
ከ 8 ሰአት በፊት
ጆ ባይደን እና ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካን ለሚቀጥለው አራት ዓመታት ማን ይመራታል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በሚመጣው ዓመት ኅዳር ይፋጠጣሉ።
በአሜሪካዊ ዘመናዊ ፖለቲካ ለየት ያለ በተባለው ምርጫ ሁለቱ ዕድሜ ጠገብ ፖለቲከኞች ድጋሚ መንበር ለመያዝ ይፋለማሉ።
በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ቀለል ያለ ነው የሚሉት በትራምፕ የሥልጣን ዘመን ፕሬስ ሴክሬታሪ ሆነው ያገለገሉት ሾን ስፓይሰር ናቸው።
ትራምፕ ዘመቻቸውን ወደ ኋላ ሊጎትትባቸው የሚችለው ጉዳይ እየቀረበባቸው ያለው ክስ ነው። አልፎም የሚያሰሟቸው አወዛጋቢ ንግግሮች እና ያለፈውን ምርጫ ውጤት ለመቀበል ማመንታታቸው እንደ ድክመት ይነሳባቸዋል።
ባይደንም ቢሆኑ ከድክመት ነፃ አይደሉም። በተለይ ደግሞ ከምርጫው በፊት የሚደረገውን ዘመቻ አቅማቸው ችሎ ያደርጉታል ወይ? ቢመረጡስ አገሪቱን መምራት ይችላሉ? የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ አላገኙም።
ጆ ተቀናቃኛቸውን ለከት የሌላቸው፣ ለአሜሪካ ስጋት የሆኑ እንዲሁም ዲሞክራሲን ስጋት ላይ የሚጥሉ ናቸው ሲሉ ይወቅሷቸዋል።
ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች የሚያደርጉትን ፉክክር ለማየት ብዙዎች የጓጓ አይመስሉም። ነገር ግን አሜሪካውያን መራጮች ከሁለቱ ግለሰቦች ውጭ ምርጫ የላቸውም።
እነሆ ምርጫውን ማን ሊያሸንፈው እንደሚችል የሚወስኑ አራት ወሳኝ ነጥቦች።
ወሳኝ ግዛቶች
ባይደን በአሜሪካውያን ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እየቀነሰ እንደመጣ ቁጥሮች እያሳዩ ነው። ሥልጣን ላይ ያለ ለሁተለኛ ዙር የሚፎካከር ፖለቲከኛ ተቀባይነቱ እንዲህ መላሸቁ አዳጋች ነው። ትራምፕም ቢሆኑ በአሜሪካውያን ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ይህን ነው የሚባል አይደለም።
ይህ የሚጠቁመው በሚመጣው ኅዳር የሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፉክክር የሚበዛበት እንደሚሆን ነው። የተሰበሰቡ ድምፆች የሚያሳዩት ሁለቱ ተፎካካሪዎች ያላቸው ተቀባይነት በጣም ተቀራራቢ አንዳንዴ ደግሞ ትራምፕ በአነስተኛ ነጥብ እየመሩ እንደሆነ ነው።
ይህ ቁጥር እምብዛም ለምርጫው ውጤት አስፈላጊ አይደለም። የአሜሪካ ምርጫ ውጤት የሚወሰነው በጥቂት ግዛቶች በሚገኝ ድምፅ ነው።
ለዚህ ምክንያቱ ኢሌክቶራል ኮሌጅ የተባለው የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት ነው። ይህ ማለት አሜሪካ ፕሬዝዳንቷን የምትመርጠው ዕጩዎች በሚያሸንፉት ግዛት መሠረት ነው። አብዛኛዎቹ ግዛቶች ዲሞክራት አሊያም ሪፐብሊካን ናቸው።
ዘንድሮ በጣም ወሳኝ የሚባሉት ግዛቶች ዊስከንሲን፣ ፔንስሊቬኒያ እና ሚሸጋን ናቸው። ባለፈው ምርጫ ባይደን ያሸነፉባቸው አሪዞና እና ጆርጂያ የተባሉት ግዛቶችም ወሳኝ ናቸው።
ኔቫዳ ግዛትም እንዲሁ ለሁለቱም ያላደላች ብትሆንም የሕዝብ ብዛቷ አነስተኛ መሆኑ አስፈላጊነቷን ዝቅ ያደርገዋል።
ፍሎሪዳ እና ኖርዝ ካሮላይና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደ ሪፐብሊካን ፓርቲ አድልተዋል። ቨርጂኒያ እና ኮሎራዶ ደግሞ ወደ ዲሞክራቲክ ፓርቲ አዘንብለዋል።
ከሕዝብ የተሰበሰቡ ድምፆች በእነዚህ ግዛቶች ትራምፕ እየመሩ መሆናቸውን ያሳያሉ። ይህ ለዲሞክራቶች አንቂ ድምፅ ነው። ነገር ግን በሁለቱ ፕሬዝዳንቶች መካከል ያለው ልዩነት አሁንም ጠባብ ነው።
