
ከ 2 ሰአት በፊት
ኢራን ለመጀመሪያ ጊዜ በእስራኤል ግዛት ላይ ጥቃት ፈጽማለች።
ቅዳሜ እኩለ ሌሊት ላይ የአየር ጥቃት ማንቂያ ድምጾች በእስራኤል ተሰሙ። ድምጹን ተከትሎ ነዋሪዎች መጠለያ እንዲፈልጉ መልዕክት ተላልፎላቸው ነበር።
በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎች የተቃጣው ጥቃት ሲከሽፍ ሌሊቱ በበርሃን ተሞልቶ ነበር።
በዚህ ሁሉ ውስጥ ቢያንስ ዘጠኝ አገራት ተሳትፈዋል። ከኢራን፣ ከኢራቅ፣ ከሶሪያ እና ከየመን ሚሳኤሎች ተተኩሰዋል። በእስራኤል፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ዮርዳኖስ ደግሞ ጥቃቱን በማክሸፍ ተሳርፈዋል።
ስለጥቃቱ እስካሁን የሚታወቁ ጉዳዮችን እንደሚከተለው አቅርበናል።
የሰው አልባ አውሮፕላኖች እና የሚሳኤሎች ጥቃት
ኢራን ከ300 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፏን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
ከ170 ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና 30 ክራይዝ ሚሳኤሎች አንዳቸውም ወደ እስራኤል ግዛት አልዘለቁም። ከ110 ባሊስቲክ ሚሳኤሎች ውስጥ ጥቂቶቹ ብቻ እስራኤል መድረሳቸውን የጦሩ ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ በቴሌቭዥን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ቢቢሲ እነዚህን አሃዞች አላረጋገጠም።
ከኢራን እስከ እስራኤል ያለው አጭር ርቀት አንድ ሺህ ኪሎሜትር ነው። ይህም ኢራቅ፣ ሶሪያ እና ዮርዳኖስን ማቋረጥን ያካትታል።
ጥቃቱ ከበርካታ አገራት ተከፍቷል
ቅዳሜ ምሽት የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ (አይአርጂሲ) ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ሚሳኤሎችን ማስወንጨፉን አስታውቋል።
የኢራቅ የፀጥታ ምንጮች ለሮይተርስ እንደተናገሩት በእስራኤል አቅጣጫ የሚምዘገዘጉ መሳሪያዎች በኢራቅ ሰማይ ላይ ሲበሩ ታይተዋል።
አብዮታዊ ዘቡ አክሎም ቀስ ብለው የሚንቀሳቀሱ ድሮኖች ከተላኩ ከአንድ ሰዓት በኋላ ባሊስቲክ ሚሳኤሎች ተወንጭፈዋል። ይህም ሁለቱም በተመሳሳይ ጊዜ እስራኤልን አንዲመቱ በማሰብ ነው።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ የአሜሪካ ጦር ከኢራን፣ ከኢራቅ፣ ከሶሪያ እና ከየመን የተተኮኮሱ ሚሳኤሎችን እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ማጨናገፉን አስታውቋል።
በኢራን የሚደገፈው እና በሊባኖስ የሚንሳቀሰው ሂዝቦላህ ሮኬቶችን በጎላን ወደሚገኙ የእስራኤል የጦር ካምፕ ማስወንጨፉን አስታውቋል። አካባቢው እስራኤል ከሶሪያ ነጥቃ ወደ ግዛቷ የከለለችው ቢሆንም በአብዛኛው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዕውቅና አላገኘም።
