
ከ 5 ሰአት በፊት
የአውስትራሊያ ፖሊስ ትናንት ቅዳሜ ሚያዚያ 5/2016 ዓ.ም. በገበያ ማዕከል ውስጥ 6 ሰዎችን በስለት ወግቶ የገደለው ግለሰብ የአእምሮ ታማሚ ነው አለ።
ጆኤል ካኡቺ የተባለ የ40 ዓመት ጎልማሳ በሲድኒ ከተማ በሚገኘ የገበያ ማዕከል ውስጥ በርካታ ሰዎችን በስለጥ አጥቅቶ አምስት ሴቶችን እና 1 ወንድ የገደለ ሲሆን ጨቅላ ሕጻናን ጨምሮ በርካቶችን አቁስሏል።
የአውስትራሊያ ባለስልጣናት ግለሰቡ ይህን ጥቃት እንዲፈጽም ያደረገው የገጠመው የአእምሮ ጤና መቃወስ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በጥቃቱ ወቅት አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች ሴቶች የነበሩ ሲሆን ግለሰቡ ሆነ ብሎ ሴቶችን ዒላማ ስለማድረጉ ምርመራ ይደረጋል ተብሏል።
ጆኤል ጥቃት በፈጸመበት የገበያ አዳራሽ ውስጥ ከፖሊስ በተተኮሰ ጠይት ተገድሏል።
የኒው ሳውዝ ዌልስ ፖሊስ ኮሚሸነር ካረን ዌብ የስለት ጥቃቱ የሽብር ወንጀል ተደርጎ አይታይም ብለዋል።
ጆኤል በሲድኒ ከተማ በሚገኝ ዕቃ ማስመጫ መጋዘኑ ውስጥ የተደረገ ብርበራ ጥቃቱን እንዲፈጽም ሊያነሳሰው የሚችል ምክንያት አልተገኘም ብለዋል የፖሊስ ኮሚሽነሯ።
- ፕሬዝዳንት ባይደን እስራኤል የኢራንን ጥቃት የመከተችው በአሜሪካ ድጋፍ ነው አሉከ 6 ሰአት በፊት
- ኢራን በእስራኤል ላይ የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶችን ከፈተችከ 7 ሰአት በፊት
- እስራኤል የምትመካበት የሚሳኤል እና የሮኬቶች ማምከኛ ‘አይረን ዶም’ ምንድን ነው?ከ 7 ሰአት በፊት
በዚህ ጥቃት ከተገደሉት አምስት ሴቶች መካከል አንዷ አሸሊ ጉድ የምትባል እናት ነች። ይህች እናት ጥቃቱ ሲፈጸምባት የ9 ወር ጨቅላ ዕድሜ ያላት ልጇን ታቅፋ የነበረ ሲሆን ሕጻኗም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባት ሕክምና እየተደረገላት ነው ተብሏል።
አንድ የዓይን እማኝ ለአውስራሊያው ናይን ኒውስ ሲናገረ፤ “እናቲቱ በስለት ከተወጋች በኋላ ሕጻኗን ወደ እኔ ወርውራ ወደቀች” ብሏል።
የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር ራይን ፓርክ የ9 ወር ዕድሜ ያላት ጨቅላ ትናንት ቀዶ ሕምክና እንደተደረገላት ገልጸው በአሁኑ ወቅት ለሕይወቷ አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆና ከፍተኛ ክትትል እየተደረገላት ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር አንቶኒያ አልባኒስ የጥቃቱን አስቃቂነት ለመግለጽ በቂ ቃላት የሉኝም ያሉ ሲሆን ያለምንም ድጋፍ ጥቃት ፈጻሚው ላይ እምጃ የወሰደችውን የፖሊስ አባል “ጀግኒት” ሲሉ አድንቀዋል።
ኢንስፔክተር ኤሚ ስኮት የተባለችው የፖሊስ አባል እራሷን አደጋ ላይ ጥላ ለሌሎች ስጋት የነበረውን ግለሰብ አስወግዳለች ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ባለስልጣናት በትላንቱ ጥቃት ጉዳት የደረሳባቸው 9 ሰዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ተናግረዋል።