
ከ 3 ሰአት በፊት
ታዋቂው አቡነ ማር ማሪ ኢማኑዔል ሲድኒ ከሚገኝ ቤተ-ክርስቲያን በቀጥታ ሥርጭት የሚተላለፍ ትምህርት እየሰጡ ሳለ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል።
አቡነ ማር ማሪ ኢማኑዔል የአሲሪያን ኦርቶዶክስ ክራይስት ዘ ጉድ ሼፐርድ የተባለው ቤተ-ክርስቲያን ወግ አጥባቂ መሪ ናቸው።
በአቡኑ ላይ ጥቃት ያደረሰው ታዳጊ በምዕመናን ቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ለፖሊስ ተላልፎ ተሰጥቷል።
የሲድኒ ፖሊስ አቡነ ማር ማሪ ኢማኑዔል እና አባ ኢሳክ የተበሉ ቄስ ጥቃት ቢደርስባቸውም “ሕይወታችን አደጋ ላይ የሚጥል አይደለም” ብሏል።
የ53 ዓመቱ አቡነ ማር ማሪ ኢማኑዔል ጭንቅላታቸው ላይ በስለት እንደተወጉ የተገለጠ ሲሆን፣ የኤንኤስደብሊው ፖሊስ ኮሚሽነር አቡኑ ቀዶ ህክምና እንደተደረገላቸው ገልጠው “በሕይወት በመትረፋቸው ዕድለኛ ናቸው” ብለዋል።
ግርማ ሞገስ ያላቸው እና አነጋጋሪ ስብከት በማሰማት የሚታወቁ ናቸው የሚባሉት አቡነ ማር ማሪ ኢማኑዔል በተለይ በአውሮፓ 2020 የኮቪድ-19 ሕግጋትን በመቃወም ነው ታዋቂነትን ያተረፉት።
ቤተ-ክርስቲያኗ አባ ማር ማሪ የሚያደርጉትን ትምህርት በማኅበራዊ ሚድያ አማካይነት በቀጥታ ታስተላልፋለች።
- በአውስትራሊያ አቡነ ማር ማሪ ኢማኑዔል ላይ የደረሰው ጥቃት “የሽብር ድርጊት” ነው ተባለከ 7 ሰአት በፊት
- ታዋቂው አቡነ ማር ማሪ ኢማኑዔል በቀጥታ የሚተላለፍ ትምህርት እየሰጡ ሳሉ በስለት ተወጉ15 ሚያዚያ 2024
- በአዲስ አበባ የተገደሉ ‘የፋኖ አባላት’ አስከሬን ይሰጠን ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱን ወላጆቻቸው ተናገሩከ 5 ሰአት በፊት
ከባግዳድ አውስትራሊያ
አቡነ ማር ማሪ ያደጉት በኢራቅ ዋና ከተማ ባግዳድ ሲሆን፣ በልጅነታቸው ነው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ አውስትራሊያ ያቀኑት።
ክራይስት ዘ ጉድ ሼፐርድ ቤተ-ክርስቲያን ድረ-ገፅ እንደሚጠቁመው አባ ማር ማሪ ኢማኑዔል በአውሮፓውያኑ 2009 ቄስ፤ ቀጥሎ ደግሞ በ2011 አቡን ሆነው ተቀብተዋል።
በ2014 ክራይስት ዘ ጉድ ሼፐርድ የተሰኘችው ቤተ-ክርስቲያን ከዋና የአሲሪያን ቸርች ኦፍ ዘ ኢስት ተገነጠለች። ይህ የሆነው በሃይማኖት አስተምሮ ምክንያት አቡኑ እንዲታገዱ ከተደረጉ በኋላ ነው።
የአቡነ ማር ማሪ ቤተ-ክርስቲያን የፌስቡክ እና የዩቲዩብ ገፅ በድምሩ 240 ሺህ ተከታዮች አሉት። ቤተ-ክርስቲያኗ የአባ ማር ማሪን አስተምህሮ በእነዚህ ገፆች ነው በቀጥታ የምታስተላልፈው።
