
ከ 5 ሰአት በፊት
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገንዘብ ዝውውር ሥርዓቱ ላይ እክል ማጋጠሙን ተከትሎ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ተወስዶበት ነበር። በዚህ የገንዘብ ዝውውር ውስጥ ደግሞ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ስምም በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል።
የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ የወሰዱ ደንበኞቹ ገንዘቡን እንዲመልሱ ባንኩ ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ ከተወሰደበት 800 ሚሊዮን ብር ውስጥ አብዛኛውን ለማስመለስ እንደቻለ ባንኩ ገልጿል።
ባለፉት ሳምንታት ደግሞ የወሰዱትን ብር ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑ ናቸው ያላቸውን ደንበኞቹን ስም እና ፎቶ የበይነ መረብ ገጽ ላይ እና በቅርንጫፎቹ አማካይነት ይፋ ሲያደርግ ቆይቷል።
ይህንንም ተከትሎ የወሰዱትን የተለያየ መጠን ያለውን ገንዘቡ ለተለያዩ ዓላማዎች ያዋሉ እና ወደ ሌሎች ባንኮች ያዘዋወሩ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ለመውጣት ካልቻሉበት አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንዳንዶች ለትምህርት ወደ ክፍል መግባት ከመቆም ጀምሮ ከዩኒቨርስቲያቸው የተሰወሩ እንዳሉ አንዳንዶች ሲናገሩ ሌሎች ደግሞ በዚህ ሁኔታ ወደ ቤተሰቦቻቸው የመመለሳቸው ነገር አሳስቧቸዋል።
‘ገንዘብ መሥራት’
ሰለሞን እና አሕመድ በተለያዩ የመንግሥት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተማሪ ናቸው። (ስማቸው እንዳይገለጽ ስለጠየቁ ስማቸው ተቀይሯል። ማንነታቸውን ጠቋሚ ነገሮችን አስቀርተናል።)
ሰለሞን እና አሕመድ አርብ ምሽት መጋቢት 6/2016 ዓ.ም በሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ነበር ካላቸው ገንዘብ በላይ ያለችግር ማዘዋወር እና ከመክፈያ ማሽኖች መውጣት እንደሚቻል የሰሙት።
የወሬው መነሻ ከሌላ ዩኒቨርሲቲ ከመጣ የስልክ ጥሪ ሳይሆን እንደማይቀር ሁለቱም ይገምታሉ። ለወትሮ በትምህርት እና በእግር ኳስ ውይይቶች የሚጠመዱት ተማሪዎች ወሬያቸው ሁሉ ስለ ብር ሆኖ ነበር ይላሉ።
የሰሙት ወሬ እውነት ነው አይደለም በሚል ‘ሞከሩ’፣ ሠራላቸው። “በኋላም በቀጥታ ወደ ‘ሥራ’ ገባን። ከጓደኞቻችን ጋር ብር መላላክ ጀመርን” ይላል ሰለሞን።
ከሰው ጋር የተላላከውን ጨምሮ ከሁለት መቶ እስከ ሦስት መቶ ሺህ የሚጠጋ ገንዘብ ‘ሠራሁ’ ይላል አሕመድ። [ተማሪዎቹ ሁኔታን ‘ሥራ’ በሚል ነው የገለጹት።]
