ፅዮን ታደሰ

April 17, 2024

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት

በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ባለው የኮሪደር ልማት የተነሱ ነጋዴዎችን አስመልክቶ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌለው፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራ ምክር ቤት ገለጸ፡፡

ሪፖርተር ከምክር ቤቱ ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የምክር ቤቱ አባል የሆኑ የተወሰኑ ነጋዴዎች ምክር ቤቱ ድምፅ እንዲሆናቸው አመልክተዋል፡፡ የነጋዴዎቹን ጥያቄ መነሻ በማድረግም በጉዳዩ ላይ ውይይት ለማድረግ እየታሰበ መሆኑ ተገልጿል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት በከተማ አስተዳደሩ እየተካሄደ ባለው የኮሪደር ልማት ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህ በፊት ሲካሄዱ በነበሩ የከተማው የልማት እንቅስቃሴዎች ላይም እየተጎዱ ያሉ ነጋዴዎችን አስመልክቶ ለመነጋገር አስፈላጊ ዝግጅት ለማድረግ መታሰቡን ከምክር ቤቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ምክር ቤቱ የኮሪደር ልማቱ በነጋዴዎች ላይ ምን ያህል ጫና ያሳድራል የሚለውን ለመገንዘብ ከመንግሥት ተቋማት የሚፈለገው መረጃ ማግኘት አለመቻሉን፣ በዚህም ምክንያት ሌሎች የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ብቻ ሳይሆኑ የምክር ቤቱ ሕንፃም  ሰለባ እየሆነ ነው ተብሏል፡፡

የኮሪደር ልማቱ በምን ያህል ስፋት እየተከናወነ እንደሆነ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መረጃ ደርሶት እንደሆነ እንደማይታወቅ፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ግን የደረሰው ምንም ዓይነት መረጃ የለም ተብሏል፡፡

ምን ያህል የምክር ቤቱ አባላት በኮሪደር ልማቱ የንግድ ቦታዎቻቸው እንደፈረሱ መረጃ እየተሰበሰበ ነው ያሉት የንግድ ምክር ቤቱ ኃላፊ፣ እንዲህ ዓይነት የልማት ሥራዎች ሲካሄዱ ለምክር ቤቱ መረጃ መሰጠት እንደነበረበትና ሕጉም እንደሚያስገድድ ገልጸው ነገር ግን የደረሰ መረጃ አለመኖሩን አስታውቀዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ‹‹ፒያሳ አካባቢ የነበሩ ነጋዴዎች እንደሰበሰበና እንዳነጋገረ፣ ለነጋዴዎችም አሮጌው ቄራ አካባቢ መሥሪያ ቦታ እንደተሰጣቸው ሰምተናል፡፡ ነገር ግን ምክር ቤቱ የንግዱ ማኅበረሰብ ወኪልና አካል ነው በሚል ከእኛ ጋር ለመነጋገር አልሞከረም፤›› ብለዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ከምክር ቤቱ ጋር ውይይት አድርጎ ነበር ወይ? ውይይቱን ካላካሄደም ምክንያቱ ምንድነው? የሚሉ ጉዳዩችን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ሙከራ ሊሳካ አልቻለም፡፡

ሆኖም የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር ዓባይ በኮሪደር ልማቱ ዙሪያ ከኢቲቪ ጋር አድርገውት በነበረው ቆይታ፣ በፕላኑ ውስጥ ሊኖሩ ከሚችሉ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይቶች ተደርገዋል ብለዋል፡፡ አሁንም ቅሬታ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሰማ አደረጃጀት ተፈጥሯል ሲሉም አቶ ጃንጥራር ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳኔች አቤቤ በበኩላቸው፣ የኮሪደር ልማት ሥራው ሲከናወን ረዥም ጊዜ የወሰደ ጥናት መካሄዱን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በዚህም ቅሬታ ያለውን የማንኛውም ነዋሪ ሐሳብ ለመስማት ዝግጁ መሆናቸውን  ተናግረው ነበር፡፡