ሱዳንን አደጋ ላይ የጣለው ጦርነት

ከ 7 ሰአት በፊት

በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) መካከል ግጭት ተቀስቅሶ አገሪቱን ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ከዘፈቋት አንድ ዓመት ሞላ።

በዋና ከተማይቱ ካርቱም የተጀመረው ሁከት እና ብጥብጥ በመላ አገሪቱ ተዛምቷል። ጦርነቱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ሲሆን ህንፃዎች እና መሠረተ ልማቶችም ወድመዋል።

አንድ ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊ ለቢቢሲ አረብኛ እንደተናገሩት አሁን በዓለም ላይ የከፋ የረሃብ ቀውስ ያለው ሱዳን ውስጥ ነው።

በዓለም የምግብ ፕሮግራም የሱዳን የድንገተኛ አደጋ አስተባባሪ ማይክል ደንፎርድ “ጥፋት አጋጥሞናል። ፍርሃቴ ችግሩ ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይደርስ ነው” ብለዋል።

ወደ 18 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች “በጣም ተርበዋል።” ይህ አሃዝ ወደ 25 ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል የሚሉ ሲሆን ብዛቱም ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የሱዳን አጠቃላይ ሕዝብ ይወክላል።

በሚቀጥሉት ወራት 220 ሺህ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ በሚል የእርዳታ ባለሙያዎችም አስጠንቅቀዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት በአገሪቱ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ፈንድቶ ወደ ለየለት ጦርነት አምርቷል።

ወደ 14 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን የሚገልጸው የተባበሩት መንግሥታት ይፋዊው አሃዝ በጣም ዝቅተኛ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች እየገለጹ ነው። እውነተኛው አሃዝ ከዚህ በእጅጉ ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችልም ይገምታሉ።

ከስምንት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሱዳናውያን ቤታቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል። በርካቶች ከቤት ንብረታቸው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ድንበር ተሻግረው ተሰደዋል።

የዓለም ምግብ ድርጅቱ ማይክል ደንፎርድ

የፈረሰችው ታሪካዊ ከተማ

ዋና ከተማዋ ካርቱም፣ ኦምዱርማን እና ባህሪ የተባሉ አጎራባች ከተሞችን በማጣማር ታላቋ ካርቱም ይባላሉ። ከጦርነቱ በፊት ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች መኖሪያም ነበሩ።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የከተማውን ሰፊ ክፍል ተቆጣጥሮታል። የሱዳን ጦር በቅርቡ ጥቃቱን በማጠናከር ላይ ሲሆን፣ በኦምዱርማን የሚገኘውን የመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና መሥሪያ ቤትን ተቆጣጥሯል።

በቢቢሲ ቬሪፋይ እና በቢቢሲ አረብኛ ያጣሯቸው ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች በሱቆች፣ በሆስፒታሎች፣ በዩኒቨርሲቲዎች እና በባንኮች ላይ የደረሱትን ጉዳቶች ያሳያሉ።

ከተጎዱት ህንፃዎች መካከል ባለፈው መስከረም በእሳት የጋየው የግሬተር ናይል ፔትሮሊየም ኦይል ካምፓኒ ህንጻ ይገኝበታል።

በግጭቱ ምክንያት ቢያንስ ሦስት ሆስፒታሎች እና አንድ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ መጠን ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የካርቱም ነዋሪ የሆኑት ዶ/ር አላ ኤል-ዲን ኤል ኑር ለቢቢሲ አረብኛ እንደተናገሩት ሆስፒታሎች ከፍተኛ የሆነ የህክምና ቁሳቁስ እጥረት እያጋጠማቸው ነው።

“እንደ ሐኪም ደኅንነት አይሰማንም። የህክምና ቁሳቁስ እና መድኃኒቶችም ተዘርፈዋል” ብለዋል።

የዓለም ምግብ ድርጅትም የመሠረተ ልማት ውድመት ችግሩን እያባባሰው ነው ብሏል።

“የምግብ እጦቱን እያጠናከረው ነው” ሲሉ ደንፎርድ አክለዋል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ እና ቢቢሲ አረብኛ ለሰብአዊ ቀውሱ መባባስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ተጨማሪ ምሳሌዎችን ከካርቱም ሰብስበዋል።

ኦምዱርማን እና ባህሪ ከተሞችን የሚያገናኘው የሻምባት ድልድይ ባለፈው ኅዳር ወር ፈርሷል። ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የናይል ወንዝን በመሻገር መሣሪያ እና ጦሩን የሚያንቀሳቅስበት ስትራቴጂያዊ ድልድይ ነበር።

በጥር ወር ከካርቱም በስተሰሜን አቅጣጫ የሚገኘው አል-ጄይሊ የነዳጅ ማጣሪያ በአካባቢው ውጊያ ምክንያት በእሳት ተያይዟል። ማጣሪያው ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የበላይነት ለመያዝ በሚያደርጉት ግጭት መካከል ለመውደቅ ተገዷል።