ከገንዘብ ከመክፈያ ማሽኖች በቀን ማውጣት የሚቻለው ገንዘብ የተገደበ ነው። ተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉትን የተለያዩ የባንክ ገንዘብ ማሽኖች እየዞሩ ሲያዳርሷቸው አምሽተዋል።
“ተማሪ ሆኖ ኤቲኤም ካርድ ሌለው የለም። የሌለውም እየተቀባበለ ነው ሲያወጣ የነበረው” ብሏል አሕመድ።
ሰለሞን 15 ሺህ ብር ገደማም ከገንዘብ መክፈያ ማሽኖች አወጣ። ቀሪውን ደግሞ ወደ ሌላ ባንክ አዛወረ።
“በእኔ [አካውንት] ተሠርቶ ወደ ሌላኛው የእሱ [ጓደኛዬ አካወንት] ገባ” በዚህም ሰለሞን እና ጓደኛው ከአንድ መቶ ሺህ ብር በላይ በጋራ ወስደዋል።
ጓደኛው በካሽ ያወጣውን አስር ሺህ ብር ስልክ ገዛበት፣ ሰለሞን በካሽ ያወጣውን 15 ሺህ ብር ስላላጠፋው ወደ የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ድረስ ሄዶ መልሷል።
አሕመድም ገንዘቡን ከጓደኛው ጋር ነበር የወሰደው። ጓደኛው የንግድ ባንክ ሒሳብ ስለሌለው አሕመድ ‘እየሠራ’ ለጓደኛው ይልካል።
የተወሰነውንም በካሽ አውጥተዋል። በጥሬ ብር ካወጡት ውስጥ አብዛኛውን አጥፍተውታል። ያልገዙት ዕቃ ያልተመገቡት ምግብ አልነበረም። “ብሩ ዝም ብሎ ስለመጣ በማይሆን ነገር ነበር የጠፋው” ይላል አሕመድ።
- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ ያልመለሱ ደንበኞቹን ፎቶ በቅርንጫፎቹ በር ላይ ይፋ ማድረግ ጀመረ5 ሚያዚያ 2024
- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞቹን ማንነት ይፋ ማውጣቱ እና የሚነሱ ሕጋዊ ጥያቄዎች4 ሚያዚያ 2024
- ንግድ ባንክ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ያልመለሱ የ565 ደንበኞቹን ስም ይፋ አደረገ26 መጋቢት 2024
የታገደው ገንዘብ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መግለጫ ሲያወጣ ሁሉም ነገር ተቀየረ። ሰለሞን “በጣም ደንግጠን ነበር። ልንታሠር ነው ብለን ፈርተን ነበር። የፈተና ጊዜም ደርሶ ነበር። ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለን መማር አልቻልንም ነበር” ይላል።
እጃቸው ላይ የነበረውን ካሽም የመለሱት በመግለጫው ማግስት ነበር። እንደዚያም ሆኖ ግን ‘ሲስተም ላይ ብዙ ብር ቀርቷል’ ይላል።
ንግድ ባንክ አካውንታቸው ላይ የነበረውን ብር በሙሉ ወስዶታል። ወደ ሌላ ባንክ ያስተላለፉትን ገንዘብ መልሶ እንደሚወስድም እጃቸው ላይ የነበረውን ጥሬ ገንዘብ ሲመልሱ ከባንኩ ባልደረቦች ተነግሯቸው ነበር።
ንግድ ባንክ ወደ ሌሎች ባንኮች የተዘዋወረውን ገንዘብ ግን አላስመለሰም። ይህንን ነው ሰለሞን ‘ሲስተም ላይ ብዙ ብር ቀርቷል’ የሚለው።
በካሽ ያለውን የመለሰው ሰለሞን ቀሪውን ገንዘብ እንዳይመልስ ደግሞ የንግድ ባንክም ሆነ የሌሎች ባንኮች ሒሳቦቹ ታግግደዋል።
የባንኩን ‘ማስጠንቀቂያ’ በመስማት እነ አሕመድም እጃቸው ላይ ቀረውን ገንዘብ ተመላሽ አደረጉ። ዩኒቨርሲቲውም ከባንክ የወሰዳችሁትን መልሱ በሚል በባንኩ ማስጠንቀቂያ ላይ አከለበት።