- እስራኤል “ትክክለኛው ሰዓት ላይ” ለኢራን ጥቃት የአጸፋ ምላሽ እሰጣለሁ አለችከ 4 ሰአት በፊት
- ከኢራን፣ ኢራቅ እና የመን ከ300 በላይ ሚሳኤል እና ድሮኖች ወደ እስራኤል መወንጨፋቸው ተነገረ14 ሚያዚያ 2024
- ፕሬዝዳንት ባይደን እስራኤል የኢራንን ጥቃት የመከተችው በአሜሪካ ድጋፍ ነው አሉ14 ሚያዚያ 2024

እስራኤል እና አጋሮቿ
በኢራን ከተሰነዘረው ጥቃት ውስጥ 99 በመቶ የሚሆነው ከእስራኤል አየር ክልል ውጪ ወይም እስራኤል እንደደረሰ እንዲጨናገፍ ሆኗል ሲሉ ሪር አድሚራል ሃጋሪ ተናግረዋል።
ይህም ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና የክሩዝ ሚሳኤሎች እንዲሁም የባለስቲክ ሚሳኤሎችን ይመለከታል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው በኢራን የተወነጨፉትን ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎች “ከሞላ ጎደል እንዲጨናገፍ በማድረግ” የአሜሪካ ጦር እስራኤልን ተከላክሏል ብለዋል።
አክለውም አሜሪካ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የተባለለት ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት አውሮፕላኖችን እና የጦር መርከቦችን ወደ አካባቢው ማሰማራቷን ተናግረዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) በበኩሉ የጦር ኃይሉ ከ80 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ቢያንስ 6 ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን አወድሟል።
ከእነዚህም መካከል በሁቲ ቁጥጥር ስር ባሉ የየመን አካባቢዎች ከመተኮሳቸው በፊት መሬት ላይ የወደሙ ባሊስቲክ ሚሳኤሎች እና ሰባት ሰው አልባ አውሮፕላኖች ይገኙበታል።
የአሜሪካ ጦር አካባቢዎቹ በግልጽ ይፋ ካልተደረጉባቸው የጦር ሰፈሮች በመነሳት በርካታ የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ዮርዳኖስ ድንበር አቅራቢያ ማክሸፋቸውን የደኅንነት ምንጮች ለሮይተርስ ተናግረዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በበኩላቸው የአገራቸው ታይፉን ጄቶች በርካታ የኢራን ጥቃቶችን ማክሸፋቸውን አረጋግጠዋል። ሱናክ አክለውም የኢራን ጥቃት “በጣም የማውግዘው አደገኛ እና አላስፈላጊ ማባባስ ነው” ብለዋል።
ዮርዳኖስ ከእስራኤል ጋር የሠላም ስምምነት ብትደርስም ቴል አቪቭ መቀመጫውን ጋዛ ባደረገው ሐማስ ላይ ጦርነቱን ያካሄደችበትን መንገድ በከፍተኛ ደረጃ ስትተች ቆይታለች።
የቅዳሜ ሌሊቱን ጥቃት ተከትሎ ዮርዳኖስ የዜጎቿን ደኅንነት ለማስጠበቅ ወደ አየር ክልሏ የገቡ የበረራ ቁሶችን ማክሸፏን የአገሪቱ ካቢኔ ገልጧል።
ፈረንሳይ የአየር ክልሉን ለመቆጣጠር ድጋፍ ያደረገች ቢሆንም ድሮኖች ወይም ሚሳኤሎች ስለማክሸፏ ግን ግልጽ አልነበረም ሲል የእስራኤል ጦር አስታወቋል።

ስንት ሚሳኤሎች ዒላማቸውን መቱ?
