April 16, 2024 – Konjit Sitotaw
አብን፣ የሕወሃት ኃይሎች በድጋሚ በአማራ ሕዝብ ላይ “አራተኛ ዙር” ጥቃት ከፍተዋል ሲል ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ከሷል። የፌዴራሉ መንግሥትና የአማራ ክልላዊ መንግሥት ሕወሃት በአማራ ሕዝብ ላይ የከፈተውን ሌላ ዙር ጥቃት ባስቸኳይ እንዲያስቆሙ የጠየቀው አብን፣ የአማራ ሕዝብ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት የሕወሃትን ጥቃት እንዲመክትም ጥሪ አድርጓል። አብን፣ መንግሥት የሕወሃትን ጥቃት በዝምታ ከተመለከተ፣ ድርጊቱ “የኹሉ ነገር መፍረሻና ማፍረሻ” እንዲኾን ፈቅዷል ማለት ነው ብሏል። አብን ይህን መግለጫ ያወጣው፣ የሕወሃት ኃይሎች በራያ አላማጣ አካባቢ አንዳንድ ቦታዎችን እየተቆጣጠሩ ስለመኾኑ በተሰማ ማግስት ነው።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፣ በደቡብ ትግራይና በሌሎች በኃይል የተያዙ የትግራይ ግዛቶች ባኹኑ ወቅት የተፈጠረው ክስተት በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ወይም በሕወሃት ወይንም በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል የተፈጠረ ግጭት አይደለም ሲሉ ትናንት እኩለ ሌሊት ላይ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስተባብለዋል።
ጌታቸው፣ ክስተቱ ኹለቱ ወገኖች የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ እያደረጉት ያለውን አወንታዊ ግንኙነት ለማደናቀፍ የፈለጉ የስምምነቱ ጠላት የኾኑ ኃይሎች የፈጠሩት ነው በማለት ከሰዋል። ከሩቅም ከቅርብም የግጭት ማቆም ስምምነቱ ጸር የኾኑ ኃይሎች ጦር እየሰበቁ መኾኑን የጠቀሱት ጌታቸው፣ ብቸኛው አዋጭ መንገድ ግን ሰላም ነው ብለዋል። ኹለቱ ወገኖች ችግሮችን ለመፍታትና የሚስማሙባቸውን ጉዳዮች ለማጎልበት አዲስ አበባ ውስጥ ስብሰባ ላይ እንደኾኑም ጌታቸው ጠቁመዋል።