አቡነ ማር ማሪ ኢማኑዔል የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን “በፈጣሪ ዐይን ይህ የወንጀል ድርጊት ነው” ሲሉ ያወግዛሉ። እንደ እስልምና እና አይሁድ ያሉ እምነቶችን በመንቀፍ አወዛጋቢ ንግግር አሰምተው ያውቃሉ።
ስለአሜሪካ እና ሩሲያ ፖለቲካ፣ ስለተባበሩት መንግሥታት እንዲሁም ፆታቸውን ስለሚቀይሩ ሰዎች ያላቸውን ምልከታ በግልፅ በመናገር ይታወቃሉ።
አቡኑ ፆታቸውን የቀየሩ ሰዎችን እንደ ሰው ልጅ እንደማይቆጥሯቸው፣ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የተቋቋመው በሰይጣን ነው ሲሉ የተናገሯቸው ንግግሮች አከራካሪ ነበሩ።
አቡኑ በቅርቡ በጋዛ ስላለው ጦርነት ትምህርት የሰጡ ሲሆን፣ በፍልስጤም ሰላም እንዲወርድ ጥሪ ሲያቀርቡ ተሰምተዋል።
ስለተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት፣ ሃይማኖት እና ኮቪድ በተደጋጋሚ በሚሰጧቸው ትምህርቶች እና ቃለ-መጠይቆች ምክንያት በተለይ በማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ዘንድ እውቅናን አፍርተዋል።
በእሳቸው ስም የተከፈተ አንድ የፌስቡክ ገፅ 294 ሺህ ተከታዮች አሉት። አቡነ ማር ማሪ ኢማኑዔል በሌሎች ቤተ-ክርስቲያናትም እየተገኙ ትምህርት ይሰጣሉ።
የቤተ-ክርስቲያኗ ድረ-ገፅ እንደሚጠቁመው ባለፈው ታኅሣሥ ወደ አሜሪካ ፊኒክስ አሪዞና አቅንተው ስለመፅሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሰጥተው ተመልሰዋል።
አሲሪያን ኦርቶዶክስ
አሲሪያን ቸርች ኦፍ ዘ ኢስት የተሰኘው ቤተ-ክርስቲያን ለየት ያለ የክርስትና እምነት የምትከተል ናት።
ነገር ግን ከሌሎች የኢስተርን ክርስቲያን አብያተ-ክርስቲያናት ጋር የሚያመሳስሉት ደግሞ ሌሎች ብዙ አስተምህሮቶች አሉት።
አሲሪያን ቸርች ኦፍ ዘ ኢስት በተለይ ከግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን እና ከካቶሊክ እምነት ጋር የሚመሳሉ ትምህርቶች ትሰጣለች።
አቡነ ማር ማሪ ኢማኑዔል የሚያስተምሩበት ክራይስት ዘ ጉድ ሼፐርድ ቤተ-ክርስቲያን አማኞች አብዛኞቹ ሊቨርፑል እና ፌርፊልድ በተባሉ የአውስትራሊያ አካባቢዎች የሚኖሩ ናቸው።
የአባ ማር ማሪ ቤተ-ክርስቲያን እየሱስ ክርስቶስ ላይ ተመሥርቶ አስተምህሮት የሚሰጥ ሲሆን፣ ራሷን ከአሲሪያን ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ጋር ታያይዛለች።
አሲሪያኖች በኢራቅ፣ በሶሪያ፣ በኢራን እና በቱርክ የሚገኙ ቁጥራቸው አናሳ የሆነ የክርስትና እምነት ተከታይ ማኅበረሰብ ናቸው።
የአቡኑ ቤተ-ክርስቲያ በእንግሊዝኛ እና አሲሪያን ቋንቋ ዋኬሌ ከሚገኘው ቤተ-ክርስቲያ የሃይማኖት ትምህርት ይሰጣል። ሰንበት ሰንበት ደግሞ ለህፃናት እና ታዳጊዎች የሚሆን ትምህርት ይተላለፋል።