በኢየሩሳሌም የቢቢሲ ዘጋቢዎች የማስጠንቀቂያ ድምጽ መስማታቸውን እና የእስራኤል የአይረን ዶም የሚሳኤል መከላከያ ሥርዓት ሲሠራ ማየታቸውን ዘግበዋል።
ማክሸፊያ ሚሳይሎች የሚተኮሱት ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ ነው የሚወድቁት ተብለው በሚታሰቡ ሮኬቶች ላይ ብቻ ነው።
ከባለስቲክ ሚሳኤሎቹ መካከል ጥቂቶቹ በማለፍ የእስራኤልን ግዛት መምታታቸውን ሪር አድሚራል ሃጋሪ ተናግረዋል።
አንደኛው በደቡብ እስራኤል በኔጌቭ በረሃ የሚገኘውን የኔቫቲም የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ላይ “ቀላል ጉዳት” ቢያደርስም የጦር ሠፈሩ አሁንም በሥራ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ዜና እንደተናገሩት አምስት ባላስቲክ ሚሳኤሎች የአየር መከላከያውን ጥሰው በማለፍ በእስራኤል ግዛት ውስጥ ጉዳት አድርሰዋል።
አራት ሚሳዔሎች ያረፉት በጦር ሰፈሩ ላይ ነው። ይህ የጦር ሰፈር የአገሪቱ ኤፍ-35 ተዋጊ ጄቶች የሚገኙበት ሲሆን፣ የኢራን ቀዳሚ ዒላማ መሆኑንም ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።
አንዱ ሚሳዔል መንደርደሪያውን ሲመታ፣ ሌላው ባዶ አውሮፕላን ማቆሚያ ቦታ ላይ ወድቋል። ሌላኛው ደግሞ ከጥቅም ውጭ የሆነ የአውሮፕላን ማቆሚያን መምታቱን ተናግረዋል። አምስተኛው ባለስቲክ ሚሳዔል በሰሜናዊ እስራኤል የሚገኝ ራዳር ላይ ያነጣጠረ ቢመስልም ዒላማውን አልመታም።
ኢራን ከተተኮሰችው 120 የባሊስቲክ ሚሳኤሎች ግማሾቹ ማስወንጨፊያ ላይ ወይም ግማሽ መንገድ ወድቀዋል ሲሉ ከባለሥልጣናቱ አንዱ ለሲቢኤስ ተናግረዋል።
የኢራን የዜና ወኪል ኢርና እንዳስታወቀው ደግሞ ጥቃቱ በአየር ኃይሉ የጦር ሰፈር ላይ “ከባድ ጉዳት” አድርሷል።
ሪር አድሚራል ሃጋሪ እንደተናገሩት አንዲት የ10 ዓመቷ ህጻን በፍንጣሪ ክፉኛ ተጎድታለች። በደቡባዊ አራድ ከተማ አቅራቢያ ከሚገኝ የቤዱይን አረብ ማኅበረሰብ ነዋሪ የተገኘችው ልጅ፤ የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖች በከሸፉበት አካባቢ ከሰማይ በወደቀ ፍንጣሪ ጉዳት እንደደረሰባት ተነግሯል። ታዳጊዋ አሁን ከፍተኛ ክትትል እየተደረገላት ይገኛል።
ዮርዳኖስ በተመሳሳይ በግዛቷ አንዳንድ ፍንጣሪዎች ወድቀው “በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ምንም ዓይነት ከባድ ጉዳት አለማድረሳቸውን” አስታውቃለች።

በቀጣይስ ምን ሊፈጠር ይችላል?
የእስራኤሉ ቻናል 12 ቴሌቭዥን አገሪቱ ለጥቃቱ ትልቅ ምላሽ እንደምትሰጥ አንድ ስማቸው ያልተገለጸ የእስራኤል ባለሥልጣንን ጠቅሶ ዘግቧል።
እንደ ጎረቤት አገራት ሁሉ የእስራኤል የአየር ክልል የተከፈተ ቢሆንም፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንት ከኢራን ጋር ያለው ፍጥጫ “ገና አላበቃም” ብለዋል።
ኢራን በበኩሏ “እስራኤል በኢራን ላይ የአጸፋ እርምጃ ከወሰደች በምላሹ የምትወስደው እርምጃ ከአሁኑ የበለጠ የከፋ ይሆናል” ሲሉ የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ባገሪ እስራኤልን አስጠንቅቀዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ በማንኛውም የእስራኤል የአጸፋ ምላሽ ውስጥ ከተሳተፈች የዋሽንግተን የጦር ሰፈሮችም ጥቃት እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል።
የአብዮታዊው ዘብ አዛዥ ሆኑት ሆሴን ሳላሚም የአገራቸው ጥቅም፣ ባለሥልጣናት ወይም ዜጎቿ ላይ ለሚሰነዘር የእስራኤል ጥቃት ቴህራን የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በእስራኤል ጥያቄ መሠረት በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር ይሰበሰባል ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በኢራን “አስፈሪ” ጥቃት ዙሪያ “የተባበረ ዲፕሎማሲያዊ ምላሽ” ለመስጠት የቡድን ሰባት የበለፀጉ አገራት መሪዎችን እሑድ ዕለት አናግረዋል።