የአላማጣ ከተማ ከፊል ገጽታ

ዜና በአላማጣና በአካባቢው በነበረው የተኩስ ልውውጥ በርካታ ነዋሪዎች ለቀው ወጡ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: April 17, 2024

ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደ

ባለፉት ጥቂት ቀናት በራያ አላማጣ አካባቢዎች በነበሩ የተኩስ ልውውጦች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አካበቢውን ለቀው ወደ ቆቦ ከተማና ወልዲያ አቅጣጫ መፈናቀላቸው ተገለጸ፡፡

የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ ለሪፖርተር እንደገለጹት ከቅዳሜ ጀምሮ የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች ወደ አላማጣና አካባቢው ዘልቀው መግባታቸውን፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት በመጣስ መፈክሮችን በማሰማት ቅስቀሳ ሲያደርጉ ነበር ብለዋል፡፡  በአላማጣና በአካባቢው በተከሰተው ሥጋትና የተኩስ ልውውጥ በርካታ  ነዋሪዎች ከከተማ ለቀው መውጣታቸውን አቶ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹እኛ ተፈናቃይ አይግባ አላልንም፣ ተፈናቃዮች እንዲገቡ በሽማግሌ ጭምር ጠይቀናል፡፡ ነገሩ ግን ተፈናቃይን መመለስ ሳይሆን የፖለቲካ ጨዋታ ነው፡፡ የፕሪቶሪያ ስምምነት ቢፈጸም ሊመጣ የሚችለውን ውጤት ስለሚያውቁት እነሱ ነገሩን ሌላ መልክ ማስያዝ ነው የፈለጉት፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ  ሪፖርተር ከቆቦና ከአላማጣ ነዋሪዎች ባገኘው መረጃ በርካቶች በመደናገጥ ስሜት ተፈናቅለው መውጣታቸውን፣ በእጃቸው የያዙት ለዕለት አገልግሎት የሚሆኑ የተወሰኑ መሣሪያዎችን ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርና በፌዴራል መንግሥቱ ወይም በጊዜያዊ አስተዳዳሩና በአማራ ክልል መካከል ምንም ዓይነት ጦርነት አለመኖሩን፣ በአካባቢው የተከሰተው የፕሪቶሪያ ስምምነት አንዳይፈጸም አጥብቀው የሚፈልጉ ኃይሎች ሥራ ነው ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ በራያ አላማጣ ወረዳ የተለያዩ አካባቢዎች ለተከታታይ ቀናት በቀጠለው የተኩስ ልውውጥ ሥጋት የተሰማቸው ነዋሪዎች ከተማውን ለቀው እየወጡ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ኃይሉ፣ መንግሥት ትብብር ሊያደርግና ‹‹አዋጭ መፍትሔ›› ሊኖረው ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሕወሓት ወረራ ሊፈጽም እንደሚችል ለመንግሥት በተደጋጋሚ ቅሬታቸውንና ሥጋታቸውን እንዳሳወቁ የገለጹት አቶ ኃይሉ፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥቱ ለትግራይ ክልል እንደሚያስበው ሁሉ ለእኛም ሊያስብልን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ጌታቸው በበኩላቸው የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲፈጸም ሁለቱም ወገኖች ሌት ተቀን እየሠሩ መሆኑን ገልጸው፣ ውጤቱ ሁለቱ ወገኖች ተግዳሮቶችን ለመፍታትና ለማጠናከር በአዲስ አበባ እየተነጋገሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲተገበር የማይፈልጉ ቅርብና ሩቅ የሚገኙ አካላት የጦርነት ቅስቀሳና ጩኸት እያደረጉ ቢሆንም፣ ብቸኛው መንገድ ሰላምና ንግግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በጉዳዩ ላይ ሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ ‹‹በሁሉም አካባቢዎች የሚገኘው ሕዝባችን ካለፈው የጥፋት ጊዜ በመማር ከታሪካዊ ጠላቱ የሚሰነዘርበትን ወረራ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት እንዲመክት፤›› ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡

በተጨማሪም ሕዝቡ ከሕወሓት በኩል ለሚመጣ ማንኛውንም ውዥንብር ጆሮ እንዳይሰጥ፣ የወገን ኃይሎች ለወያኔ የሚያሳዩትን የተለሳለሰ የባንዳነት መንገድ ሕዝባችን ፈጽሞ እንዳያዳምጥና እንዲህ ያሉትን ቡድኖች አጥብቆ እንዲታገል፤›› ሲል አብን አስታውቋል፡፡

አብን የአማራና የአፋር ሕዝቦች የጦርነቱ ዋና ገፈት ቀማሽ በመሆናቸው፣ የኢትዮጵያ ኃይሎች የሚፈልጉትን ሁሉ በማቅረብ ከአገራቸው ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡

አብን ባወጣው መግለጫ በሕወሐት ችግር የአማራና የትግራይ ሕዝቦች፣ እንዲሁም መላ አገሪቱና ቀጣናው ችግር ውስጥ እየወደቁ ስለሆነ ይህ በአስቸኳይ እንዲቆም ብሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንትና የፀጥታና ሰላም ምክር ቤት ኃላፊ ሌተናል ጄኔራ ታደሰ ወረደ ማክሰኞ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ የትግራይና የአማራ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች የተቋቋመው የአማራ ክልል የአስተዳደር መዋቅሮች እንዲፈርሱ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

በምዕራብ ትግራይ፣ በፀለምትና በደቡብ ትግራይ የተቋቋሙ የአማራ ክልል የአስተዳደር መዋቅሮች እንዲፈርሱ፣ እንዲሁም በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ የታጠቁ ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱና ከአካባቢዎቹ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች እንዲመለሱ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ስምምነት መደረሱን አስታውቀዋል፡፡

በቀጣይ ደግሞ በተጠቀሱት አካባቢዎች ከተፈናቀሉ ነዋሪዎች ላይ የተነጠቁ የመሬት ይዞታዎችና ቤቶች ለተፈናቃዮች እንዲመለሱ ለማድረግ መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ውዝግብ በተነሳባቸው አካባቢዎች ዘላቂ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ በፌዴራል መንግሥት የተቀመጠውን ሕዝበ ውሳኔ፣ አሁንም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንደማይቀበለው ገልጸዋል፡፡