- ትራምፕ፤ ፕሬዝደንት ባይደን እጅና እግራቸው ተጠፍሮ የሚታዩበት ፎቶ መለጠፋቸውን ተከትሎ ወቀሳ ደረሰባቸው31 መጋቢት 2024
- ባይደን እና ትራምፕ በሚቀጥለው ምርጫ ለመፋጠጥ የሚበቃቸውን ድምፅ አገኙ13 መጋቢት 2024
- ትራምፕ በማጭበርበር ክስ 354 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ተወሰነ17 የካቲት 2024
ምጣኔ ሀብት
አሜሪካውያን መራጮች ድምፃቸውን የሚሰጡት ኪሳቸውን አይተው ነው። ምጣኔ ሀብቱ መልካም ከሆነ ለተቀማጭ ፕሬዝዳንት፤ ካልሆነ ደግሞ ለተቀናቃኝ ዕጩ ድምፃቸውን ይሰጣሉ።
የ2024 የአሜሪካ ምርጫን ለመገመት አዳጋች ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ምጣኔ ሀብቱ አዎንታዊ መሆኑ ነው። ምጣኔ ሀብቱ በተረጋጋ መልኩ እያደገ ነው።
የሥር አጥነት ደረጃው እጅግ ዝቅተኛው ሊሆን ተቃርቧል። የአክሲዮን ገበያው ደግሞ እያሻቀበ ይገኛል። ቢሆንም አሜሪካውያን መራጮች በምጣኔ ሀብቱ ዙሪያ ያላቸው ምልከታ አሁንም የተምታታ ነው።
ይህ ሊሆን የቻለበት አንደኛው ምክንያት በተከታታይ ዓመታት የነበረው የዋጋ ግሽበት እና አሁንም በበርካታ የአሜሪካ ግዛቶች የመኖሪያ ቤት ዋጋ አለመቀነሱ እንደሆነ ይገመታል።
በአሜሪካ አሁን ያለው የመኖሪያ ቤት ሽያጭ ባለፉት 30 ዓመታት ከተመዘገበው እጅግ አነስተኛው ነው።
ትራምፕ በአዮዋ ግዛት ውስጥ ባዘጋጁት ፓርቲ ላይ ሁሉት ስክሪኖች ተሰቅለው ይታያሉ። እኒህ ስክሪኖች በባይደን ዘመነ መንግሥት ገንዘብ ተበድረው ቤት የገዙ ሰዎች ወለድ ስለተጨመረባቸው ነው ክፍያቸው የጨመረው የሚል መልዕክት ይዘዋል።
ነገር ግን ምጣኔ ሀብቱን በተለመከተ ባይደን የሚጽናኑበት መረጃ እየወጣ ይገኛል። የሚሺጋን ዩኒቨርሲቲ የሠራው ጥናት እንደሚያሳየው የዋጋ ንረት እና የነዳጅ ዋጋ እየቀነሱ መጥተዋል። የአሜሪካ መራጮች ስለምጣኔ ሀብት ያላቸውን አመለካከት ለመቀየር ገና ጊዜ አላቸው።
ትራምፕ እርሳቸው ሥልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን የነበረው ምጣኔ ሀብት የተሻለ ነው ብለው ይከራከራሉ።
ባይደን ደግሞ በበኩላቸው በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ኢኮኖሚያቸው ከተዳከሙ ሀገራት መካከል አሜሪካ ናት ማንሰራራት የቻለችው የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ።

ፅንስ ማቋጥ ወይስ ሕገ-ወጥ ስደተኞች?
የባይደን የምርጫ ዘመቻ ቡድን በአብዛኞቹ የአሜሪካ ግዛቶች ፅንስ ማቋረጥ ሕጋዊ እንዳይሆን ያደረጉት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ናቸው ይላል።
ትራምፕ የመረጧቸው ሦስት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ለ50 ዓመታት የቆየውን ለፅንስ ማቋረጥ የተሰጠውን ሕገ-መንግሥታዊ ጥበቃ አንስተዋል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ዲሞክራቶች የፅንስ ማቋረጥን ጉዳይ በማንሳት ድጋፍ ሲያገኙ ይስተዋላል።
በሚመጣው ኅዳር በሚደረገው ምርጫ በፍሎሪዳ እና አሪዞና ግዛቶች መራጮች በፅንስ ማቋረጥ ላይ ሕዝበ ውሳኔ ያደርጋሉ። ምክትል ፕሬዝዳንት ካማለ ሐሪስ እያደረጉ ባሉት የምርጫ ቅስቀሳ ላይ የሴቶች መብት ጉዳይን አጥብቀው ይዘዋል።
የፅንስ ማቋረጥ ጉዳይ ብዙዎች ካሰቡት በላይ እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል። ብዙውን ጊዜ ምርጫ ሲደርግበት ፅንስ ማቋረጥ የግለሰብ ምርጫ መሆን አለበት የሚለው ድምፅ ብልጫ ሲያገኝ ይታያል።
ዲሞክራቶች ፅንስ ማቋረጥን በተመለከተ ያላቸውን አቋም ድጋፍ ለመሰብሰብ ሲጠቀሙበት፤ የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ደግሞ የሕገ-ወጥ ስደተኞችን ጉዳይ አጥብቆ ይዞታል።
