
ከ 8 ሰአት በፊት
የሐማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሃኒዬህ ሦስት ልጆች እና አራት የልጅ ልጆቻቸው ረቡዕ ዕለት እስራኤል ጋዛ ውስጥ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ተገድለዋል።
የሦስቱ ልጆች እና የልጅ ልጆች መገደል የተሰማው የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነትን አስመልከቶ አዲስ ንግግር በካይሮ እንደሚጀመር እየተነገረ ባለበት ወቅት ነው።
ሦስቱ ወንድ ልጆቻቸው ሃዜም፣ አሚር እና መሐመድ ከህጻናት አራት ልጆቻቸው ጋር የተገደሉት በጋዛ ከተማ አቅራቢያ ወደሚገኘው አልሻቲ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ከዘመዶቻቸው ጋር የኢድ በዓልን ለማክበር በመኪና እየተጓዙ በነበረበት ወቅት ነው።
በዚህ ጥቃት የተገደሉት የእስማኤል ሦስቱ ሴት የልጅ ልጆች እና አንድ ወንድ ሲሆኑ፣ አነሱም ሞና፣ አማል፣ ካሊድ እና ራዛን እንደሆኑም ሐማስ አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር በማዕከላዊው ጋዛ ሰርጥ “ሦስት የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ታጣቂዎችን ማስወገዱን” ጠቁሞ የእስማኤል ሃኒዬህ ልጆች መሆናቸውን ገልጿል።
ሃኒዬህ የልጆቻቸው እና ልጅ ልጆቻቸውን ግድያ የሰሙት በጥቃቱ የቆሰሉ ፍልስጤማውያን ለህክምና እሳቸው ወደሚኖሩበት የኳታሯ መዲና ዶሃ በመጡበት ወቅት ነው።
የልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸው መገደል ሐማስ በጋዛ ላይ እንዲደረስ በሚፈልገው ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ዙሪያ በሚደረገው ንግግር ላይ ለውጥ እንደማያመጣ መሪው ተናግረዋል።
እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን ጥቃት ተከትሎ 60 የሚሆኑ የቤተሰብ አባላት እንደተገደለባቸው ሃኒዬህ ገልጸዋል።
እንደ ሐማስ ምንጮች ሃኒዬህ 13 ወንድ ልጆች እንዳሏቸው የሚታመን ሲሆን፣ አንዳንዶቹም መኖሪያቸው ኳታር ዶሃ ውስጥ ነው።
- የሐማስ መሪ ሦስት ልጆቻቸው በእስራኤል የአየር ጥቃት እንደተገደሉባቸው ተናገሩ11 ሚያዚያ 2024
- እስራኤል ልታጠፋው ቀን ከሌት የምትፈልገው በጋዛ የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ማን ነው?23 ህዳር 2023
- በሞት ጥላ ስር ሆነው እስራኤልን እንቅልፍ የነሷት የሐማስ መሪዎች እነማን ናቸው?14 ጥቅምት 2023
የሃኒዬህ ልጆች በወታደራዊ እንቅስቃሴ ይሳተፉ ነበር?
