April 14, 2024 – Konjit Sitotaw 

አውሮፓ ኅብረት፣ የኦነግ አመራር በቴ ኡርጌሳ በተፈጸመው ግድያ ላይ “ሙሉ ምርመራ” እንዲደረግ ትናንት ምሽት ባወጣው አጭር መግለጫ ጠይቋል። ኅብረቱ፣ ለኢትዮጵያ መጻዒ ብልጽግና እና ሰላማዊ መጻዒ ዕጣ ፋንታ፣ በባለድርሻ አካላት መካከል ንግግር እንዲደረግ እና ተጠያቂነት፣ ፍትህ እና ዕርቅ እንዲሠፍን ኹሉንም ጥረቶች ለማገዝ ዝግጁ እንደኾነ አስታውቋል።

ፈረንሳይ፣ በኦሮሚያ ክልል መቂ ከተማ ባለፈው ማክሰኞ ተገድለው በተገኙት የኦነግ አመራር በቴ ኡርጌሳ ግድያ ዙሪያ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቃለች። በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኢምባሲ ዛሬ ባወጣው አጭር መግለጫ፣ በበቴ ግድያ ላይ “አስቸኳይ”፣ “ገለልተኛ” እና “ሙሉ” ምርመራ እንዲደረግ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ አውሮፓ ኅብረት እና ሌሎች ዓለማቀፍ አጋሮች ያቀረቡትን ጥያቄ ፈረንሳይ እንደምትጋራው ገልጧል።

ፈረንሳይ፣ በተቃዋሚ ፖለቲከኛው ግድያ ዙሪያ “ፍትህ እና ተጠያቂነት” መስፈኑ አስፈላጊ መኾኑንም ገልጣለች። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ በበቴ ኢርጌሳ ግድያ እጁ እንደሌለበት ገልጦ፣ በግድያው ላይ የወንጀል ምርመራ መጀመሩንና ምርመራው ሲጠናቀቅ ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ከቀናት በፊት መግለጡ አይዘነጋም።