

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ (ከግራ ሁለተኛው) ቤቴልአቪቭ በሚገኘው የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ከጦር አበጋዞቻቸው ጋር መክረዋል (የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር)
ዓለም ኢራን በእስራኤል ምድር የሰነዘረችው ጥቃት
ቀን: April 17, 2024
ኢራን በእስራኤል ምድር ቅዳሜ ሚያዝያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ሌሊት ያዘነበችውና 99 በመቶ ያህሉ ከሽፏል የተባለው የሚሳኤልና የድሮን ጥቃት፣ የዓለም ሰሞነኛ አጀንዳ ሆነ እንጂ በእስራኤልና ኢራን መካከል ያለው አለመተማመንና አለመግባባት በርካታ አሠርታትን ያስቆጠረ ነው፡፡
እስራኤል በተገኘው መድረክ ሁሉ ኢራንን ‹‹ሥጋቴ›› ናት ሳትል የቀረበችበት አጋጣሚ የለም፡፡ ‹‹ኢራን የኑክሌር ጦር መሣሪያ እያመረተች ነው፣ ማምረትም ሆነ መሣሪያው በእጇ ሊገባ አይገባም፤›› የሚለው የዘወትር ውትወታም፣ የእስራኤል ብቻ ሳይሆን አሜሪካን ጨምሮ በአውሮፓ የሚገኙ የእስራኤል ወገንተኛ አገሮች አቋም ነው፡፡

ማክሸፏን አሜሪካ ገልጻለች (ሮይተርስ)
እስራኤል የፍልስጤማውያንን ምድር ወርራ ሠፍራለች፣ ፍልስጤማውያን ላይ ግፍና ሰብዓዊ ጥሰት ትፈጽማለች፣ በጋዛው ጦርነት እስራኤል በሺዎች የሚቆጠሩ ገድላ፣ መሠረተ ልማት አፈራርሳለች በሚል በተለይ በዓረቡ አገሮች የምትወቀሰው እስራኤል፣ መቼውንም ለኢራን ተኝታም አታውቅም፡፡
በየጊዜው የፍልስጤሙ ሃማስ፣ የሊባኖሱ ሂዝቦላህ፣ የየመኑ ሁቲ እንዲሁም በኢራቅና ሶሪያ ያሉ በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉ ቡድኖችና ታጣቂዎች በእስራኤል ግዛት በተደጋጋሚ ጥቃት ሲሰነዝሩ ይሰማል እንጂ፣ ኢራን በቀጥታ እስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽማለች ሲባል አይሰማም፡፡
ከእስራኤል ወገን ግን በኢራን ምድር በርካታ ጥቃቶች ተፈጽመዋል፡፡ ተቋማትንና ግለሰቦችን በቦምብ ከመበታተን እስከ ሳይበር ጥቃት እስራኤል በኢራን ላይ ፈጽማለች፡፡
ኢራን በእስራኤል ላይ ለፈጸመችው ጥቃት መነሻው እስራኤል በሶሪያ ደማስቆ በሚገኘው የኢራን ቆንጽላ ጽሕፈት ቤት ፈጽማዋለች በተባለው ጥቃት ከፍተኛ ጄኔራሎችን ጨምሮ 13 ሰዎችን ማጣቷ እንደሆነ፣ ዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙኃን የኢራን ባሥልጣናትን ጠቅሰው ዘግበዋል፡፡
አልጀዚራ እንደሚለውም፣ ዛሬ ላይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢራን እስራኤል ላይ ጥቃት ፈጸመች ብሎ አጀንዳ ያድርገው እንጂ፣ እስራኤል በኢራን ተቋማትና ሥጋቴ ናቸው በምትላቸው የኢራን ዜጎች የፈጸመቻቸው በርካታ ጥቃቶች ይህንንም ያህል ትኩረት ሳይሰጣቸው ቀርተዋል፡፡

ከሆነ፣ ኢራን ኃይል ጨምራ እስራኤን እንደምትመታ
አስጠንቅቃለች (ዘ ጋርድያን)
እስራኤልና አጋሮቿ በተደጋጋሚ ‹‹ኢራን ኑክሌር ቦምብ እያመረተች ነው፤›› በሚል ወቀሳ ይሰነዝራሉ፡፡ ኑክሌርን ለኃይል አቅርቦት መጠቀም መብቷ እንደሆነ የምትከራከረው ኢራን፣ ለወታደራዊ ፕሮግራም እንደማትጠቀም በተደጋጋሚ ብትናገርም ከሳይበር እስከ ሳይንቲስቶቿ ግድያ የሚዘልቅ ጥቃት እንደሚፈጸምባት ገልጿል፡፡
