ልናገር አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

አንባቢ

ቀን: April 17, 2024

በአየለ ት.

የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን ጠቅላላ ጉባዔና የፀጥታ ምክር ቤቱን ላለፉት 75 ዓመታት ሲያነታርክ የኖረ በመሆኑ፣ ኃያላን መንግሥታትም በየጎራው በመሠለፍ የተፋጠጡበት ጥያቄ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። ዘንድሮ ደግሞ ከመተውም በላይ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤትን አጀንዳ ይዞ የነበረው ጉዳይ ይኼው የፍልስጤም ጉዳይ ነው። ከሃምሳዎቹ እስከ ቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ ድረስ የዓረቡ ዓለም በአንድ ጋ ሆኖ በሶሻሊስት አገሮች እየታገዘ የበርካታ የሦስተኛው ዓለም አገሮችንም ድጋፍ ይዞ የፍልስጤምን ጉዳይ በፊታውራሪነት መርቶ ነበር። ዩናይትድ ስቴትስ (በተለምዶ አሜሪካ የሚባለው) ግብፅን ‘የማልመድ’ ፖሊሲው ተሳክቶለት በእስራኤልና በግብፅ መሀል የካምፕ ዴቪድ ስምምነት ከተፈረመና የዓረቡ ዓለም መከፋፈል ከጀመረ በኋላ፣ እያንዳንዱ የዓረብ መንግሥት ተራ በተራ (ከኢራቅ፣ ሊባኖስ፣ ሶሪያና አንዳንዶች በስተቀር) ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ተፈራርሞ የዲፕሎማቲክ ግንኙነትም መሥርቷል። ይህ በተራው በፍልስጤም ሕዝብ ትግል ላይ ትልቅ አንድምታ ፈጠረ። በአጭሩ የእስራኤል መንግሥት ከካምፕ ዴቪድ በኋላ በዲፕሎማሲው ረገድ በፍልስጤሞች ላይ የበላይነት ይዞ ቆይቶ፣ የዓረቡም ዓለም “ከሃዲ” እስከ መባል ደርሶ ነበር። ድሮ ድሮ ግብፅ የሌለበት የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ሊኖር አይችልም ይባል ነበር። በእርግጥም ሳዳት ያንን የካምፕ ዴቪድ ስምምነት ከፈረመ በኋላ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የሚባል አልነበረም።

እስራኤልም “የማትበገር” ተብላ ነበር። የሚገርመው ዘንድሮ የማንም የዓረብ አገር ወታደር ሳይገባበት ከፍልስጤሞችም ሃማስ የተባለው ድርጅት ብቻውን (ረመላ የከተመው የፍልስጤሙ አስተዳደር እንኳ ሳይገባበት) ደቡብ እስራኤልን በመውረር እስራኤል እንደሚባለው ‘የማትበገር’ አለመሆኗን አሳየ። ይህ በተራው የዓረብ አገሮች ቢተባበሩ እስራኤልን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ታይቷል። ከዕብደት ባልተናነሰ እስራኤልን የሚገዛው የኔታንያሁ መንግሥትም ከናዚ ጀርመኒ በኋላ ታይቶ በማይታወቅ  ጭካኔና ግፍ (እስካሁን ድረስ) የፍልስጤምን ሰላማዊ ሕዝብ በመጨፍጨፉ በዕረቡ ዓለም የፈጠረው ቁጭት የኋላ ኋላ የዓረቡ ዓለም ተመልሶ ከፍልስጤሞች ጋር ይሠለፍ ይሆናል የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ ሰፍኗል። የኔታንያሁ ግፍ አንደኛውና ትልቁ ውጤቱ ይኸው ዓረቦችን አንድ የማድረግ የሒደት ክስተት ሆኗል። በአሁኑ ጊዜ እስራኤል ደቡብ ሊባኖስን በአየርና በድሮን እየደበደበች ነው፣ ከኢራን ጋርም ፍጥጫው ቀጥሏል። ከኢራን ጋር ጦርነት ከተጀመረ ግጭቱ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የመዝለቅ ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ የኃያላኑ ጎራ የመለየት ተግባር ሊከተል ነው ማለት ነው። ኢራን፣ ኢራቅ፣ ሶሪያና የመን ከሩሲያ ጋር ሆነው ምናልባትም በሩሲያ፣ በቻይናና በሰሜን ኮሪያ ድጋፍ በዓረቡ ወገን፣ የምዕራቡ ዓለም ደግሞ ከእስራኤል ጎን ሆነው ሊሠለፉ ነው። ይህ ከሆነ የምዕራቡ አገሮች በተለይም ፈረንሣይ፣ ጣሊያንና የስካንዲኔቪያ አገሮች በጦርነቱ ለመሠለፍ የሕዝብ ድጋፍ ላይኖራቸው ስለሚችል ወደ ጦርነቱ ላለመግባት ሲሉ ሌላ መፍትሔ ፍለጋ ሳይሄዱ አይቀሩም።

