April 16, 2024 – Konjit Sitotaw 

“ ሕወሓት /TPLF ወረራ ፈጽሟል። የፕሪቶሪያውን ስምምነት ጥሷል ” – አቶ ሀይሉ አበራ

የትግራይ እና አማራ ክልሎች የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች በሚያነሱባቸው የራያ አላማጣ አካቢዎች ሰሞኑን በተለይ ዛሬ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን የአላማጣና አካባቢው ባለስልጣናትና የአካባቢው ነዋሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

የአላማጣ ከተማ እና ዙሪያው ነዋሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል፣ “ የትግራይ ታጣቂዎች በስናይፐርና ሌሎች መሳሪያዎች የታገዘ ተኩስ ተከፍቶብናል ” ብለዋል።

አክለውም፣ “ ባለፈው ጦርነት በደረሰብን ሀዘን እንባችን አልደረቀም። መንግሥት ግን እስከመቼ ድረስ ነው የዚህን አካባቢ ችግር የማይቀርፈው ? ነው ወይስ ሕዝቡ እርስ በእርሱ እንዲተላለቅ ነው የፈለገው ? ” ሲሉ ጠይቀዋል።

“ ወያኔ የኔ ናቸው የሚላቸው የአላማጣና አጠገቡ አካባቢዎች በሙሉ የአማራ እንጂ የትግራይ መሬት ሆነው አያውቁም። ደማችን ይፍሰስ እንጂ መሬታችንን አንለቅም። መንግሥት የትግራይ አመራሮችን ይዳኝልን ” ብለው፣ በንጹሐንና በንብረት ላይ ጉዳት ሳይደርስ እንዳልቀረ፣ አሁን ግን ትክክለኛውን ቁጥር ለመግለጽ ለጊዜው እንደሚያስቸግር አስረድተዋል።

ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ጥያቄ ያቀረበላቸው አንድ የአላማጣና አካባቢው አመራር በሰጡት ቃል፣ “ ወያኔ ሰሞኑን በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን ተቆጣጥሯቸው ከነበሩ ቦታዎች በተጨማሪ ተቆጣጥሯል። አርሚ 24 ነው ተኩስ የከፈተብን ” የሚል አጭር ቃሎ ሰጥተው ሁነቱን በሂደት እንደሚገልጹ ጠቁመዋል።

በተጨማሪ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ስለግጭቱ ሁኔታ፣ የደረሰው ጉዳት ምን እንደሚመስል አላማጣ ከተማን በከንቲባነት እያስተዳደሩ ለሉትና የወሎ ራያ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ ለሆኑት አቶ ሀይሉ አዱኛ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ፥ “ ሕወሓት ወረራ ፈጽሟል። የፕሪቶሪያውን ስምምነት ጥሷል። ፍላጎታቸውን በኃይል ለመፈጸም እየሞከሩ ነው። ሂደቱ በዋነኝነት ይህን ነወሰ የሚመስለው። ዝርዝር ገለጻ ነገ እሰጣለሁ ” ብለዋል።

ዝርዝር ምላሻቸው ነገ ይቀርባል።

🔵 በትግራይ በኩል ምን ተባለ ?

የቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለው አባል ፥ በትግራይ በኩል ነዋሪዎችን እና የመንግስት ሰዎችን ስለ ሁኔታው ጠይቋል።

ዛሬ ከሰዓት ቃላቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ፥ ” የራያ ጨርጨር ፣ የራያ አላማጣ ፣ ኮረም ኦፍላና ዛታ አከባቢ ያሉ ቀበሌዎች ከታጣቂዎች ነፃ ሆነዋል ” ብለዋል።

አጠቃላይ በርካታ ስፍራዎች ቦታውን ይዘው ከነበሩ ታጣቂዎች ነጻ ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል።

በከፍተኛ የፀጥታ ስጋት ምክንያት ከአካባቢው የወጡ ነዋሪዎችም አሉ ሲሉ ገልጸዋል።

አሁንም ቢሆን የፕሪቶሪያው ስምምነት ተከብሮ የአማራ ታጣቂዎች ከአካባቢው ሊወጡ የተፈናቀለው ህዝብም ወደ ቦታው ሊመለስ ይገባል ብለዋል።

ትናንትና ወደ ራያ ጨርጨር አስተዳዳሪ አቶ ካልኣዩ ግደይ ደውለን የነበረ ሲሆን መጠነኛ ግጭት እንደነበረ ተናግረዋል።

ዛሬ በሰጡት ቃል ደግሞ ፥ ” በወረዳው በአማራ ታጣቂዎች ሰር የነበሩት ሁለት ቀበሌዎች ነፃ ወጥቷል ” ብለዋል።

ሌሎች የክልሉን ኃላፊዎች ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

የትግራይና አማራ ክልሎች ይገባኛል በሚያነሱበት በራያ አካባቢ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግጭት ሁኔታዎች ይታዩ እንደነበር በሁለቱም በኩል ያሉ የመንግስት አካላትን በማነጋገር መረጃ ማድረሳችን ይታወሳል።