
ከ 4 ሰአት በፊት
ከ10 ዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ 2014፤ 276 ታዳጊ ሴቶች ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ ዓለም አቀፍ ታዋቂነት ያላቸው ሰዎች ሳይቀሩ #bringbackourgirls የተሰኘው የማሕበራዊ ሚድያ ዘመቻ ጀመሩ።
እነሆ ክስተቱ 10 ዓመት ቢሆነውም አሁንም በሥፍራው የሚኖሩ ሴቶች በታጣቂ ቡድኖች የመታፈን ስጋታቸው አልቀነሰም።
ኢስተር ያኩቡ ሕይወት ካለ ሰቴች ልጇ ዶርካስ ምን ያክል ከባድ እንደሆነ እንባዋን እየጠረገች ታስታውሳለች።
“ቦኮ ሐራም ልጄን አፍኖ ከወሰደብኝ 10 ዓመት ሆኗል። በጣም ከባድ ነው። ሰዎች በቃ ሕይወትሽን ቀጥይ፤ ሌሎች ልጆች አሉሽ ይሉኛል። ነገር ግን ብቻየን ስሆን ልጄ ድቅን ትልብኛለች።”
ኢስተር የልጇ ዶርካስን ዕቃዎች ቤት ውስጥ ስታይ ሀዘኗ ይበረታል። ይሄኔ ነው ከጥቂት ፎቶዎች በቀር ሌሎቹን ለማስወገድ የወሰነችው።
“የሷን ዕቃዎች ጠቅላላ ሰብስቤ ከቺቦክ ውጭ ላሉ ሰዎች የሰጠሁት ማየት ስለማልፈልግ ነው” ትላለች።
በአውሮፓውያኑ ሚያዚያ 14/2014 ኢስላማዊው ታጣቂ ቡድን ቦኮ ሐራም ቺቦክ ከተማ ካለ አንድ አዳሪ ትምህርት ቤት 276 ሴት ተማሪዎችን አፍኖ ወሰደ።
ይህን አፈና ተከትሎ በማሕበራዊ ሚድያ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ተጀመረ። በተለይ #bringbackourgirls የተሰኘው ዘመቻ ተስፋፋ። የቀድሞ የአሜሪካ ቀዳማዊ እመቤት ሚሼል ኦባማ፣ የኖቤል ሎሬት አሸናፊ ማላላ ዩሱፍዛይ እና ሌሎችም ይህን ዘመቻ ተቀላቀሉ።

ከ10 ዓመታት በኋላ ብዙዎች መታደግ ተችሏል ወይም ሴቶች በራሳቸው ከአጋቾች አምልጠዋል። ነገር ግን ከ276 ተማሪዎች 87ቱ አሁንም በቡድኑ ቁጥጥር ሥር ነው የሚገኙት።
ዶርካስ ከእነዚህ መካከል ናት። ታፍና በተወሰደች ወቅት የ16 ዓመት ታዳጊ ነበረች።
እናቷ ኢስተር ልጇ ምን ሆና ሊሆን ይችላል የሚለውን ማወቅ አለመቻሏ መሸከም የማትችለው ጫና ነው።
“መንግሥታችን ልጆቻችንን ነፃ እንዲያወጣልን እንፈልጋለን። ቤታቸው እንዲያመጣልን እንፈልጋለን። በሕይወት ያሉትን አይተን ደስ ይበለን። በሕይወት ከሌሉም ቁርጣችን ይነገረን እና ይውጣልን።”
ኢስተር ልጇ የት እንዳለች አታውቅም። ነገር ግን ታጣቂዎቹ 2016 በለቀቁት ቪድዮ ላይ ታይታለች። በዚህ ቪድዮ ላይ ዶርካስ ስሜ ማይዳ ነው ስትል ትደመጣለች። ይህ ስም አጋቾቹ ያወጡላት ነው።
“ዶርካስ አሁን ልትሰማኝ ከቻለች በሕይወት እንዳለሁ ነገራታለሁ። ቺቦክ ከተማ አለች እላታለሁ። ተመልሳ መጥታ እኛን እንድታየን፤ ያደገችበትን ቀዬ እንድታየው እፈልጋለሁ።”
ጉዞ ወደ ቺቦክ
ወደ ሰሜን ምስራቋ የናይጄሪያ ከተማ ለመድረስ መጀመሪያ ወደ አማዳዋ ግዛት መሄድ ይጠይቃል። ቺቦክ ለመድረስ በጣም ረዥም ገላጣ እና ደረቅ መሬት በመኪና መጓዝ አለብዎ።
መንገድ ላይ አንድ የቴሌኮም ማማ ወድቆ ይታያል። እንደ አካባቢው ሰዎች ከሆነ ቦኮ ሐራም ኔትዎርክ ለማቋረጥ ያደረገው ነገር ነው። እዚህ የሚኖሩ ሰዎች እንዴት ብለው እርዳታ ይጠራሉ?
ቦኮ ሐራም አሁንም በሥፍራው ይንቀሳቀሳል።
ወደ ቺቦክ ከተማ ከመድረስዎ በፊት ቢያንስ ግማሽ ደርዘን ፍተሻዎችን ማለፍ ግድ ነው። ቺቦክ ከተማ ወታደራዊ መለዮ በለበሱ ሰዎች የተሞላች ናት። ጦር ሠራዊቱ ሁለት የፍተሻ ጣቢያዎች አቋቁሟል። ሰዓት እላፊም ታውጇል።