ባለፈው ታኅሣሥ በሜክሲኮ ድንበር በኩል ወደ አሜሪካ ለመግባት ሲሞክሩ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 249 ሺህ 785 ነበር። በድንበር በኩል ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ከምንጊዜውም በላይ ከፍ ብሎ የታየበት ወር ነበር። ነገር ግን በተለይ በቅርብ ወራት ይህ ቁጥር ዝቅ ያለ ይመስላል።
በርካት ያሉ ወረቀት የሌላቸው እና ጥገኝነት የሚጠይቁ ሰዎች ጉዳይ መንግሥት እና የአሜሪካ ዜጎችን ያሳሰባቸው ይመስላል።
ከሕዝብ የተሰበሰቡ ድምፆች እንደሚያሳዩት የትራምፕ ደጋፊዎች የስደተኞችን ጉዳይ ቁጥር አንድ መነጋገሪያ አድርገው ይዘውታል። በዲሞክራቶች መካከል ደግሞ ይህ ርዕስ ከፋፋይ ሆኖ ታይቷል።
የአሜሪካ ኮንግረስ ድንበር አቋርጠው የሚገቡ ስደተኞችን በተለመከተ ያደረገው ውይይት ያለውጤት ተጠናቋል።
“የባይደን አስተዳደር ድንበራችንን በማስጠበቅ ዙሪያ በተለይ ደግሞ በደቡባዊው ክፍል ባለው ጉዳይ ያለውን ክርክር ተሸንፏል” ይላሉ ሾን ስፓይሰር።
ሌሎችም እንደ የወንጀል መስፋፋት፣ የከባቢ አየር ጉዳይ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲም ምርጫውን ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል ሊወስኑ የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው።
በተለይ በጋዛ ያለው ጦርነት ለባይደን አስተዳደር የራስ ምታት ነው። አስተዳደሩ ለእስራኤል ያለውን ድጋፍ መግለጹ አንዳንድ ዲሞክራት ወጣት መራጮችን አስቆጥቷል።

የአደባባይ ምስጢሮች
ምርጫው እስከሚካሄድበት ወርሃ ኅዳር ድረስ ያለው ጊዜ ብዙ የማይጠበቁ ጉዳዮች ሊከሰቱ የሚችሉበት ነው።
ባይደን ዕድሜያቸው 81 ነው። ትራምፕ ደግሞ 77። እስከ ምርጫው ባለው ጊዜ ጤናቸው ላይ አንዳች ዓይነት እክል ቢገጥም መነጋገሪያ ከመሆን አያመልጥም።
በተለይ ደግሞ ሁለቱ ዕጩዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው የሚያደርጉት ክርክር በጉጉት ይጠበቃል።
ባይደን ዕድሜያቸው እንደገፋ እሙን ነው የሚሉት ተንታኞች፣ ትራምፕስ ምን ያህል ጉልበት ይቀራቸዋል የሚለውን ጥያቄ ከማንሳት ወደኋላ አይሉም።
በሁለቱ ዕጩዎች ደስተኛ ያልሆኑ መራጮች ሦስተኛ ፓርቲ አሊያም ራሱን የቻለ ዕጩ ብቅ አንዲል ይፈልጋሉ።
ፀረ-ክትባት አቋም በማራመድ የሚታወቁት ሮበርት ኬኔዲ ጁኒዬር በብሔራዊ ድምፅ ስብሰባው ከ10 በመቶ በላይ ድምፅ አላቸው። ነገር ግን የሁለቱን ንዑስ ፓርቲዎች ዕጩዎችን የሚፎካከር አቅም አላቸው የሚለው እርግጥ አይደለም።
ግራ ዘመሙ ምሑር ኮርኔል ዌስትም እንዲሁ ራሳቸውን ችለው እየተፎካከሩ ነው። ሊበርታሪያን እና ግሪን ፓርቲም የራሳቸውን ዕጩዎች ያሰልፋሉ።
ትራምፕ በ91 ክሶች በአራት ችሎቶች ይፈለጋሉ። ይህ ትልቁ ራስ ምታታቸው ነው። ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙም በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ሊቀንስ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
በአውሮፓውያኑ ጥር 2021 የትራምፕ ደጋፊዎች ካፒቶል የተሰኘውን የመንግሥት መቀመጫ ሰብረው መግባታቸው በአሜሪካ ፖለቲካ ላይ ጥሎ ያለፈው ጠባሳ አለ።
ምንም እንኳ ሪፐብሊካን መራጮች ይህን ጉዳይ ረስተው ወደፊት መጓዝ ቢፈልጉም፣ ዲሞክራቶች ግን ይህን አይፈቅዱም።
ምናልባት ራሳቸውን ከዕጩው ሐሳብ እንጂ ከፓርቲ ጋር የማያይዙ ሰዎች የሚመጣውን ምርጫ የመወሰን ኃይል ሊኖራቸው ይችላል።