
ከ 6 ሰአት በፊት
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እስራኤል ከኢራን የተቃጡባትን በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖችን እና ሚሳኤሎችን የመከተችው በአሜሪካ ድጋፍ ነው አሉ።
ፕሬዝዳንቱ ጥቃቶቹን በማምከን የተሳተፉ የአሜሪካ ጦር ኃይል አባላትን አሞካሽተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ባወጡት መግለጫ ከዚህ የኢራን ጥቃት አስቀድሞ አሜሪካ የጦር አውሮፕላኖችን እና መርከቦችን ወደ ቀጠናው ማስጠጋቷን ተናግረዋል።
“እነዚህን ጥቃቶች እጥብቄ አወግዛለሁ” ያሉት ባይደን “ከጠቅላይ ሚንስትር ኔታኒያሁ ጋር በስልክ በተነጋገርንበት ወቅት አሜሪካ ለእስራኤል ደኅንነት ከብረት የጠነከረ ድጋፏ እንደማይለያት አረጋግጫለሁ” ብለዋል።
እስራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖች እና ሚሳኤሎች ከኢራን እንደተተኮሱባት ገልጻለች።
እስራኤል አብዛኛዎቹን ከኢራን፣ ሶሪያ እና ኢራቅ የተተኮሱ ድሮችን እና ሚሳኤሎችን መትታ ብትጥልም በደቡባ እስራኤል በሚገኝ የጦር ሰፈር ውስጥ የወደቁ ሚሳኤሎች መኖራቸውን አስታውቃለች።
ኢራን ከ11 ቀናት በፊት በሶሪያ ዋና ከተማዋ በሚገኘው ቆንስላ ጽህፈት ቤቷ ላይ በተፈጸመው ጥቃት እስራኤልን ተጠያቂ አድርጋ እስራኤል ለዚህ ጥቃቷ ዋጋ ትከፍላለች በማለት ስትዝት ቆይታለች።
ባይደን እስራኤል ከኢራን የተፈጸማትን ጥቃት መከላከል ችላለች ብለዋል።
- ኢራን በእስራኤል ላይ የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶችን ከፈተችከ 7 ሰአት በፊት
- በእስራኤል የአየር ጥቃት ስለተገደሉት የሐማሱ መሪ እስማኤል ሃኒዬህ ልጆች የሚታወቁ ጉዳዮችከ 8 ሰአት በፊት
- እስራኤል የምትመካበት የሚሳኤል እና የሮኬቶች ማምከኛ ‘አይረን ዶም’ ምንድን ነው?ከ 7 ሰአት በፊት
ዛሬ እሁድ ባይደን የካናዳ፣ ፈንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያ፣ ጃፓን፣ ዩኬ እና የአውሮፓ ኅብረት መሪዎችን የሚያካትት የጂ7 ስብሰባ እንደሚጠሩ ገልጸዋል።
ባይደን ከዚህ በተጨማሪም ኢራን በቀጠናው ባሉ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት ላይ ጥቃት ከመፈጸም እንድትቆጠብ አሳስበዋል።
የዋይት ሃውስ የብሄራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ፕሬዝዳንት ባይደን ከእስራኤል እና ከአጋር አገራት ጋር በጥቃቱ ዙሪያ በቅርበት መነጋገራቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል።
ሁለት የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ እንደተናገሩት በአካባቢው ያሉ የአሜሪካ ኃይሎች በርካታ የኢራን ድሮኖችን እና ሚሳኤሎችን መትተው ጥለዋል።
ከአሜሪካ በተጨማሪ በኢራቅ እና ሶሪያ የሚገኝ የዩናይትድ ኪንግደም አየር ኃይል እስራኤል ላይ የተጠቃጣውን የአየር ጥቃት ለማክሸፍ ተሰማርቷል።
የዩኬ መከላከያ ሚኒስቴር ለእስራኤል ጦር ድጋፍ የሚያደርጉ ተጨማሪ የጦር ጀቶች መላካቸውን አስታውቋል።
ፈረንሳይ፣ ካናዳ እና ዩናይትድ ኪንግደም የኢራንን ጥቃት አውግዘው ለእስራኤል ድጋፋቸውን የሰጡ አገራት ናቸው።
በሌላ በኩል የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለእስራኤል ተጨማሪ የጦር ድጋፍ መስጠት የሚያስችል እና ኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ የሚጥል ረቂቅ ላይ እየሰሩ መሆኑን ይፋ አድርገዋል።