የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ

ከ 6 ሰአት በፊት

ከአንድ ሳምንት በፊት በርካታ የሩሲያ ድሮኖች ወደ ሰሜን ምስራቋ የዩክሬን ከተማ ኻርኪቭ ተተኮሰው ጉዳት አድርሰዋል።

ሁለተኛዋ ትልቋ ከተማ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በተደጋጋሚ ጥቃት ከሚደርስባቸው ቦታዎች አንደኛዋ ናት።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ወደ ሥፍራው ለነበስ አድን ሥራ ሲመጡ በተከፈተ ሁለተኛ ዙር ጥቃት ሶስቱ ተገድለዋል።

በተመሳሳይ ሳምንት አርብ ዕለት በዩከሬኗ ዛፖሪዣዚያ ከተማ ሩሲያ የሚሳዔል ጥቃት ካደረሰች በኋላ ወደ ሥፍራው የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እና ጋዜጠኞች መጥተው በሁለተኛ ዙር ጥቃት ተገድለዋል።

በአጠቃላይ በዚህ ጥቃት አራት ሰዎች ሲገደሉ ሁለት ጋዜጠኞችን ጨምሮ 20 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

በሁለቱ ከተማዎች ሩሲያ ያደረሰችው ጥቃት “ደብል ታፕ” ይባላል። ይህ ማለት በመጀመሪያው ዙር ጥቃት የደረሰውን አደጋ ለመታደግ የሚመጡ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ላይ የሚደረግ ጥቃት ነው።

ሩሲያ መሰል ጥቃት ስታደርስ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም።

የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ባለፈው መጋቢት በኦዴሳ ከተማ የደረሰውን ተመሳሳይ ጥቃት ተከትሎ በሰጡት አስተያየት “ወራዳ ተግባር” ማለታቸው ይታወሳል።

የዩክሬን ባለሥልጣናት ሩሲያ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ “ደብል ታፕ” ጥቃቶችን እየፈፀመች ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።

የኻርኪቭ ክልል አስተዳዳሪ ኦሌህ ሴኔሁቦቭ ለዩክሬን መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ሩሲያ “ቀን ከሌት” የምታደርገውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች ብለዋል።

ባለፈው ሐሙስ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን በቅርብ ሳምንታት የሩሲያ “ደብል ታፕ” ጥቃቶች ጨምረዋል ካሉ በኋላ ሩሲያ መሰል ጥቃቶችን “እንድታቆም” አሳስበዋል።

የዩክሬን አደጋ ጊዜ ሠራተኞች ጥቃት ሲደርስ ቀድመው ነው የሚመጡት። ነገር ግን የሩሲያ ጥቃቶች ለሕይወታቸው አደጋ እየሆኑ እንደመጡ ይናገራሉ።

የዩክሬን አደጋ ጊዜ መሥሪያ ቤት ሩሲያ በአውሮፓውያኑ የካቲት 2022 ዩክሬን ላይ ጥቃት ከጀመረች ጊዜ ጀምሮ 91 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ተገድለዋል፤ 340 ደግሞ ቆስለዋል ይላል።

በዩክሬን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ማለትም የሕክምና ሰዎችና የእሳት አደጋ ተቆጣጣሪዎች ቁጥር ከምንም ጊዜውም በላይ የመነመነ ሲሆን የሩሲያ ደብል ታፕ ጥቃቶች ደግሞ ሌላ አደጋ ደግነዋል።