ይህ እስራኤል ከወዳጅ አገሮች ጋር የምታራምደው አቋም ለበርካታ የኢራን ሳይንቲስቶች ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ ኢራንም፣ በቴህራን ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ፕሮፊሰር የነበሩት ማሱድ አል ሞሃማዲ፣ በኑክሌር ኢንጂነሪንግ ፋኩልቲ ፕሮፌሰር ለነበሩት ማጂድ ሻህራሪ፣ የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ምሩቁ ሙስጠፋ አህመዲንን ጨምሮ ለበርካታ ምሁራኖቿ በተጠመደ ቦምብም ሆነ በድሮን ጥቃት መገደል እስራኤልንና አሜሪካንን ተጠያቂ ታደርጋለች፡፡
ዜጎቿን ከመንጠቅ ባለፈ በተቋማትና በኑክሌር ጣቢያዎቿ ለሚያጋጥሙ የኮምፒውተር ቫይረስ ጥቃቶች እስራኤልን ትወነጅላለች፡፡
‹‹እስራኤል በርካታ ጥቃቶችን ፈጽማብኛለች፣ ለደማስቆው ጥቃት ግን አፀፋ እንሰጣለን፤›› ስትል ያስታወቀችው ኢራን፣ ጥቃቱን መፈጸሟ ለመካከለኛው ምሥራቅ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሥጋት ሆኗል፡፡
በዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት፣ በሶሪያ፣ በየመን፣ በሱዳን፣ በሊቢያ፣ በማይናማር፣ በአፍሪካ በሚገኙ አገሮች ያሉ የእርስ በርስ ጦርነቶች፣ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለው ድንገተኛ አደጋ፣ ረሃብና ድርቅ ዕልባት ሳያገኝ፣ የኢራን እስራኤል ግጭት ዓለምን ሌላ ተጨማሪ ምስቅልቅል ውስጥ የሚከታት እንደሆነም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል፡፡
ከአምስት ሰዓታት በላይ በፈጀውና 300 የሚሳኤልና የድሮን ጥቃት ያስተናገደችው እስራኤል፣ 99 በመቶው በእስራኤና አሜሪካን ጨምሮ በእስራኤል ወዳጆች ጥምረት መክሸፉን አስታውቃለች፡፡ ጥቃቱ የተሰነዘረው ከኢራን ብቻ ሳይሆን ከኢራቅ፣ ሶሪያና የመን ጭምር መሆኑን ደግሞ አሜሪካ ገልጻለች፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ዋና ቢሮ ፔንታጎን ከኢራቅ፣ ከሶሪያና ከየመን ወደ እስራኤል የተሰነዘሩ በርካታ የሚሳኤልና የድሮን ጥቃቶችን ማክሸፉንም ገልጿል፡፡
ኢራን ጥቃቱን ከመፈጸሟ ከ72 ሰዓታት አስቀድሞ ‹‹ለእስራኤል ወዳጅና ጎረቤት አገሮች ለዜጎቻቸው ማስጠንቀቂያ እንዲሰጡ አሳውቄያለሁ፤›› ብላ የሰነዘረችውን ጥቃት፣ ለመመከትም አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይና ዮርዳኖስ በጥምረት ተሳትፈዋል፡፡
ዘንድሮ በጥቅምት አጋማሽ ከፍልስጤም ጋዛ ድንገት በተሰነዘረባት የሮኬት ጥቃት 1,200 ዜጎቿ መገደላቸውን ገልጻ፣ ከፍልስጤም ጋዛ ጋር ወደ ሙሉ ጦርነት የገባችው እስራኤል፣ በጋዛው ጦርነት በፍልስጤማውያን ላይ እየደረሰ ያለውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ለመሸፈን ከኢራን ጋር መተነኳኮስ ጀምራለች በሚል የተተቸችው እስራኤል፣ በኢራን ላይ መወሰድ ስለሚገባው ዕርምጃ ከጦር አበጋዞቿ ጋር በቴልአቪቭ መክራለች፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የኢራን እስራኤል ግጭትን ተከትሎ በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ፣ እስራኤል የአፀፋ ዕርምጃ ከመውሰድ እንድትቆጠብ ቢያሳስብም፣ ከእስራኤል ወገን መቼና እንዴት የሚለው ባይገለጽም የአፀፋ ምት እንደሚኖር መነገሩን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
