” ክፍፍል እና ፅንፈኝነት ካልተገታ በማናቸውም ቦታ ወደ ዘር ማጥፋት ሊያመራ ይችላል ” – ፖል ካጋሜ
ከ30 ዓመታት በፊት በሩዋንዳ በ100 ቀናት ብቻ እስከ 1,000,000 ሚደርሱ ሰዎች የተጨፈጨፉበት የሩዋንዳ ዘር ፍጅት እየታሰበ ይገኛል።
የዘር ፍጅቱ የተፈፀመበትን 100 ቀናት ታሳቢ በማድረግ ከሚያዚያ 7 (እ.ኤ.አ) አንስቶ ለ100 ቀናት የዘር ጭፍጨፋው ሰለባዎች ይታሰባሉ ፤ ይህም ኪውቡካ /Kwibuka/ ይባለል።
ከሳምንት በፊት በኪጋሊ በነበረ ስነስርዓት ላይ ፕሬዜዳንት ፖል ካጋሜ ፤ ከዘር ፍጅቱ በህይወት የተረፉ ዜጎች ለብሄራዊ አንድነት ሲሉ ስላደረጉት ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።
” እጅግ የሚከብደውን የእርቀ ሰላም ሸክም እናተ እንድትሸከሙ ጠየቅናችሁ እንሆ ለሀገራችን ስትሉ ይሄንን በየቀኑ ማድረጋችሁን ቀጥላችኃል ስለዚህ እናመሰግናችኃለን ” ነው ያሉት።
ፖል ካጋሜ ፥ አሁንም ድረስ በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት የጎሳ ፖለቲካ እየተባባሰ መሄዱን እና የብሄረሰብ ማጽዳት አደጋ መደቀኑን በማንሳት አስጠንቅቀዋል።
” ሩዋንዳ ውስጥ የደረሰው መከራ ማስጠንቀቂያ ሊሆን ይገባል። ክፍፍል እና ፅንፈኝነት ካልተገታ በማናቸውም ቦታ ወደ ዘር ማጥፋት ሊያመራ ይችላል ” ብለዋል።
ሩዋንዳ መከራ ውስጥ በገባችበት ጊዜ በርካታ ሀገራት የሰላም አስከባሪ ልጆቻቸውን ሩዋንዳ መላካቸውን እና እነዛም ወታደሮች ለሩዋንዳ እንደደረሱላት ገልጸዋል።
” ነገር ግን በጥላቻም ይሁን በፍራቻ ያልደረሰልን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ነው ” ሲሉ ተናግረዋል።
በሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ በወቅቱ በነበረው የሁቱ መንግሥት መሪነትና የሁቱ ብሄረሰብ አባላት በሆኑ ጽንፈኛ አክራሪዎች እንዲሁም በመንግሥት በሚደገፈው የ ” ኢንተርሀምዌ ‘ ሚሊሻ አማካኝነት እስከ 1,000,000 ቱትሲዎች ፣ ለዘብተኛ ሁቱዎችና ትዋዎች ተጨፍጭፈዋል።