በመሬት ላይ ያሉ ሁሉም መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከእስማኤል ሃኒዬህ ልጆች አንዳቸውም በወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ እንዳልነበሩ ነው።
አንዳንዶቹ በሐማስ ወታደራዊ ክንፍ፣ ኢዝ አል ዲን አል ቃሳም ብርጌድ ሥልጠና ቢወስዱም በወታደራዊ አገልግሎት ውስጥ ተሳትፎ አልነበራቸውም።
እንዲሁም በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ የላቸውም። የሐማስ መሪ ሃኒዬህም ከሮይተርስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ልጆቻቸው የሐማስ ተዋጊዎች አልነበሩም ብለዋል።
በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት ሦስቱ የሐማስ መሪ ልጆች በወታደራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ ቢኖራቸው ኖሮ ያን ያህል በነጻነት እንደማይንቀሳቀሱ የሚናገሩት በጋዛ የፖለቲካ ተንታኝ እና የሐማስ ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት ያሲር አቡ ሃይን ናቸው።
እነዚህ ልጆች በወታደራዊ እንቅስቃሴ ተሳትፎ ቢኖራቸው ራሳቸውን ለመደበቅ እና የድርጅቱ መሪዎች በአብዛኛው እንደሚያደርጉት በዋሻዎች ውስጥ ወይም በማይታወቁ ቦታዎች ይንቀሳቀሱ ነበር ሲሉ ተንታኙ ያስረዳሉ።
የረመዳን ፆም ማለቁን ተከትሎ የሚከበረውን የዒድ አልፈጥር በዓልን ከዘመድ አዝማድ ጋር ለማክበር ከትናንሽ ልጆቻቸው ጋር በሲቪል መኪና ተሳፍረው ሲጓዙ እንደነበርም ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ እንደሆነም ተንታኙ ያሰምራሉ።
የእስማኤል ሃኒዬህ ልጆች እና የልጅ ልጆች መገደል እስራኤል ግራ መጋባቷን እና ወታደራዊ አላማዎቿን ማሳካት አለመቻሏን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው ይላሉ ያሲር አቡ ሃይን።
እስራኤል ወታደራዊ ጠቀሜታ የሌላቸውን ዒላማዎች ላይ እያነጣጠረች ያለችው የሐማስ ዋና መሪዎችን ማግኘት ወይም የተወሰዱባትን ታጋቾች ማስለቀቅ ያሉ ግቦችን ማሳካት ባለመቻሏ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
በተጨማሪም የሐማስ መሪ ልጆች መገደል የአልቃሳም ብርጌድ በቅርቡ ባደረገው ዘመቻ በደቡባዊ ጋዛ ኻን ዩኒስ ከተማ በስተምሥራቅ በምትገኘው ዛና በተሰኝ ስፍራ በርካታ የእስራኤል ወታደሮችን መግደሉን መግለጹን ተከትሎ የእስራኤል ጦር ገጽታውን ለመመለስ ያደረገው ሙከራ ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል።
የተነጣጠሩ ግድያዎች የስለላ ጥረቶችን እንዲሁም ምሥጢራዊ መረጃዎች ማሰባሰብን ቢያስፈልግም ረቡዕ ዕለት የሐማሱን መሪ ልጆች እና የልጅ ልጆች የገደለው የአየር ጥቃት ግን በሲቪል መኪና በግልጽ ሲጓዙ በነበሩ ላይ የተፈጸመ ከመሆኑ አንጻር የስለላ ጥረቶች የሚያስፈልጉት ጉዳይ እንዳልነበረም ያሲር አቡ ሃይን ያስረዳሉ።
እስራኤል ሃኒዬህን ጨምሮ ሁሉንም የሐማስ መሪዎች እንደ “አሸባሪ” ታያቸዋለች። በጥር ወር መጀመሪያ ላይም ምክትላቸው ሳሌህ አል አሮሪ ቤይሩት ውስጥ በድሮን ጥቃት የተገደሉ ሲሆን፣ ከዚህም ጀርባ እስራኤል እንዳለች በሰፊው ይታመናል።

የእስራኤል ፕሮፓጋንዳ በሐማስ መሪዎች ላይ
የእስራኤል ጦር ቀደም ሲል እስማኤል ሃኒዬህን ጨምሮ ከፍልስጤም ግዛት ውጪ በሚኖሩ የሐማስ መሪዎች ላይ ያነጣጠረ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሲያካሂድ ቆይቷል።