ስለጥቃቱ የምናውቀው
ቤተ-ክርስቲያኗ ሁሌም ሰኞ ምሽት 1፡00 እና አርብ አመሻሹን 6፡00 በአቡነ ማር ማሪ ኢማኑዔል አማካይነት ትምህርት እንደምትሰጥ ድረ-ገፁ ይጠቁማል።
ሰኞ አመሻሹን 1፡00 አካባቢ አቡኑ ትምህርት እየሰጡ ሳለ ነው አንድ ወጣት ወደ አትሮነሳቸው ተጠግቶ በስለት ጥቃት ሲሰነዝርባቸው የታየው።
የአውስትራሊያ ፖሊስ ሰኞ ምሽት ሲድኒ በሚገኘው ቤተ-ክርስቲያን ላይ የደረሰው ጥቃት ሃይማኖታዊ “የሽብር ድርጊት” ነው ብሏል።
በአሲሪያን ዘ ጉድ ሼፐርድ ቤተ-ክርስቱያን የሚገኙ አቡን፣ ቄስ እና ምዕመናን ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ የ16 ዓመት ታዳጊ በቁጥጥር ሥር ውሏል።
ቢያንስ አራት ሰዎች “ሕወይታቸውን አደጋ ላይ የማይጥ” ጉዳት ደርሶባቸዋል ያለው ፖሊስ፣ ጥቃት ያደረሰውም ግለሰብ መጎዳቱን አሳውቋል።
በሲድኒ ዋኬሌ በተባለች ሥፍራ የደረሰው ድርጊት በቀጥታ ሥርጭት የተላለፈ ሲሆን፣ ሥፍራው እንዲታመስ ምክንያት ሆኗል።
የአውስትራሊያ ፖሊስ የሽብር ድርጊትን በርዕዮተ-ዓለም የተነሳ የሚፈጸ ሲል ይተነትነዋል። ምንም እንኳ ምርመራው ባይጠናቀቅም ጥቃቱ የተፈፀመው ሃይማኖታዊ ፅንፈኝነትን ተከትሎ ነው ይላል ፖሊስ።
ባለሥልጣናት ጥቃት አድራሹ ታዳጊ እምነቱ ምን እንደሆነ ከመናገር ተቆጥበዋል።
ታዳጊው አቡኑ ላይ በስለት ጥቃት ሲያደርስ የሚያሳይ ቪድዮ ማኅበራዊ ሚድያውን ያጥለቀለው ሲሆን፣ ይህን የተመለከቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤተ-ክርስቲያኗ ተመዋል።
ቤተ-ክርስቲያኗ ከከተማው ማዕከል 35 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ነው የምትገኘው።
በጥቃቱ ተቆጥተው በሥፍራው የተሰበሰቡት ሰዎች ከፖሊስ ጋር የተጋጩ ሲሆን፣ ፖሊስ ጥቃት አድራሹ ግለሰብ ሕክምና እስኪያገኝ ድረስ ቤተ-ክርስቲያኗን ከቦ ሲጠብቅ አምሽቷል።
ፖሊስ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ አቡኑ እና ቄሱ ቀዶ ጥገና እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጦ የኃይማኖት አባቶቹ “በሕይወት መቆየታቸው አስደናቂ ነው” ብሏል።
ፖሊስ ጥቃት አድራሹ ግለሰብ ወደ አቡኑ ተጠግቶ ጥቃት ከማድረሱ በፊት “ኃይማኖት ተኮር” አስተያየት መስጠቱንና በቀጥታ በሚተላለፍ ፕሮግራም ጥቃት ማድረስ የፈለገው ሆነ ብሎ መሆኑን ተናግሯል።
ተጠርጣሪው ይህን ድርጊት የፈፀመው ብቻውን መሆኑን አልፎም “እስከምናውቀው ድረስ” የሽብርተኞች መዝገብ ላይ አለመኖሩን የፖሊስ መግለጫ ያሳያል።