የእስራኤል ጦር ካቢኔ

ከ 3 ሰአት በፊት

የእስራኤል ጦር ካቢኔ ለኢራን ያልተጠበቀ የሰው አልባ (ድሮን) እና ሚሳኤል ጥቃት ምላሽ ለመስጠት በመከረበት ስብሰባው ወጥ ውሳኔ ላይ መድረስ ሳይችል ቀረ።

በ24 ሰዓታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተሰበሰው የጦር ካቢኔ ለጥቃቱ አጸፋዊ ምላሽ እንዴት እና መቼ ይስጥ በሚለው ላይ መከፋፈሉም ተዘግቧል።

እስራኤል የጥቃቱን ምላሽ በተመለከተ ውሳኔ ላይ መድረሷን ለህዝብ ይፋ አላደረገችም።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የእስራኤል መንግሥት ሙሉ ጦርነት ሳይቀሰቀስ ኢራንን የሚጎዳ ጥቃት ማካሄድ ይፈልጋል።

ይህንንም ጥቃት የእስራኤል ሚኒስትሮች ከአሜሪካ ጋር በመቀናጀት መፈጸም እንደሚፈልጉም ተዘግቧል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት አገራቸው በኢራን ላይ በሚወሰድ ወታደራዊ እርምጃ አሜሪካ ተሳታፊ እንደማትሆንም ከወዲሁ ግልጽ አድርገዋል።

የእስራኤል አጋሮች የኢራንን ድርጊት አጥብቀው ቢያወግዙም የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር አጸፋዊ ምላሹ ላይ እንዲጠነቀቅ አሳስበዋል።

ኢራን ያደረገችው ጥቃት መጠናቀቁን ብትጠቁምም የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል ኃላፊ ጥቃቱ ምላሽ ሳያገኝ እንደማይቀር አጽንኦት ሰጥተዋል።

“ቀጣይ እርምጃዎችን እንመዝናለን። ነገር ግን በእስራኤል ግዛት ለተወነጨፉ ሚሳኤሎች፣ የክሩዝ ሚሳኤሎች ምላሽ ሳንሰጥ አንቀርም” ሲሉ ሌተናል ጄነራል ሄርዚ ሃሌቪ ተናግረዋል።

ነገር ግን አገራቸው የምትወስደውን እርምጃ በተመለከተም ምይአይነት ወይም መቼ ሊሆን እንደሚችል የተናገሩት ጉዳይ የለም።

የቀድሞ የሲአይኤ ኃላፊ ዴቪድ ፔትራየስ ለቢቢሲ እንደገለጹት እስራኤል በኢራን ላይ በምትወስደው አጸፋዊ የበቀል እርምጃ አሜሪካ የአለም ኢኮኖሚ ደህንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ አትፈልግም ብለዋል።

በኢራቅ እና አፍጋኒስታን የሚገኘው አለም አቀፍ ኃይል አዛዥ የነበሩት ጄነራል ፔትራየስ በበኩላቸው የኢራን ጥቃት“ከፍተኛ ጉዳይ” እንደሆነ ገልጸው ይህ ለእስራኤል ያለውንም አንድምታ ምዕራባውን መረዳት አለባቸው ብለዋል።

ጡረተኛው ጄኔራል በእስራኤል መንግሥት ውስጥ ያለው ክርክር “ሁኔታው የበለጠ እንዳይጋጋል “ እድል ሳይሰጥ የእስራኤልን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ምላሽ እንዴት ትስጥ የሚለው ነው ብለዋል።

ጄኔራሉ በአሁኑ ወቅት የሚገኙበት በደቡባዊ እስራኤል የሚገኘው የኔቫቲቭ የጦር ሰፈር ሲሆን ኢራን ቅዳሜ ዕለት በፈጸመችው ጥቃት ጉዳት ቢደርስበትም እስራኤል “አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ” አስታውቃለች።

ኢራን የፈጸመችው ጥቃት በሶሪያ ቆንስላዋ ውስጥ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ለገደለቻቸው ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦቿ አጸፋዊ ምላሽ ነው ትላለች።

የእስራኤል ጦር ከ300 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) እና ሚሳኤሎች ከኢራን ተወንጭፈዋል ብሏል። ኢላማቸውን ከማሳካታቸው በፊትም በአሜሪካ፣ ዩናይድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ እና ሌሎች አገራት ኃይሎች ድጋፍ ከሽፈዋልም ተብሏል። ምንም አይነት ሞት ያልተዘገበ ሲሆን እስራኤል የደረሰባት ጉዳት ውስን መሆኑን ተናግራለች።