የሳል ሽሮፕ

ከ 4 ሰአት በፊት

ቢያንስ አምስት የሚሆኑ የአፍሪካ አገራት የተወሰኑ የጆንሰን ኤንድ ጀንሰን የሳል ሽሮፖች ከገበያ እንዲሰበሰቡ አዘዋል። “እጅግ ከፍተኛ” መርዛማ እና የመግደል አቅም ያለው ዳይትሊን ግላይኮል የተባለውን ንጥረ ነገር በምርመራ እንዳገኙበት ገልጸዋል።

ቤንይሊን የተሰኘውን የህጻናት ሽሮፕ ዓይነት ከገበያ እንዲሰበሰብ ሲል የኬንያ የመድኃኒት ተቆጣጣሪ ባለፈው ሳምንት አስታውቋል። ቀደም ሲል የናይጄሪያው ብሔራዊ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደርም ተመሳሳይ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።

ደቡብ አፍሪካ ሁለት የሽሮፑን ዓይነቶች እንዲሰበሰቡ አዛለች። ሩዋንዳ እና ታንዛኒያ ደግሞ አንዱ ዓይነት ከገበያ እንዲሰበሰብ አዘዋል።

የኬንያው የፋርማሲ እና የመርዝ ተቆጣጣሪ ቦርድ እንዲሰበሰብ የታዘዘው ምርት ግንቦት 2021 ላይ በጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተመረተ ነው። የአገልግሎት ማብቂያ ጊዜውም የካቲት 2024 ነው።

ቦርዱ ባወጣው መግለጫ በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል። በመላው አገሪቱ ማስጠንቀቂያ ማስነገሩን እና ሰዎች መድኃኒቱን በአቅራቢያቸው ለሚገኙ አከፋፋዮች እንዲመልሱም መክሯል።

የጤና ተቋማትም መድኃኒቱን በፍጥነት በማስወገድ ከሥርጭት እና ከሽያጭ ውጪ እንዲያደርጉት አሳስቧል።

የቦርዱ የማርኬቲንግ ኃላፊ ካሪም ዋንጋ እንዳሉት መድኃኒቱን ወደ ኬንያ በዋናነት የሚያስገባው አከፋፋይ በቅርቡ ያስገባቸውን ምርቶችንም ሆነ አደጋ ያስከትላሉ የተባሉትን በመያዝ ለተጨማሪ ምርመራ ትብብር እንዲያደርግ አዟል።

ተጨማሪ ምርመራ እየተከናወነ ሲሆን፣ ውጤቱ ሲታወቅ ተጨማሪ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል።

ከጆንሰን ኤንድ ጆንሰን በመለየት ቤንይሊን የተባለው ብራንድ ባለቤት የሆነው ኬንቩ ምርቶቹን የሚጠቀሙ ሰዎች “ጤና እና ደኅንነት ቀዳሚ ቦታ እንደሚይዝ” ለቢቢሲ ገልጿል። ለጉዳዩ “ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ” እንደሚመለከተው አስታውቋል።

ከናይጄሪያ የመድኃኒት ተቆጣጣሪ ጋር “ለናሙና ስለተወሰደው ምርት ትክክለኛነት፣ ጥቅም ላይ ስለዋለው የሙከራ ዘዴ እና በኤጀንሲው ሪፖርት የተደረጉ ውጤቶችን” ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ግምገማዎችን በማካሄድ ላይ መሆኑን ኩባንያው በመግለጫው አስታውቋል።

የሳል ሽሮፕ

ሽሮፑ ለምን አደገኛ ነው ተባለ?

እንደ ናይጄሪያው የመድኃኒት ተቆጣጣሪ ተቋም ከሆነ ዳይታሊን ግላይኮል የሆድ ህመም፣ ማስታወክ፣ ተቅማጥ እና የኩላሊት መቁሰልን ጨምሮ ከባድ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል።

እአአ ከ2022 ጀምሮ ዳይታሊን ግላይኮል በጋምቢያ፣ በኡዝቤኪስታን እና በካሜሩን ከበርካታ ህጻናት ሞት ጋር ተያይዟል።

በካሜሩን እና በጋምቢያ ህጻናት መሞታቸውን ተከትሎ በሕንዱ ኩባንያ ማይደን ፋርማሲዩቲካልስ የተመረቱ አራት የሳል ሽሮፖች ላይ ዓለም አቀፍ ማስጠንቀቂያ ወጥቷል።

የዓለም ጤና ድርጅት ሽሮፖቹን ከ66 ህጻናት ሞት ጋር በማያያዝ፤ በመድኃኒቶቹ ውስጥ “ተቀባይነት የሌለው” የመርዛማነት መጠን ማግኘቱን ገልጿል።

የህጻነቱን ሞት የመረመረው የጋምቢያ ፓርላማ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አማዱ ካማራ “እነዚህን መድኃኒቶች መርምረናል፤ ማስረጃም አለን” ብለዋል።

ሽሮፖቹ “ተቀባይነት የሌለው መጠን ያለው ኤቲሊን ግላይኮልን እና ዳይታሊን ግላይኮልን ያላቸው ሲሆን፣ በቀጥታ ከሕንድ የመጡ እና በሜይደን የተመረቱ ናቸው” ብለዋል።

ማስተባበያ

ማይደን ፋርማሲውቲካልስ እና የሕንድ መንግሥት በሳል ሽሮፑ እና በህጻናቱ ሞት መካከል ግንኙነት የለም በማለት ጉዳዩን ውድቅ አድርገዋል።

ሕንድ እአአ ታኅሣሥ 2023 ሽሮፑ ላይ በአገር ውስጥ በተደረገ ምርመራ የጥራት ደረጃዎችን እንደሚያሟላ መረጋገጡን አስታውቃለች።

ኩባንያዎች ወደ ውጭ ከመላካቸው በፊት የሳል ሽሮፕ ናሙናዎች በመንግሥት በተፈቀደላቸው ቤተ ሙከራዎች መመርመር እንዳለባቸው ለኩባንያዎች አስገዳጅ እርምጃዎችን ማውጣቷን ጨምራ ገልጻለች።

ጋምቢያም ከሐምሌ 2023 ጀምሮ ከሕንድ ለሚገቡ መድኃኒቶች መስፈርቱ ተግባራዊ እንዲደረግ አዛለች።

ሕንድ እአአ መጋቢት 2023 በሚጠናቀቀው የፋይናንስ ዓመት 25.4 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ መድኃኒቶችን ወደ ውጭ ልካለች። ከዚህ ውስጥ 3.6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣውን የላከችው ለአፍሪካ አገራት ነው።