በውይይቱም ከጦር አበጋዞቹ ሁለቱ ለኢራን ጥቃት አፋጣኝ ምላሽ መሰጠት አለበት ማለታቸውን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኢራን ከዓለም አቀፉ መድረክ እንድትገለል የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት የሚል አማራጭ መቅረቡንም አክሏል፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ በተገኙበት የጦር አበጋዞቹ ውይይት አድርገዋል ያለው ሲኤንኤን፣ በሰዎች ላይ የሚደርስ ሞትን አስወግዶ በኢራን ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸም የሚል ሐሳብ እንደተሰነዘረና መቼና የትኛው አማራጭ በኢራን ላይ ተፈጻሚ ይሁን? የሚለው በግልጽ እንዳልታወቀ ዘግቧል፡፡
ይህንን ተከትሎ መግለጫ የሰጡት የሃያላን አገር መሪዎች፣ እስራኤል ከአፀፋ ጥቃት እንድትቆጠብ አሳስበዋል፡፡
የእንግሊዝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን አገራቸው የአፀፋ ጥቃትን እንደማትደግፍ ሲያስታውቁ፣ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ‹‹ፈረንሣይ እስራኤል የአፀፋ ዕርምጃ እንዳትወስድ የማሳመን ሥራ ትሠራለች፤›› ብለዋል፡፡ አሜሪካም የብቀላ ዕርምጃውን ከማይደግፉ አገሮች ተሠልፋለች፡፡
አሜሪካ ‹‹እስራኤል ማንኛውንም የአፀፋ ጥቃት በኢራን ላይ መፈጸም የለባትም፣ አሜሪካም የአፀፋ ጥቃትን አትደግፍም፤›› ስትልም አስታውቃለች፡፡
‹‹እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት አላት›› በሚለው አቋሟ የምትታወቀው አሜሪካ፣ በኢራን ላይ የሚወሰድ የበቀል ዕርምጃን ባትደግፍም፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እየተባባሰ ከመጣው ውጥረት እስራኤል ራሷን እንድትጠብቅ በአሜሪካ ቃል የተገባላት የ14 ቢሊዮን ዶላር የዕርዳታ ፓኬጅ በአፋጣኝ እንዲፀደቅ እየሠራች ነው፡፡
የእስራኤል አጋሮች እስራኤል የአፀፋ ዕርምጃ እንዳትወስድ ቢያሳስቡም፣ እስራኤል መቼና እንዴት የሚለውን ሳታሳውቅ በኢራን አስተማሪ የሆነ የአፀፋ ዕርምጃ ለመውሰድ መምከሯን ተከትሎ፣ እስራኤል አርፋ እንድትቀመጥ ኢራን አስጠንቅቃለች፡፡
በሶሪያ ደማስቆ በኢራን ቆንጽላ ጽሕፈት ቤት የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ኢራን እስራኤልን እንደምትመታ ቀድማ ለቀጣናው አገሮች ማስታወቋን የዘገበው ዘጋርድያን፣ እስራኤል ወይም አሜሪካ በኢራን ላይ የአፀፋ ጥቃት ከፈፀሙ፣ ኢራን ኃይሏን አጠናክራ በእስራኤል ምድር ዳግም ጥቃት የምትሰነዝር መሆኑን ማስታወቋን ገልጿል፡፡
እስራኤል ከኢራን ቀጥታ ጥቃት ከተፈጸመባት በኋላ የመጀመርያ ያለችውን ‹‹ዲፕሎማሲያዊ ጥቃት›› በኢራን ላይ ጀምራለች፡፡ አልጀዚራ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በኢራን ማዕቀብ እንዲጣል ሚኒስቴሩ ለ32 አገሮች ደብዳቤ ልኳል፡፡
በኢራን የሚሳኤል ፕሮጀክቶች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል በእስራኤል ከተጀመረው ዘመቻ ጎን ለጎን፣ የዓለም ኃያላን አገሮች የኢራን አብዮታዊ ዘብን የሽብር ድርጅት ብለው እንዲያውጁም ውይይት መጀመሩንም አስታውቋል፡፡