በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ከተማ በተካሄደው ዕርዳታ የማሰባሰብ መርሐ ግብር የተገኙ የለጋሽ አገሮች ተወካዮች

ዜና በጄኔቫ ለኢትዮጵያ በተካሄደ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማሰባሰቢያ መድረክ 630 ሚሊዮን ዶላር ተገኘ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: April 17, 2024

በሲሳይ ሳህሉ

በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ለኢትዮጵያ አስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ድጋፍ ለማፈላለግና ለማስተባበር በተጠራው ስብሰባ፣ ከ21 ለጋሾች 630 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱ ተገለጸ፡፡

የእንግሊዝ መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 21 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን፣ በጄኔቫ ዕርዳታ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡

ኢትዮጵያ ከሚያስፈልጋት 3.2 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ በተካሄደው ስብሰባ እንግሊዝ 100 ሚሊዮን ፓውንድ፣ አሜሪካ 154 ሚሊዮን ዶላር፣ ሉግዘምበርግ 2.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ዴንማርክ 14 ሚሊዮን ዶላር፣ አየርላንድ 9.5 ሚሊዮን ዩሮ፣ ደቡብ ኮሪያ 18 ሚሊዮን ዶላር፣ ቼክ ሪፐብሊክ 8.6 ሚሊዮን ዩሮ፣ እንዲሁም ኖርዌይ 5.2 ዩሮ ድጋፍ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ ሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2024 ትኩረት ከሚያስፈልጋቸው ዘጠኝ የዓለም አገሮች ውስጥ አንዷ መሆኗን ገልጾ ነበር፡፡  

ተመድ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎትን ለማሳካት 3.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ፣ እስካሁን የተገኘው ግን ከአራት በመቶ በታች እንደሆነ ገልጿል፡፡ በተመሳሳይ እ.ኤ.አ. በ2023 ማሳካት የተቻለው ከሚፈለገው 36 በመቶ የሚሆነውን ብቻ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በጄኔቫ የዕርዳታ ማፈላለጊያ መድረክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አፅቀ ሥላሴ (አምባሳደር) በጄኔቫው መድረክ ባቀረቡት የመክፈቻ ንግግር፣ የተቀናጀ ዕድገት ዕቅድን ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን ኢትዮጵያ እያከናወነች መሆኗን ተናግረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ንግግር እያደረጉ በነበሩበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚቃወም ድምፅ ተሰምቶ ነበር፡፡ ሚኒስትሩም፣ ‹‹እዚህ የመጣነው ለመሰድብ አይደለም፤›› የሚል ምለሽ ሰጥተዋል፡፡ የሚኒስትሩን  ንግግር እንዲቋረጥ ያደረጉት ግለሰብ ከስብሰባው በፀጥታ ሠራተኞች እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡

የእንግሊዝ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪው ሚሸል ባደረጉት ንግግር፣ ከወራት በፊት በኢትዮጵያ በነበራቸው ጉብኝት ሕፃናትና እናቶች በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ዕጦት ተቸግረው መመልከታቸውንና ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ስም በመጥራት ድጋፍ ማድረግ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን መደገፍ እንደሆነ የተቃውሞ ድምፅ ሲሰማም፣ ምክትል ሚኒስትሩ በዚህ መንገድ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲቋረጥ ማድረግ ተቀባይነት የለውም በማለት ንግግራቸውን ቀጥለዋል፡፡

የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ ዓለም አቀፍ ለጋሾች ለኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ  የሚሆን ድጋፍ እንዲያደርጉ በጠየቀበት መግለጫው፣ በአየር ንብረት ለውጥና በግጭት ምክንያት፣ እንዲሁም በድርቅ ሳቢያ ያጋጠመውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ለማርገብ የሚረዳ ድጋፍ እንዲያደርጉ ለአገሮች መሪዎች ጥሪ አቅርቧል፡፡