በጦርነቱ ከወደሙት ተቋማት መካከል የካርቱም መለያ የነበረው ህንጻ በእሳት በተያያዘበት ጊዜ
የምስሉ መግለጫ,በጦርነቱ ከወደሙት ተቋማት መካከል የካርቱም መለያ የነበረው ህንጻ በእሳት በተያያዘበት ጊዜ

በዩናይትድ ኪንግደም የግጭት እና የአካባቢ ጥበቃ ተመራማሪ የሆኑት ሊዮን ሞርላንድ በዚህ ከኅዳር 2023 እስከ ጥር ባሉት ወራት በ32 ትላልቅ የነዳጅ ማጠራቀሚያዎች ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

“ምን ጥንቃቄ ካልተደረገ ነዳጅ እየፈሰሰ የከርሰ ምድር ውሃን እና የግብርና አካባቢዎችን ሊያዳርስ ይችላል” ሲሉ ለቢቢሲ አረብኛ ተናግረዋል።

“ይህ አዲስ ብክለት በጣቢያው ቀደም ሲል የነበረውን የመሬት ብክለትን ያባብሳል። መጀመሪያም ቢሆን ችግሩ ሰፊ መሆኑን ከሳተላይት ምስሎች ማየት ይቻል ነበር።”

የሳተላይት ምስሎችም እንደሚያሳዩት ከሆነ በካርቱም ያሉ ሦስት የውሃ ማጠራቀሚያ ጣቢያዎች ባዶ መሆናቸውን ነው። ይህ እንዴት እንደተከሰተ ግልጽ አይደለም።

የካርቱም ነዋሪው የ31 ዓመቱ ሐሰን መሐመድ ላለፉት አራት ወራት በውሃ እና በመብራት መቆራረጥ ሲቸገር መቆየቱን ለቢቢሲ አረብኛ ተናግሯል።

“ንፁህ ውሃ ለማግኘት ረዥም መንገድ መጓዝ ወይም ለመጠጥ የማይመች የወንዞችን ውሃ ለመጠቀም እንገደዳለን። ይህም ለበሽታዎች ሥርጭት ምክንያት ሆኗል” ብሏል።

የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ የካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ትልቁ የጦርነት አውድማ በመሆኑ እና በረራዎች በመቋረጣቸው የአገሪቱ የዕርዳታ አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ጦርነቱ በተቀሰቀሰ በ48 ሰዓታት ከአየር ማረፊያው ያገኛቸውን በርካታ ቪዲዮዎችን አረጋግጧል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ያረጋገጠው የመጀመሪያው ቪዲዮ እንደሚያሳየው ከአውሮፕላን ማረፊያው ሰሜናዊ አቅጣጫ ሲሆን፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አባላት መንደርደሪያው ላይ እየሮጡ ወደ አየር ማረፊያ ህንጻዎች ሲተኩሱ ታይቷል።

ብዙም ሳይቆይ ቢያንስ ከአንድ አውሮፕላን ከፍተኛ ጭስ ሲወጣ ነበር።

በሌላ ቪዲዮ ደግሞ ምናልባት ልክ እንደ ቀደመው ቪዲዮ ሁሉ በእሳት የተያያዘ ተመሳሳይ አውሮፕላኖችን ቢያሳይም ይኼኛው ግን ከአውሮፕላን ማረፊያው ምሥራቃዊ ክፍል ነው።

የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በካርቱም ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን በማውደም ቢከሰሱም ሁለቱም ግን እርስ በእርሳቸው ጣት ይቀሳሰራሉ።

የተኩስ አቁም ካልተደረሰ ህጻናት አደጋ ላይ ይወድቃሉ

መጨረሻ ያለው አይመስልም

በሌሎች የሱዳን ክፍሎች ጦርነቱ እየተካሄደ ነው። ለዓመታት በአፍሪካ እና በአረብ ማኅበረሰቦች መካከል የዘለቀው ብጥብጥ የታየበት ምዕራብ ዳርፉርም ገፈት ቀማሽ ሆኗል።

ሴንተር ፎር ኢንፎርሜሽን ሪዚሊያንስ በቅርቡ ባደረገው ጥናት መሠረት በምዕራብ ሱዳን ብቻ ከ100 በላይ መንደሮች ተቃጥለዋል።

የሱዳናዊው የምጣኔ ሐብት ተንታኝ ዋኤል ፋህሚ እንደሚለው ከሆነ ጦርነቱ በኢኮኖሚው እና በምግብ ሥርዓቱ ላይ ያስከተለው ጉዳት አስከፊ የሚባል ነው።

“ኢኮኖሚው በግማሽ ቀንሷል። 60 በመቶ የሚሆነው የግብርና እንቅስቃሴ ቆሟል” ብሏል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንቅስቃሴም በተመሳሳይ ደካማ ነው።

“በሱዳን ዛሬ እየሆነ ያለው ፍፁም አሳዛኝ ነገር ነው” ብለዋል ማይክል ደንፎርድ።

የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ በርካታ ዓለም አቀፍ ሙከራዎች ቢደረጉም አልተሳኩም። አዲስ ሙከራ በሳዑዲ ዋና ከተማ ጄዳ እንዲጀመር ግፊት እየተደረገ ነው።