“የግል ባንክ ላይ ያለውን [ገንዘብ] መመለስ አቅቷቸው ነው መሰለኝ ወደ ሌላ ባንክ የላክነው አሁንም ኔጋቲቭ ሆኖ ነው የተቀመጠው” የሚለው አሕመድ ስማቸው እና ፎቷቸው የወጣው በዚሁ ወደ ሌላ ባንክ በላኩት ገንዘብ መሆኑን ይናገራል።
ይህንን ሐሳብ ሰለሞንም ይጋራዋል። የሚቀርባቸውን ገንዘብ መመለስ ይችላሉ። ለዚህ የሚሆን በቂ ገንዘብም አላቸው። ገንዘቡ ግን በባንኮች ውስጥ እንዲታገድ ተደርጓል።
ስም እና ፎቶ ይፋ መሆኑ
ባንኩ ወደ ሌሎች ባንኮች የላኩትን ገንዘብ ሳይወስድ ስማቸውን እና ፎቷቸውን ይፋ ማድረገ ጀመረ። የሰለሞን ስም እና ፎቶም በበይነመረቦች ላይ ተሰራጩ።
በተወለደበት፣ ባደገበት እና አሁንም ወላጆቹ በሚኖሩበት ከተማ ነበር የባንክ አካውንቱን ያወጣው። በቀዬው ፎቶው አደባባይ ላይ ተሰቀለ።
አሕመድም ያጠፋውን ብር ከቤተሰብም ከሌላም ብሎ መመለስ ችሏል።
ንግድ ባንክ ላይ ያለው ገንዘብ ተመላሽ ተደርጓል። ወደ ሌላ የባንክ ሒሳብ የላከው ባለመመለሱ ግን ስሙ እና ፎቶ ይፋ ተደርጓል።
ከ70 እስከ 80 ሺህ ካልመለሱት ጋር ነው ፎቶው ይፋ የተደረገው።
ሰለሞን ፎቶው እንደሚለጠፍ የጠበቀው ዩኒቨርሲቲው ባለበት ቅርንጫፍ ነበር። ያላሰበው ሆኖ በትውልድ ቀዬው ሒሳቡን ባወጣበት ቅርንጫፍ መለጠፉን አይተው “ጓደኞቼ ደውለው እዚህ ፎቶህ ተለጥፏል አሉኝ” ብሏል።
ቢቢሲ ሰለሞንን እስካናገረበት ቀን ድረስ የሰለሞን እንጂ የጓደኛው ፎቶ ይፋ አልተደረገም። ፎቶውን አይተው ጓደኞቹ እና የሚያውቁት እየደወለሉት ነው።
ብሩን አለማጥፋቴን እየተናገርኩም “እንዴት ብሩን አጥፍተኽዋል ይሉኛል” ብሏል። በዚህ ምክንያትም ጭንቀት ውስጥ እንደገባውም ያስረዳል።
“ክፍል ውስጥ ትምህርቴን መከታተል አልቻልኩም። አንድ መምህር እንዲያውም መማር ካልቻልክ ውጣ እያለኝ ነበር” ብሏል።
አሕመድ በበኩሉ ፎቶው በበይነ መረብ መለቀቁን አውቋል። ሒሳቡን በከፈተበከት ቅርንጫፍ ግን ፎቶው እስካሁን አልተለጠፈም። እስካሁን በዩኒቨርሲቲያቸው በኩል ምንም የተባሉት ነገር የለም።
ገንዘቡ እያለ ማዘዋወር አለመቻል
እነሰለሞን ማንነታቸው ይፋ እንዳይሆን በአቅራቢያቸው የሚገኘውን ባንክ አናግረው ‘ጠብቁ’ የሚል ምላሽ ብቻ ነው የተሰጣቸው።
አሕመድ ደግሞ ሒሳቡን ባልጠቀምበት እንኳን ብር ማስተላለፍ እንድችል ተደርጎ ከግል ባንክ ወደ ንግድ ባንክ ገንዘቡን ማስተላለፍ ብቻ ይፈቀድልኝ ሲል ጠይቋል። ተበድረህም ቢሆን ገንዘቡን ክፈልና ሒሳብህ ሲለቀቅ መክፈል ትችላለህ የሚል ምላሽ አግኝቷል።
አሁን የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እና ጓደኞቹ እንዲሁም የተወሰኑት የቤተሰቡ አባላት ከንግድ ባንል ብር መውሰዱን አውቀዋል። ቀሪው ብር በሌላ የባንክ ሒሳብ መኖሩን ስለነገራቸው ቤተሰቦቹ ተረጋግተዋል።
አህመድ ፎቶው ከተለጠፈ በኋላ ‘አለብህ’ ተብሎ ከነበረው ብር ግማሹ ተቀንሶለታል። በግል ባንክ ከነበረው ብር ተቀንሶ ለንግድ ባንክ መተላለፉንም አውቋል። አሁን 30 ሺህ ብር ገደማ እንዳለበት አውቋል።