ቀይ መስቀል ለጋሽ አካላት በድርቅ፣ በጎርፍና በተመጣጠነ ምግብ ዕጦት ለተጎዱ ሰዎች የሕይወት አድን ዕርዳታ፣ ምግብ፣ ውኃና ሕክምና ለማድረስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት ጊዜ አሁን ነው ብሏል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭቶችና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከሚያስከትሏቸው ተፅዕኖዎች አንፃር ለጋሽ ድርጅቶች ወቅታዊውን ችግር ለመፍታት ብቻ ሳይሆን፣ ማኅበረሰቦችን ለወደፊት በተሻለ ሁኔታ እንዲዘጋጁ የሚያግዙ የማገገምና የአቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ ድጋፍ እንዲያደርጉ የጠየቀው ቀይ መስቀል፣ ‹‹በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች ሕይወት አደጋ ላይ ነው፣ መዘግየት አንችልም፤›› ብሏል።

ይህ በዚህ እንዳለ የጀርመን ተወካይ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ የደረሰው ዝርፊያ ሙሉ ምርመራ እንዲደረግና የሰብዓዊ ዕርዳታ ስርቆት እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡  አክለውም  መንግሥት በሰብዓዊ ዕርዳታ ሥርጭት ላይ ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆም አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ሠራተኞች ጤንነትና ደኅንነት እንዲጠበቅ፣ እንዲሁም የዕርዳታ ድርጅቶች ሠራተኞች ወደ አገር ውስጥ በሚያስገቧቸው ተሽከርካሪዎችና ቁሳቁሶች ላይ የተጣለው ታክስ እንዲቆም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የጀርመኗ ተወካይ በንግግራቸው አገራቸው እ.ኤ.አ. በ2023 ከሰጠችው ድጋፍ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ገንዘብ እ.ኤ.አ. 2024 ለመስጠት የምትፈለግ ቢሆንም፣ ይህን ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁኔታዎችን አስተካክሎ በለጋሽ አካላት ላይ እምነት ማሳደር አለበት ብለዋል፡፡ እንዲሁም ተጨባጭና ገንቢ ሪፎርም አድርጎ የዕርዳታ ስርቆትን በማስቀረት ሕይወት አድን የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚፈልጉ ወገኖች በተገቢው መንገድ መድረስ ሲቻል እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ የጀርመኗ ተወካይ ጋር ንግግር ሲያደርጉ አንዲት ሴት፣ ‹‹ጀርመን እናመሠግናለን፣ ጀርመን እናመሠገናለን›› የሚል ድምፅ በሚል በጩኸት ሲያሰሙ ከአዳራሹ በፀጥታ ሠራተኞች እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡

በተመሳሳይ ስዊድን 21 ሚሊዮን ዩሮ ለመደገፍ ቃል ገብታለች፡፡  ይሁን እንጂ ስዊደን የኢትዮጵያ መንግሥት የቢሮክራሲ ማነቆዎች እንዲቃለሉ፣ ለዕርዳታ ሠራተኞች የሥራ ፈቃድና የቪዛ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲያቀላጥፍ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

የስዊዘርላንድ መንግሥት ሰብዓዊ ዕርዳታ በግልጽነትና ተጠያቂነት በተሞላበት መንገድ እንዲፈጸም፣ በኢትዮጵያ ለተፈናቀሉ ዜጎች ቋሚ የሆነ መፍትሔ እንዲሰጣቸው የስዊዘርላንድ መንግሥት ተወካይ  ጠይቀዋል፡፡ በርካታ አገሮች የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትና ሥርጭትን በጠንካራ ክትትል እንዲስፈጽምና ድጋፍ ለሚስፈልጋቸው አካላት መድረሱን ማረጋገጫ ጠንካራ ሥርዓት እንዲዘረጋ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ታዬ (አምባሳደር) የቀረቡትን አስተያየቶች መንግሥታቸው በሚገባ መቀበሉን ገልጸዋል፡፡