በዚህ ላይ የመላው ዓለም ሕዝብ አመለካከት በአሁኑ ጊዜ ፀረ እስራኤል እየሆነ ነው። በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚገባው ደቡብ አፍሪካ ለፍልስጤም ሕዝብ ያደረገችው ውለታ ነው። ይኼውም እስራኤልን በዘር ማጥፋት ወንጀል በዓለም ፍርድ ቤት መክሰሷ ነው። የደቡብ አፍሪካና የፍልስጤም ሕዝብ ትግሎች ያላቸው መተጋገዝ የቆየ ነው። የማንዴላ ፓርቲ የደቡብ አፍሪካ ናሽናል ኮንግሬስ አፓርታይድን ሲታገል እስራኤልን በመታገል ላይ የነበረው ፍልስጤም ነፃ አውጭ ድርጅት (PLO) ለማንዴላ ፓርቲ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጓል። ደቡብ አፍሪካም ፍልስጤምም ከአውሮፓ የፈለሱ ዘረኞች በጉልበት አገራቸውን ወስደው አገሬውን በግፍ የሚገዙበት ስለነበር ተመሳሳይነት ነበራቸው። ሌሎች አገሮችም (ለምሳሌ ኢንዶኔዥያ) የደቡብ አፍሪካን ፈለግ ተከትለው እስራኤልን በተለያዩ ወንጀሎች በዓለም ፍርድ ቤት ከሰዋል። ኮሎምቢያም በቅርቡ ጠንካራ አቋም በመያዝ እስራኤልን ከሰዋል፣ ቬኒዝዌላም እንዲሁ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ካውንስልም መንግሥታት ለእስራኤል የጦር መሣሪያ እንዳይሰጡ ወስኗል። በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች፣ በራሱ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በአውስትራሊያና በካናዳ ፀረ እስራኤል ሠልፎች አሁንም እንደቀጠሉ ነው። በመላው ዓለም ያሉ ታዋቂ ምሁራንና ሳይንቲስቶች የእስራኤልን የዘር ማጥፋት ጦርነት እያወገዙ ነው።

በሌላ በኩል በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራው የምዕራቡ ዓለምም ራሱን የቻለ ችግር አለበት። በመጪው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሙስሊሙ ኅብረተሰብና ዓረብ አሜሪካውያን ለባይደን ድምፃቸውን እንደማይሰጡ የታወቀ ሆኗል። ይህ ሌላኛውን ተወዳዳሪ ማለትም ትራምፕን የሚረዳ ቢሆንም፣ ትራምፕም በፍልስጤም ጉዳይ ከባይደን የተለየ ፖሊሲ የለውም። እንዲያውም ከባይደን የባሰ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከባድ ከባድ ችግር እያጋጠመው ነው። ትራምፕ ከተመረጠ የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ድርጅት  ከባድ ቀውስ ውስጥ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። ምክንያቱም ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስ በዓለም ላይ የምትከተለውን የበላይነት ፖሊሲ በመቀየር የሰሜን አትላንቲክ መከላከያ ድርጅቱን  (ናቶ) በጀት አባል ድርጅቶች በሙሉ በጋራ እንዲወጡት እንደሚያስፈልግ፣ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቱም ላይ ሁሉም እንዲሳተፉ ያስፈልጋል፣ ወዘተ የሚል ፖሊሲ እንደሚከተል አስታውቋል። ይህ ከሆነ ናቶ ይዳከማል፣ የምዕራቡም ጣልቃ ገብነት ይቀንሳል የሚል ግምት አለ። በእርግጥ ይህ ከሆነ በዓለም ላይ ሰላም ሊመጣ ይችላል ሊባል ይችላል። ለነገሩ ናቶ የተቋቋመው ድሮ በሶቪዬት ኅብረት የሚመራው የምሥራቅ አውሮፓ መከላከያ ድርጅት (ዋርሶው ፓክት የሚባለው) ሲቋቋም ለዚያ ምላሽ ሆኖ ስለነበር፣ አሁን የዋርሶው ፓክት በሌለበት ናቶ ለምን ያስፈልጋል ሊያሰኝ ይችላል።

