊዜን ማሳለፍ እና በማኅበራዊ እንቅስቀሴዎች ላይ መሳተፍን ይመርጣሉ

4. ፅናት

በርካታ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ክፍለ ዘመን የደፈኑ ሰዎች ከሚጋሯቸው ሥነ-ልቦናዊ ባህሪያት መካከል አንዱ ፅናት ነው።

ፅኑ መሆን ማለት ፈተናን መቻል ማለት ነው። እንዲያውም ይህን ልምድ ተጠቅሞ የበለጠ ጠንካራ መሆን ረዥም ዓመት ለመኖር መሠረታዊ ነው።

“በጣም ጠንካራ መሣሪያ ነው። ፅናት ካለን የሚገጥመንን መከራ ተሻግረን ነገን ማየት እንችላለን። ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ ሳይጋጥመን ወደፊት መገስገስ አያቅትነም” ትላለች ሜሪኖ።

“ረዥም ዓመት የኖሩ ሰዎች አስቸጋሪ ወቅት አልፈው ልምድ አዳብረዋል ማለት ነው። ለምሳሌ ጦርነት እና ወረርሽኝ አልፈዋል፤ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን በሞት አጥተዋል።”

ስቴሲ አንደርሰን በዚህ ትስማማለች።

“እርግጥ ነው ሐዘን ይሰማቸዋል፤ አይሰማቸውም ማለት አይቻልም። ነገር ግን እሱን አልፈው ወደፊት ማየት ይችላሉ” ትላለች ስቴሲ።

5. በቁጥጥር ሥር ያለ ሕይወት

አጥኚዎች እንደሚሉት ከአንድ ክፍለ ዘመን ለላቀ ጊዜ እዚህች ምድር ላይ የኖሩ ሰዎች ውሳኔ ለመወሰን አይሳሱም፤ ሕይወታቸውን ተቆጣጥረው መኖር ይችላሉ።

“ብዙውን ጊዜ ሕይወታቸውን የሚመሩት እነሱ በፈቀዱት መንገድ ነው” ስትል ሜሪኖ ታስረዳለቸ።

“ብዙ ዕድል እንዴት መፍጠር እንዳለባቸው ያውቃሉ። ከዚያ ቀጥሎ የትኛውን መንገድ መከተል እንዳለባቸው ይገነዛበሉ።”

6. ዕውቀት መገብየት

የማሪያ ዶለረስ ሜሪኖ የቅርብ ጥናት እንደሚጠቁመው ሴንቴናሪያኖች ጭንቅላታቸውን ንቁ ማድረግ ይመርጣሉ።

አዲስ ነገር የማወቅ ጉጉት አላቸው። ትምህርት መገብየት ይወዳሉ። ራሳቸውን ያስተምራሉ።

ለዚህ ጥናት ቃለ-መጠይቅ ያደረጉ ሰዎች በዓለማችን ዙሪያ ምን እየሆነ እንዳለ ማወቅ ይፈልጋሉ፤ አሊያም ለራሳቸው የሚሆን አዲስ ዕውቀት ለመገብየት ዝግጁ ናቸው።

“አብዛኞቹ በጣም አንባቢ ናቸው። በጣም በርካታ መጽሐፍት አሏቸው” ትላለች ሜሪኖ።

ማርጋሪታ ፍሎሬዝ አንዷ ናት። በአሁኑ ወቅት የካቶሊክ ሊቀ-ጳጳስ ፍራንሲስን የሕይወት ታሪክ የሚዳስስ መጽሐፍ እያነበበች ነው።

“ብዙ ነገር አነባለሁ። ከፋሽን ጋዜጣ ጀምሮ እስከ የፍቅር ልብ-ወለድ ድረስ ማንበብ ደስ ይለኛል” ስትል በኩራት ትናገራለች።

ቼዝ የሚጫወቱ አዛውንቶች

7. ቀና አስተሳሰብ

ስቴሲ እንደምትለው ከሆነ “100 ዓመት የደፈኑ ሰዎች በእርግጥም በጣም ቀና አስተሳሰብ ያላቸው ናቸው።”

“100 ዓመት ሞልቷቸው «እስካሁን ባልቆይ ደስ ይለኝ ነበር» የሚሉ ሰዎች ማግኘት በጣም ከባድ ነው። ነገር ግን አንድ የ40 ዓመት ሰው እስከ 100 መኖር ትፈልጋለህ? ቢባል «አልፈልግም» እንደሚል እሙን ነው።”

የሜሪኖ ጥናት እንደሚያሳየው ቀና አስተሳሰብ አላቸው ማለት ሁሌም “ደስተኛ” ናቸው ማለት አይደለም። ነገር ግን “በየቀኑ በሕይወታቸው ባሉ ነገሮች ራሳቸውን ዘና ማድረግ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ ትልቅ ነገር ነው” ትላለች ምሑሯ።

ማርጋሪታ ፍሎሬዝ ሁሌም መንፈሷ የተነቃቃ እንደሆነ ትናገራለች።

“ሁሉም ሰው በጣም ደህና ትመስያለሽ ይሉኛል። እውነት ነው፤ በጣም ደህና ነኝ” ትላለች።

8. ልኅቀት

የመጨረሻው መለያ ባህሪይ ልኅቀት ነው። ይህ ደግሞ ሌሎች ባህሪያትንም ያካትታል።

እንደ ሜሪኖ ከሆነ እነዚህ ሰዎች ማሰብ፣ ማሰላሰል፣ ምክንያታዊነት፣ ለችግሮቻቸው መፍትሔ ማበጀት እና በፍጥነት መማር ይችላሉ።

“አብዛኞቹ 100 ዓመት የደፈኑ ሰዎች ባህሪይ ወደ ልኅቀት ይወስደናል” ትላለች።

“ለምሳሌ በትምህርታቸው እጅግ የላቀ ውጤት የሚያመጡ፤ በሥራ ሕይወታቸውም ስኬታማ ናቸው። ራሳቸውን ያስተምራሉ። ውሳኔ ለመወሰን አይቸገሩም፤ ምንም እንኳ ሥልጠናው ባይኖራቸውም አዲስ ነገር ሲመጣ ራሳቸውን ከመፈተን ወደ ኋላ አይሉም፤ ለመማር እና ለማወቅ ዝግጁ ናቸው፤ የማስታወስ ችሎታቸውም ጥሩ ነው።”

“ማርጋሪታ 107 ዓመት ለመኖር ምን ማድረግ አለብን?” ተብለው ተጠየቁ።

“እኔ እንጃ። ሁሌም ደስተኛ ነኝ። ሁሌም እንቀሳቀሳለሁ፤ ጥልፍ እጠልፋለሁ አሊያም የሆነ ሥራ እሠራለሁ። ይህን በማድረግ ጭንቅላቴ ሥራ እንዳይፈታ አደርጋለሁ። እሱ ያገዘኝ ይመስለኛል” ይላሉ።

ማርጋሪታ፤ “ላ ሬይና” የተሰኘው የሳንዲዬጎ 100 ዓመት ያለፋቸው ጓደኛሞች ስብስብ ትልቋ አባል ናቸው።

እርግጥ ነው እየደከመች እየመጣች እንደሆነ ብታምንም ያለችበት ማኅበረሰብ 110 ዓመት ከደፈኑ ትልቅ አከባበር ሊያደርጉላት ቃል ገብተዋል።

“ትልቅ በዓል ይጠብቀኛል፤ ስለዚህ የማርፍበት ጊዜ የለኝም” ይላሉ በደስታ ተሞልተው።