በጋዛ ሰርጥ ፀረ ሐማስ ፕሮፓጋንዳ የያዙ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በራሪ ወረቀቶችን በእስራኤል አውሮፕላኖች ተበትነዋል። እነዚህ በረሪ ወረቀቶች ላይ “መሪዎቻችሁ እናንተን በጋዛ እንድትሞቱ ትተዋችሁ ሄደው እነሱ በሚያማምሩ ሆቴሎች በቅንጦት ይኖራሉ” የሚል መልዕክት ለፍልስጤማውያን ሰፍሯል።
ይህ ብቻ አይደለም የእስራኤል የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ፀረ ሐማስ የፕሮፓጋንዳ ይዘቶችን ለማሰራጨት ውለዋል።
ባለፈው ሳምንት የእስራኤል ፖሊስ የእስማኤል ሃኒዬህን እህት በደቡባዊ እስራኤል፣ ኔጌቭ ግዛት በቴልቪሻ ከተማ በቁጥጥር ስር አውሏታል።
ፖሊስ በሐማስ መሪ እህት ላይ ከበባ በማድረግ የፈተሸ ሲሆን “የእስራኤል መንግሥትን አደጋ ላይ በሚጥሉ ወንጀሎች” ጋር የሚያገናኛትን ማስረጃ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
የ57 ዓመቷ ሳባህ አብዱልሳላም ሃኒዬህ በቴልቪሻ ታስራ በእስራኤል የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ሺን ቤት ምርመራ እየተደረገባት እንደሆነ ፖሊስ አስታውቋል።
የእስማኤል ሃኒዬህ የበኩር ልጅ አብዱልሰላም አል ባክር በፍልስጤም ፖለቲካ ውስጥ በርካታ ቁልፍ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ ይገኛል።
ከእነዚህም መካከል የፍልስጤም ወጣቶች እና ስፖርት ከፍተኛ ምክር ቤት አባል እንዲሁም ጂብሪል ራጁብ የተሰኘው የፍልስጤም እግር ኳስ ማኅበር ምክትል መሪ ነው።
አብዱልሰላም ባለው ሚናም በፍልስጤም ፖለቲካ ውስጥ ሁለቱን ተቀናቃኝ ቡድኖች ፋታህ እና ሐማስ መካከል ያለውን ልዩነትም ለማጥበብ አስተዋፅኦ አድርጓል።
በተለይም በተለያዩ መሪዎች በሚተዳደሩት ጋዛ እና ዌስት ባንክ መካከል ስፖርት ብሔራዊ አንድነትን ለማምጣት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት እንደሚያምን ሲናገር ይደመጣል።
ነገር ግን በቅርቡ በየካቲት ወር በእስያ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ በኳታር እና በኢራን መካከል የተካሄደውን የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ መታደሙ በጋዛ ነዋሪዎች እና በማኅበራዊ ሚዲያ ተሟጋቾች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል። በጋዛ እየተካሄደ ካለው ጦርነት አንጻር በዚህ ጨዋታ መታደሙም አግባብ እንዳልሆነም በርካቶች ስሜታቸውን አንጸባርቀዋል።
ከእስራኤል መከላያ ሠራዊት ጋር ግንኙነት ያላቸው የእስራኤል ሚዲያዎች የአብዱልሰላምን ምስል በተለያዩ መድረኮች በማጋራት የንቅናቄውን እንዲሁም የፖለቲካ ጽህፈት ቤቱን ስም ለማጠልሸት በሚያደርጉት ጥረትም ተጠቅመውበታል።
ሃኒዬህ የሐማስን ንቅናቄ ከፍተኛ አመራር የሆኑት በአውሮፓውያኑ 2017 ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜም በቱርክ እና ኳታር መካከል ተደጋጋሚ ጉዞ ያደርጋሉ።
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ የጣለችውን የጉዞ ማዕቀብም በመተላለፍ ነው ይህንን ጉዞ የሚያደርጉት። በቅርብ ጊዜ የሚደረገውን የተኩስ አቁም ስምምነት ድርድሮችን የሚመሩ ሲሆን፣ በቅርቡም ወደ ኢራን እና ሩሲያ ተጉዘዋል።