ያም ሆነ ይህ ፕሬዚዳንቱ ባይደንም ሆነ ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስ በአሁኑ ጊዜ ከባድ ከባድ ቅራኔዎች ውስጥ ስለገባ የበላይነቱ እየተዳከመ መሆኑ እየታየ ነው። ዩናይትድ ስቴትስ በአሁኑ ጊዜ ከባድ ከባድ በሆኑ ጉዳዮች ተወጥሯል። በደቡብ ቻይና ባህር ከቻይና ጋር ያለው ፍጥጫ፣ በታይዋን ጉዳይም እንዲሁ፣ በዩክሬይኑ ጦርነትም ምዕራባውያን እንደ ዘበት የቀሰቀሱት ቀውስ በአሁኑ ጊዜ የሩሲያ የበላይነትን እያስከተለ ነው፣ በቀይ ባህር ሰላጤም በአንድ በኩል ከጋዛ ጦርነት ጋር በተያያዘ ከሁቲ ታጣቂዎች ጋር ተፋጧል፣ ሩሲያ ኤርትራን ይዞ በቀይ ባህር ሰላጤ ሌላ ውጥረት ውስጥ ገብቷል፣ በደቡብ አሜሪካም የፀረ ቬኒዝዌላ ዘመቻው የትም አልደረሰም፡፡ እንዲያውም ለቬኒዝዌላ አመቺ ሁኔት እየተፈጠረ ነው፣ በብራዚልም የሉላ መመረጥም አይመቸውም፣ ወዘተ፡፡ በዚህ ሁሉ ውጥረት ዩናይትድ ስቴትስ ምናልባት የመካከለኛው ጦርነት ቢነሳ እስራኤልን ለመርዳት ምን ያህል ርቀት ሊሄድ ይችላል የሚለው ጥያቄ ሊነሳ ይገባዋል። እነዚህ ሁሉ የዩናይትድ ስቴትስን መዳከም የሚያመለክቱ ሲሆኑ፣ በአሁኑ ጊዜ ባጋዛ እስራኤል የምታካሂደውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ በመደገፉ፣ በተለይም በአሜሪካ ኅብረተሰብ ዓይን ምን ያህል አሜሪካ በዚህ ዕርዳታው ሊያስኬደው ይችላል የሚለውን ጥያቄ ያስከትላል። 

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት አንድ ጉዳይ አለ። እስራኤል በጋዛ ያካሄደው የዘር ማጥፋት ዕርምጃና ከናዚ ጭካኔ የማይተናነሰውን ሥራ የፖለቲካ አንድምታውን ራሱ የዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ፣ በተለይም ምሁራን ማንሳታቸው የማይቀር ነው። ደቡብ አፍሪካ የፍልስጤምን ችግር ከራሷ የአፓርታይድ ተሞክሮ ተነስታ ያነፃፀረችውን ያህል አሜሪካኖች ራሳቸው በራሳቸው ታሪክ የአውሮፓው መጤ ፈረንጅ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ስንትና ስንት የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሞ የወንጀልና ፖሊሲ ይከተል የነበረውን ከፅዮናውያን ወንጀለኞች ፖሊሲ ጋር፡፡ ከመነሻው ላይ ካለው ተመሳሳይነት አንፃር ራሱ የአሜሪካ ኅብረተሰብ ጥያቄና ተቃውሞ ሊያስነሳ ይችላል። በአሁኑ ጊዜ ራሳቸው በትውልድ አይሁድ ከሆኑት የዓለም የምሁራን ቁንጮ ተብሎ ከሚገመተው የሃርቫርዱ ኖምቾምስኪ (Noam Chomsky) ሌላ እንደ ኖርማን ፊንከልስታይን (Norman Finkelstein) የመሳሰሉና ሌሎችም አይሁዳውያን ያልሆኑ ምሁራንና ጸሐፊዎች የእስራኤልንና የዩናይትድ ስቴትስን ፖሊሲ በመቃወም በሰፊው እየጻፉም እየተናገሩም ነው። በስድሳዎቹና ሰባዎቹ የቬትናም ጦርነት በራሱ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያስከተለውን የፖለቲካ ቀውስና ለውጥ ጋር የሚመሳሰል ሒደት በጋዛው ጦርነት ምክንያት እየተነሳ ነው። የዚህ ሒደት መድረሻውን አሁን መናገር ባይቻልም ይዋል ይደር እንጂ፣ በዩናይትድ ስቴትስና እስራኤል ፖሊሲ ላይ ግን ለውጥ ማስከተሉ የማይቀር ነው። የፍልስጤሞች ደምና ዕንባ በከንቱ አይቀርምና።

