ዜና ምርጫ ቦርድ አጠራጣሪ መረጃ ላቀረቡ 21 የፖለቲካ ፓርቲዎች ትዕዛዝ አስተላለፈ

ዮናስ አማረ

ቀን: April 17, 2024

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአባሎቻቸውን ቁጥር በተጋነነ ወይም አጠራጣሪ በሆነ መንገድ ሪፖርት ላቀረቡ 21 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተጣራ መረጃ ይዘው እንዲቀርቡ የሚያዝ ደብዳቤ ጻፈ፡፡ ቦርዱ ደብዳቤውን የጻፈው በ21 የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ሲሆን፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተጣራ መረጃ ይዘው እንዲቀርቡ ማዘዙን ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የአባላቶቻቸውን ቁጥር በተለይም የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች አባሎቻቸውን ቁጥር በተዛባ (በተጋነነ) አኃዝ እያስደገፉ አቅርበዋል የሚል እምነት እንዳደረበት ገልጿል፡፡ ይህ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን መጣስ እንዳስከተለ አስታውቋል፡፡

ቦርዱ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ለአገው ብሔራዊ ሸንጎ ፓርቲ በጻፈው ደብዳቤ፣ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች ቁጥርን በሚመለከት ምርጫ ቦርዱ ጥርጣሬ እንዳደረበት መግለጹን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የአገው ሸንጎ ፓርቲው በ2014 ዓ.ም. ሴት አባላቱ 3,047 ናቸው ብሎ ማቅረቡንና በ2015 ዓ.ም. ደግሞ 4‚002 አድርጎ ማቅረቡን በማስታወስ፣ በ2016 ዓ.ም. ግን ይህ አኃዝ ወደ 42‚560 አሳድጎ ማቅረቡ ምርጫ ቦርድን እንዳጠራጠረው ደብዳቤው ይገልጻል፡፡ የአካል ጉዳተኞቹ አባላት ቁጥር በ2014 ዓ.ም. 27 የነበረው በ2015 109 መድረሱን፣ በ2016 ዓ.ም. ደግሞ እጅግ በጣም ጨምሮ 5‚234 ደረሰ የሚለው ቦርዱ ይህም የተጋነነ ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም የተጣራ መረጃ ፓርቲው እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በዚህ ለአገው ብሔራዊ ሸንጎ ላይ በተጻፈው ደብዳቤ ፓርቲው ባቀረባቸው መረጃዎች በፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር አዋጅ አንቀጽ 78/1ሀ፣ እንዲሁም 79/1 ላይ የተቀመጡ የተጣራ የአባላት ቁጥርና መረጃ የማቅረብ ግዴታዎችን ጥሶ ሊሆን እንደሚችል ቦርዱ ገልጿል፡፡ ከዚህ ተነስቶም ፓርቲው አሉኝ የሚላቸውን የሴትና የአካል ጉዳተኞች አባላቱን ስም ዝርዝር እስከ አያታቸው፣ ዕድሜ፣ የመኖሪያ አድራሻና ሌሎች ተዓማኒ መረጃዎች በአንድ ወር ጊዜ እንዲያቀርብም አዟል፡፡

ሪፖርተር በዚህ ጉዳይ ላይ ያናገራቸው የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ሊቀመንበር አቶ አላምረው ይርዳው ግን፣ ምርጫ ቦርድ አሟሉ ያላቸውን ጥያቄዎች በተሰጠው ጊዜ አሟልቶ ለማቅረብ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አሉ ብለዋል፡፡ ‹‹ፓርቲያችን በሚንቀሳቀስባቸው የአማራና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች አካባቢዎች ያለው የሰላም ሁኔታ የአባሎቻችንን መረጃ አጣርቶ ለማቅረብ ፈተና እንደሚሆንብን በመጥቀስ ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ጽፈናል፡፡ ለዚህ ምላሽ እየተጠባበቅን እንገኛለን፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

ቦርዱ አጠራጣሪ ሆኑብኝ የሚላቸው የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች ቁጥርን፣ ‹‹ለእኛ እንዲያውም ትንሽ ነው፡፡ አባላቶቻችንን ለማብዛት ብዙ ሠርተናል፡፡ ስለዚህ ከተጠቀሰው በላይ አባል ማቅረብ እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡

አቶ አላምረው የአባላትን መረጃ ቦርዱ በጠየቀው መሠረት በተሟላ ሁኔታ አጠናቅሮ ለማቅረብ በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ምቹ የሰላም ሁኔታ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቦርዱ የተጋነነ ሊሆን ይችላል ያለውን መረጃ እንዲያውም ትንሽ ነው በማለት፣ ከዚያ በላይ አባላት ማፍራታቸውን በመጠቆም ከላይ ያነሱትን ሐሳብ አፍርሰውታል፡፡

ከምርጫ ቦርድ እንደተገኘው መረጃ ከሆነ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች በተጋነነ አኃዝ አስደግፈው የአባሎቻቸውን፣ በተለይም የሴቶችና አካል ጉዳተኞች መረጃ የሚያቀርቡት ከቦርዱ ለሚያገኙት የበጀት ድጎማ መጨመር ሲሉ ነው፡፡

ቦርዱ በዚህ መሰል የተጋነነ ወይም የተሳሳተ መረጃ የበጀት ጭማሪ ለማግኘት የሚሞክሩ ፓርቲዎችን በሚያደርገው ማጣራት፣ ጥፋተኛ ሆነው ካገኛቸው እስከ መሰረዝ ሊሄድ እንደሚችል ነው ያስታወቀው፡፡

ምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎች የበጀት ድልድል ከማድረጉ በፊት ብቻ ሳይሆን፣ ያከፋፈለው በጀት በትክክል በሥራ ላይ መዋሉን የሚከታተልበት ጥብቅ አሠራር እንዳለው ይገልጻል፡፡

ቦርዱ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ለአንድነት ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በጻፈው ደብዳቤ፣ ፓርቲው የበጀት ድጋፍ አጠቃቀም የግልጽነትና ተጠያቂነት ሥርዓት ጉድለት እንዳገኘበት ገልጾ ነበር፡፡ ፓርቲው ለ2015 በጀት ዓመት 2,750,873 ብር በጀት እንደተፈቀደለት የገለጸው ቦርዱ፣ ይሁን እንጂ ባቀረበው የበጀት አጠቃቀም ኦዲት ሪፖርት አሳማኝ ባለመሆኑና ጉድለት በመገኘቱ በፓርቲው አመራሮች የተፈጸመው ድርጊት ተጣርቶ እስከሚቀርብ ፓርቲውና አመራሮቹ መታገዳቸውን በዚሁ ደብዳቤ አሳውቋል፡፡