አዲስ ትምህርት ቤት
ቺቦክ ያለው ሁለተኛ ደረጃ የመንግሥት ትምህርት ቤት አዲስ መልክ አለው። በአውሮፓውያኑ 2021 ነው እንደ አዲስ የተገነባው።
ታዳጊዎቹ ታፍነው የተወሱደበት ማደሪያ ፈርሷል። ከጥቂት የፈራረሱ ብሎኬቶች በቀር ከአስር ዓመት በፊት እዚህ ምን እንደተፈጠረ የሚያሳይ ነገር የለም።
ምንም እንኳ አዲስ ቢሆንም የክሬም ቀለም ያለወ የትምህርት ቤቱ ግድግዳ ቀለም መልቀቅ ጀምሯል። እርግጥ ነው ሥፍራው እጅግ ሞቃታማ ነው። አረንጓዴ ነገር ማየት የሚታሰብ አይደለም።
ትምህርት ቤቱ እንደ አዲስ ከተቋቋመ በኋላ ሙሐማድ ቺሮማ ዳይሬክተር ሆኖ ተቀጥሯል። አሁን የፀጥታው ሁኔታ ከቀድሞው የተሻለ ነው ይላል።
ቺቦክ ከተማ ጥቂት ትምህርት ቤቶች ነው ያሏት። አንደኛው ይህ የሕዝብ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው።
ምንም እንኳ ከተማዋ በጥብቅ ወታደራዊ ጥበቃ ውስጥ ብትሆንም ባለፈው ታኅሣሥ እና ጥር የቦኮ ሐራም ታጣቂዎች ጥቃት አድርሰው 14 ሰዎችን ገድለው ምግብ ሰርቀው ተሰውረዋል።
ፈተና

ማናሴህ አለን ተወልዶ ያደገው ቺቦክ ከተማ ነው። ታዳጊዎች ታፍነው ከተወሰዱ ከስምንት ወራት በኋላ ወደ ፌዴራል መንግሥት መቀመጫዋ አቡጃ አመራ። አቡጃ ሆኖ ላደገባት ከተማ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ሲሆን አልፎ አልፎ ደግሞ እየመጣ ቤተሰቦቹን ይጎበኛል።
“ልጆቹ ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ አሁንም ቺቦክ ውስጥ ብዙ ያልተቀየሩ ነገሮች አሉ። ትምህርት ቤቱም ብዙ አልተቀየረም። የኮምፒውተር ትምህርት የለም፣ ቤተ-ሙከራ የለም፣ ቤተ-መፃሕፍት የለም፣ ውሀ የለም። ምንም የለም።”
ከተማዋ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ካገኘች 10 ዓመት እንዳለፋትም ይናገራል።
አክቲቪስቱ እና ፖለቲከኛው አለን ወደ አቡጃ ከማቅናቱ በፊት በግብርና ሥራ ነበር የሚተዳደረው። ነገር ግን ቦኮ ሐራም ያለውን ንብረት ሁሉ እንዳወደመበት ይገልጣል።
ሀሰን ዑስማን በቺቦክ ማዕከላዊ ገበያ የሕንፃ መሣሪያዎች ይሸጣል። ከተማዋ ባላት የፀጥታ ችግር ምክንያት ገበያው እንደቀዘቀዘ ይናገራል። ማንም ቤት ለመሥራትም ሆነ ቤቱን ለማደስ ፈቃደኛ አይደለም ይላል።
ምንም እንኳ የፀጥታው ጉዳይ ቀስ በቀስ እየተስተካከለ ቢሆንም በርካቶች ከታዳጊዎቹ አፈና በኋላ ከተማዋን ለቀው አንደወጡ ሀሰን ያወሳል።
በ2014 የቺቦክ ታዳጊ ሴቶች ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ በሌሎች 10 ጥቃቶች 1400 ተማሪዎች ታፍነው ተወስደዋል። ባለፈው መጋቢት በሁለት ጥቃቶች 300 ተማሪዎች መታፈናቸው የሚታወስ ነው።
መንግሥት በ2016 21 ተማሪዎችን ለማስለቀቅ ገንዘብ ከፍሏል የሚባለውን መረጃ ሐሰት ነው ቢልም 82 ተማሪዎችን ለማስለቀቅ በቁጥጥር ሥር የነበሩ የቦኮ ሐራም ታጣቂዎችን መለወጡን አምኗል።
አንዳንዶች ታፍነው የተወሰዱ ታዳጊዎችን ለማስለቀቅ ገንዘብ መክፈሉ ሁኔታውን አባብሶታል ብለው ያስባሉ።

በአቡጃ የሚገኙት የምክር ቤት አባሉ ሙሐመድ አሊ ንዱሜ መንግሥት ታግተው የሚገኙ ሴቶችን ለማስለቀቅ ጥረት እያደረገ ነው ይላሉ።
ይህ ፖለቲከኛ እንደሚሉት ከዚህ ቀደም መንግሥት በድርድር 100 ታዳጊ ሴቶችን ሲያስለቅቅ የከፈለው ከፍተኛ ገንዘብ ቀሪ ሴቶችን ለማስለቀቅ ትልቅ ፈተና ሆኗል ይላሉ።
“በቀደመው የመንግሥት አስተዳደር የተከፈለውን ገንዘብ አላውቅም። ነገር ግን ከዚያ በኋላ ሰውን አግቶ መውሰድ ገንዘብ እንደሚያስገኝ ማሳያ ሆነ” በማለት ይናገራሉ።
ይህ የምክር ቤት አባሉ መንግሥታ ታዳጊዎችን እንዲያስለቅቅ ጫና ይደረጋል ይላሉ።
ያልተመለሱት 87 ሴቶች ቤተሰቦች ተስፋቸው እየጨለመ ይመስላል። ኢስተር ግን በፍፁም ተስፋ አልቆርጥም ትላለች።
“ፈጣሪ ከሷ ጋር እንደሆነ አውቃለሁ። አንድ ቀን መልሼ እንደማያት ተስፋ አለኝ።”