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የአሜሪካ መንግሥት ፖሊሲ ሁልጊዜ እስራኤልን እንዲደግፍ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ የሚሠሩ በርካታ ድርጅቶች አሉ። እነዚህ ድርጅቶች በአንድ የጥቅል ስም ሲጠሩ “The Israel Lobby” (የእስራኤል ጠበቆች እንደ ማለት ነው) ይባላሉ። ዋናው ጉዳይ ዩናይትድ ስቴትስ እንዲህ የእስራኤል ዋና ጠበቃ ሊሆን የበቃው እንዴት ነው የሚለው ጥያቄ መልስ የሚያገኘው የእስራኤል ሎቢን ሥራ ስንረዳ ነው። በርካታዎቹ መሰል ድርጅቶች በአይሁዶች ስም ይቋቋሙ እንጂ ዋነኛው የእስራኤል ጠበቃ ግን አይፓክ (AIPAC: American Israel Public Affairs Committee) ነው። ይህ አይፓክ ተብሎ የሚታወቀው በአሜሪካ የእስራኤል ጠበቃ የሆነው ድርጅት የተቋቋመበት ዋና ዓላማ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እስራኤልን በመደገፍ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ለማድረግ በመሆኑ፣ አይፓክ ይህንን ሥራውን ለማከናወን አያሌ ሥራዎችን ይሠራል። እነዚህ በጣም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁትን በቅጡ ለመሥራት ከዩናይትድ ስቴትስ አይሁድና ሌሎችም ሀብታሞች እጅግ ብዙ ገንዘብ በየጊዜው ይሰበስባል።  ይህ እስራኤልን ለመደገፍ ተብሎ የተቋቋመው ድርጅት በአሁኑ ጊዜ እጅግ ኃይል ከማካበቱም በላይ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የሕዝብ ምክር ቤቱንና የሴኔቱን (ኮንግረሱን ማለት ነው) አባላት (ከ535 የኮንግሬሱ አባላት 342 ያህሉ በገንዘብ ኃይል ጠርንፎ ይቆጣጠራቸዋል)፣ እንዲሁም በራሱ በመንግሥቱ ውስጥ ያሉትን ክፍሎች (ነጩን ቤተ መንግሥት (White House) ስቴት ዲፓርትመንት፣ ወዘተ.) ይቆጣጠራል፡፡ አይፓክ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በየትኛውም የመንግሥት ደረጃ (ከንቲባዎችንና የከተሞች መማክርት ቤቶችን ጭምር) ያሉ ፖለቲከኞች በምርጫ ውድድር ወቅት ከፍተኛ የገንዘብ ዕርዳታ በማድረግ በመልሱ እነዚህ ፖለቲከኞች ዘወትር እስራኤልን የሚደግፍ ፖሊሲ እንዲከተሉ/እንዲደግፉ ያደርጋል። በዚህ ረገድ ሂላሪ ክሊንተንን ይዞ ሌሎቹንም ለፕሬዚዳንትነት የተወዳደሩትን ሁሉ በከፍተኛ የገንዘብ ክፍያ ጠፍግጎ ይዟቸዋል። ባለፈው ሳምንት የወጣ አዲስ መረጃ እንደሚያመለክተው ባይደን ራሱ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ከአይፓክ እንደተከፈለው ነው።

ከዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲከኞች በአይፓክ ገንዘብ ያልተጠመደ የአሜሪካ መሪ ቢኖር ጂሚ ካርተር ብቻ ነው። በዚህም ጂሚ ካርተርም በነጩ ቤተ መንግሥት ከአንድ ተርም በላይ እንዳይቀመጥ ተደርጓል። እስካሁን በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ በፍልስጤም ጥያቄ ላይ ሀቀኛ ፖሊሲ ይከተል የነበረው ጂሚ ካርተር ነው። ጂሚ ካርተር የአሜሪካ የፖለቲካ ሥርዓት እንዴት አላፈናፍን እንዳለው ብዙ ጊዜ ቢናገርም “Palestine: Peace not Apartheid” የተሰኘው መጽሐፉ ግን ከአንድ የአሜሪካ ፖለቲከኛ በማይጠበቅ ሀቀኝነት ብዙ ነገር ዘርዝሯል።

ሌሎች አይፓክ የሚቆጣጠራቸው ደግሞ ታላላቅ የዩናይትድ ስቴትስ የሚዲያ አውታሮችን (የቴሌቪዥንና የጋዜጣ ድርጅቶችን) ነው። እነዚህን ታላላቅ የሚዲያ አውታሮች አይፓክ በገንዘብ ኃይል ጠፍንኖ  ይዟቸዋል። እንደ አንቶኒ ሉዊስ (Anthony Lewis) ያለ ራሱ አይሁዳዊ የሆነ ግን ለሀቅ ቆሞ በቅጡ ይዘግቡ ከነበሩት ጥቂት ጋዜጠኞች በስተቀር የአሜሪካ ሚዲያ ሲባል መሳ በመሳ በአይፓክ ገንዘብ የተጠረነፈ ነው ማለት ይቻላል። በዚህ ምክንያት አሜሪካኖች ስለመካከለኛው ምሥራቅ እውነተኛውን ዜና ለማግኘት የውጭ የዜና አውታሮትን መከታተል ይኖርባቸዋል። ይህንን ራሱን አሜሪካ ውስጥ ለማድረግ በጣም ከባድ ነው። ምክንያቱም የአሜሪካ ኅብረተሰብ የውጭ አገር የሚዲያ አውታሮችን መከታተል አይችልም ነበር። እንዲያውም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አሜሪካ ውስጥ ሾርት ዌቭ (Short Wave) ሬዲዮ ማግኘት አይቻልም ነበር። በአንፃሩ የአሜሪካ መንግሥት የራሱ ሕዝብ የሌላ አገር ሚዲያ ሥርጭት እንዳይከታተል እያደረገ ራሱ ግን በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሬዲዮ ጣቢያዎች (ለምሳሌ ምሥራቅ አውሮፓ፣ ደቡብ አሜሪካ፣ ወዘተ) ሥርጭቶች ነበሩት። ከሚዲያ በላይ አይፓክ የተለያዩ ሥራ ያላቸውን የምርምር ድርጅቶችን (Think Tanks) ፈጥሮ በተለያዩ ጊዜያት “በጥናት ላይ የተመሠረተ” ማስረጃዎችን እያወጣ በሚቆጣጠራቸው የሚዲያ አውታሮች ያሠራጫል። እነዚህ ሁሉ የአሜሪካ ሕዝብ አፍዝ አደንግዝ በሆነ ፕሮፓጋንዳ ተወጥሮ የእስራኤል ደጋፊ እንዲሆን ቢደረግም፣ አሁን እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በፍልስጤም ሕዝብ ላይ የሚያካሂደውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ግን ሕዝቡ በሰፊው እየተቃወመው ይገኛል።

አይፓክ በአሜሪካ ፖለቲከኞችና ሚዲያ እየታገዘ ታሪክን በማፋለስ፣ የኦስሎ ስምምነቱን ራሳቸው እስራኤሎች (ኢሁድ ባራክ በኦስሎ የካምፕ ዴቪድ ድርድር) ማፍረሳቸው ሳያንስ ፍርጃውን በያሲር አራፋት ላይ በማላከክ፣ የፍልስጤም ታጋዮችን እንደ አሸባሪ በመፈረጅ በመላው ዓለም በፍልስጤም ሕዝብ ላይ ያካሂድ የነበረው የሐሰት ዘመቻ አሁን እየፈራረሰ ነው። ራሳቸው ከአይሁድ ቤተሰብ ሆነው ግን ለፍልስጤም ሕዝብ ተቆርቋሪ ሆነው ከቆሙት መሀል የዓለም ምሁራን ቁንጮ ተብሎ የሚገመተው የሃርቫርዱ ኖም ቾምስኪ (Noam Chomsky)፣ እንዲሁም እንደ ኖርማን ፊንከልስታይን (Norman Finkelstein) ያሉ በርካታ የአሜሪካ ምሁራን፣ በተጨማሪም ከእስራኤልም ጭምር በርካታ ምሁራን፣ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች በአሁኑ ጊዜ የእስራኤል መንግሥትን ግፍ እያጋለጡ ነው።