“ትንሽ ጭንቀት አለው። ለፈተናም ከባድ ነው። [ሒሳብ ከከፈትኩበት ቅርንጫፍ] ባንክም እየተደወለ ከአሁን በኋላ ወደ ሕግ አካል ነው የምንወስዳችሁ ይሉን ነበር” ብሏል። ይህ ነው የጭንቀቱም ምክንያት።
አሕመድ ሒሳቡን ማንቀሳቀስ ባይችልም ሒሳቡ ውስጥ ያለውን ገንዘብ መመለከት መቻሉ ዕዳው እጨመረ መሆኑን ለማወቅ ችሏል።
“ወለድም እየወለደ ነው መሰለኝ። በቆየ ቁጥር እየጨመረ ነው። 500 እና 400 ብር እየወለደ ነው። ብሩ እየጨመረ ነው። ያለኝን ብር ወስደው አንደኛውን ቢመልሱት ዕዳውም ይቆማል። ካልሆነ ግን ብሩ እየጨመረ ነው የሚሄደው” ብሏል።
አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት ተማሪዎች
ትምህርት ተጠናቆ ተማሪዎች ለእረፍት የሚመለሱበት ጊዜ እየተቃረበ ነው። ሰለሞን ግን ወደ ቤተሰቦቹ ዘንድ የሚመለስ አይመስልም።
“ብሄድ ፎቶዬ አደባባይ ላይ ነው። ከሥነ ልቦና አንጻር ጥሩ ነገር ሊሰማኝ አይችልም። ጓደኞቼም፣ ቤተሰቦቼም አሉ። ስሜ እና ፎቶዬ ተለጥፎ በየቀኑ ሳየው ጥሩ ነገር ስለማይሰማኝ መሄድ አልፈልግም” ብሏል።
አሕመድ ግን ይህ ጭንቀት የለበትም። አካውንቱን የከፈተበት እና የሚኖርበት የተለያየ ቦታ በመሆናቸው ወደ ቤተሰቦቹ እንደሚመስ ገልጿል። “እኔም ሒሳብ ወደ አወጣሁበት [አካባቢ] የምመለስ ቢሆን ይከብደኝ ነበር” ብሏል።
መጀመሪያ ላይ ያጠፋው ገንዘብ ከቤተሰብ እስኪሟላለት ጭንቀት ቢገባውም፤ አሁን በግል ባንክ ያለው ገንዘብ ቀሪውን ‘ዕዳ’ መከፈል ስለሚያስችለው ተረጋግቷል።
አሕመድን ከዚህ ይልቅ የሚያስፈራው ትምህርት ከጨረሰ በኋላ ሊኖረው ይችላል የሚለው ጫና ነው። ፎቶው እና ስሙ ይፋ መደረጉ ወደ ሥራ ዓለም እንዳይገባ እንቅፋት እንዳይሆንበት ከወዲሁ ስጋት ፈጥሮበታል።
ብሩን መመለሳችን ግዴታ ነው የሚለው ሰለሞን ደግሞ ፎቶ እና ስም መለጠፉ ግን በምን አግባብ ይሆን ሲል ይጠይቃል።
ባንኩ ወደ ሌሎች ባንኮች የተላለፉትን ገንዘቦች “በራሱ መልሶ በካሽ የወሰዳችሁትን አምጡ ቢል ጥሩ ነበር” ብሏል።
በርካታ ተማሪዎች በንግድ ባንክ ላይ ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያእዞ ሒሳባቸው በመታገዱ ብር ማግኘት ስላልቻሉ በጣም እየተቸገሩ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ሰለሞን ፎቶው ከተለጠፈ ቀናት አልፈውታል። ዩኒቨርሲቲው እስካሁን ምንም ያለው ነገርም የለም። ትውልድ ስፍራው ላይ ግን መነጋገሪያ ሆኗል።
ለዚህም ነው “ብሩን ከፍዬ ከዚህ ሁሉ ጫና ብገላገል ደስተኛ ነበርኩ” የሚለው።
ቢቢሲ ተማሪዎቹ ወደ ሌላ ባንክ ያስላስተላለፉትን ገንዘብ እንዴት ማስመለስ እንደሚችሉ እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማብራሪያ ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።