የእስራኤል ሕዝብ ራሱ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አሁን ራሱን ከኔታንያሁ መንግሥት እያራቀ፣ ለጦርነቱም መጀመር መንግሥቱን እየከሰሰ ነው። ምንም እንኳን የእስራኤል መንግሥትና ደጋፊዎቹ የአሁኑ ጦርነት ‹‹ኖቤምበር 7 በሃማስ የተጀመረ ነው›› እያሉ ቢያናፉም፣ የኔታንያሁ መንግሥት ከሃማስ ጋር ጦርነት ለመጀመር ሁለት ዓመት ሙሉ ሲተነኩስ ነበር። በዚሁ ሁለት ዓመት ውስጥ ሰላማዊ ሠልፍ ባደረጉ የፍልስጤም ወጣቶች ላይ የእስራኤል ወታደሮች ወደ 400 የሚጠጉ የፍልስጤም ወጣቶችን ገድለዋል። የኔታንያሁ ትንኮሳ ሃማስን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማጥፋት መላ ጋዛን ጠቅልሎ የእስራኤል ግዛት ለማድረግ፣ ብሎም ጎላን ሃይትስን ከሶሪያ፣ ደቡብ ሊባኖስን ከሊባኖስ ጠቅልሎ ለመያዝ ነበር። ይህ ከተሳካ ያንን የጥንቱን የጠዋቱን የፅዮናውያን የግዛት ማስፋፋት ዓላማ ያሳካው ኔታንያሁ ነው እንዲባል ነው። ይሁን እንጂ አንድ ታላቅ ፈላስፋ ገና ድሮ እንዳለው ሰዎች ታሪክን እንዳሻቸው ሊሠሩ አይችሉም።

በዓለም አቀፍ ደረጃም እስራኤል ይበልጥ ተቃውሞ እየገጠመው ነው። በተለያዩ የዓለም አቀፍ ጉባዔዎች እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል እያወገዙ ነው። በተለያዩ ክፍለ ዓለማትና አገሮች ፀረ እስራኤል ሠልፎች አሁንም እየተካሄዱ ነው። ደቡብ አፍሪካ እስራኤልን በዘር ማጥፋት ወንጀል በዓለም ፍርድ ቤት ከሳለች፣ ኢንዶኔዥያ እስራኤልን እንዲሁ በሌላ ወንጀል ክስ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ከሳለች፣ ቬኒዙዌላና ሌላም አገር እንዲሁ ክስ መሥርተዋል። አሁን በቅርቡ ደግሞ ኒካራጓ ጀርመን እስራኤል ለምታካሂደው የዘር ማጥፋት ዘመቻ መሣሪያ ሰጥታለች በማለት በዓለም ፍርድ ቤት ከሳለች። ይህ ክስ አንድምታው በተለይም በራሱ በጀርመን ውስጥ ከፍተኛ እንደሚሆን ይገመታል። ከሁሉ የሚገርመው ግን ይኼ ሁሉ ግፍና ጭፍጭፋ በፍልስጤም ሕዝብ ላይ ሲካሄድ እኛ የየካቲት 12 ተጨፍጫፊዎች ምንም አለማለታችን ነው። የምዕራቡ ዓለም በሰሜኑ ጦርነት ወያኔን በመደገፉ ኢትዮጵያ ምን ያህል የዓለም አቀፍ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት የተንገበገበውን ያህል፣ አሁን ደግሞ ተመሳሳይ ድጋፍ ለሚፈልገው የፍልስጤም ምንም ድጋፍ አለመግለጻችን የታሪክ ምፀት ነው፣ ያሳዝናልም።

(በዚህ ጉዳይ ይበልጥ ንባብ ለማድረግ ለሚፈልጉ አንባብያን የሚሆን ዋቢ፦ ፩- The Israel Lobby by John Mearsheimer and Stephen Walt, 2- The Other Israel, Voices of Refusal and Dissent, ed. Roane Carey and Jonathan Shainin)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