

ዜና የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ወደ ሦስት ሺሕ የሚጠጉ አቤቱታዎች እንደገና መቅረብ እንዳለባቸው…
ቀን: April 17, 2024
- የተሻሻለው አዋጅ ኅትመት መዘግየት በቀረቡ አቤቱታዎች ብዛት ላይ ጫና ፈጥሯል ተብሏል
የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የተሻሻለው የማቋቋሚያ አዋጅ ከመፅደቁ በፊት፣ በትልልቅ የግል ተቋማት ላይ የቀረቡ ወደ ሦስት ሺሕ የሚጠጉ አቤቱታዎች እንደገና መቅረብ እንዳለባቸው አስታወቀ፡፡
ኅዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1307/2016፣ ‹በትልልቅ የግል ተቋማት› ማለትም በሽርክና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና በአክሲዮን በተቋቋሙ የግል ተቋማት ውስጥ ከአስተዳደር በደል ጋር የተያያዙ አቤቱታዎችን መቀበልና ምርመራ በማካሄድ የመፍትሔ ሐሳብ የመስጠት ኃላፊነትና ሥልጣን ተሰጥቶታል።
ፓርላማው አዋጁን አሻሽሎ ካፀደቀ አራት ወራት ቢያልፉም በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በመውጣት ተግባር ላይ የዋለው ግን በመጋቢት ወር አጋማሽ መሆኑን፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሕግና አስተዳደር ዘርፍ ምርመራ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ ቀኜ ለሪፖርተር አስረድተዋል።
‹‹አዋጁ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከታተመ አንድ ወር ቢሆነው ነው። ከዚያ በኋላ የተቀበልነው በግል ተቋማት ላይ የቀረበ አቤቱታ በጣም ትንሽ ነው፤›› ብለዋል። ባለፈው አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ተቋሙ በግል ተቋማት ላይ የቀረቡለት አቤቱታዎች ከአምስት እንደማያልፉም መሪ ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
አቶ መንግሥቱ ለአቤቱታዎቹ መጠን ማነስ ሁለት ምክንያቶችን አስቀምጠዋል። ‹‹አቤቱታዎች በብዛት ያልመጡት አንደኛ አዋጁ ለመታተም የወሰደው ጊዜ ቆይታ ነው። ሁለተኛ ደግሞ በማኅበረሰቡ ዘንድ ይህንን አገልግሎት መስጠት መጀመራችንን በተመለከተ ግንዛቤው ምንም የለም በሚባል ደረጃ መሆኑ ነው። እነዚህ ተደምረው የቀረቡት አቤቱታዎች በምንጠብቀው ደረጃ አይደለም፤›› ሲሉ ተናግረዋል።
መሪ ሥራ አስፈጻሚው በተጨማሪም፣ ‹‹ምክር ቤት ፀደቀ ማለት ሕጉ ሥራ ላይ ዋለ ማለት አይደለም። ወደ ብርሃንና ሰላም ለኅትመት ይሄዳል። እሱን ደግሞ እኛ አይደለንም የምናደርገው ምክር ቤቱ ነው። እሱን ብቻ ሳይሆን ድሮ እኛ በመንግሥት ተቋማት ላይ ብቻ ነው አቤቱታ የምናየው፣ አሁንም ያለው ግንዛቤ ይህ ነው። እዚህ ላይ የማስተዋወቅና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ለማከናወን አዋጁ ታትሞ መውጣቱ ወሳኝ ነበር፤›› ብለዋል።
የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር) ባለፈው ወር ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በግል ተቋማት ላይ እስካሁን ምን ያህል ቅሬታዎች ቀርበዋል የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በየዓመቱ በአማካይ ወደ ስድስት ሺሕ አቤቱታዎችን እንቀበላለን። ስድስት ሺሕ ስል ከ40 እስከ 50 ሺሕ ዜጎችን የሚይዙ ጉዳዮች ናቸው የሚቀርቡት። ከእነዚህ ውስጥ ሦስት ሺሕ አካባቢ በተቋሙ ሥልጣን ሥር የማይወድቁ ነበሩ። ከሦስት ሺሕ ውስጥ ደግሞ አብዛኛው ከግል ተቋማት የሚመጡ ጉዳዮች ስለነበሩ፣ ይኼ የዕንባ ጠባቂ ተቋምን አይመለከትም ወይም ከተቋሙ ሥልጣን ገደብ ውጪ ነው ብለን የምንመልሰው ነበር፤›› የሚል ማብራሪያ ሰጥተው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ሪፖርተር ከአዋጁ መሻሻል በፊት የቀረቡ ወደ ሦስት ሺሕ የሚጠጉ በግል ተቋማት ላይ የቀረቡ አቤቱታዎችን አስመልክቶ ምን ዓይነት አሠራር ለመከተል እንደተወሰነ ለተቋሙ የሕግና አስተዳደር ዘርፍ ምርመራ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ላቀረበው ጥያቄ፣ አቤቱታዎቹ በድጋሚ መቅረብ እንደሚኖርባቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የዕንባ ጠባቂ ተቋም በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን የአስተዳደር በደሎችን በራስ ተነሳሽነት፣ እንዲሁም በሥልታዊ መንገድ ምርመራ የማካሄድ ሥልጣን ቢኖረውም እነዚህን ግን አዋጁ ከመሻሻሉ በፊት የቀረቡ አቤቱታዎችን ለመመርመር መጠቀም እንደማይችልም አቶ መንግሥቱ አስረድተዋል።
‹‹አዋጁ ከመሻሻሉ በፊት በግል ተቋማት ላይ የቀረቡ አቤቱታዎች በድጋሚ ካልቀረቡ በስተቀር፣ ምርመራ ልናካሂድባቸው የሚያስችለን ሕግም ሆነ አሠራር የለም፤›› ብለዋል።
አሁን ለታየው የግል ተቋማት ላይ አቤቱታ አቅራቢ ዜጎች መጠን ማነስ ከአዋጁ ለኅትመት መዘግየትና ግንዛቤ ማነስ በተጨማሪ፣ የተቋሙ የነፃ የስልክ ጥሪ መስመር ለሰባት ወራት ያህል ተዘግቶ መቆየት የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለውም ተናግረዋል።
ተቋሙ የ2016 በጀት ዓመት በስድስት ወራት የተከናወኑ ሥራዎችን በሥራ አስፈጻሚዎቹ ባስገመገመበት ወቅት፣ እስከ በጀት ዓመቱ አጋማሽ በ938 አቤቱታዎች ሥር 19,590 ሰዎች የአስተዳደር በደል ተፈጽሞብናል በማለት ለተቋሙ አቤቱታቸውን ወይም ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን ያስታወቀ ሲሆን፣ የአቤቱታው መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ መቀነሱ ተገልጾ ነበር።
የአቤቱታዎች ብዛት ሊቀንስ የቻለውም በተለይ በዋናው መሥሪያ ቤት 7502 ነፃ የጥሪ ማዕከል በተፈጠረ የቴክኒክ ችግር አገልግሎት መስጠት በማቋረጡ፣ እንዲሁም በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶችና አለመረጋገት ምክንያት ቅሬታ አቅራቢዎች ወደ ተቋሙ እየመጡ ባለመሆኑ የሚል ማብራሪያዎች ተሰጥተውበት እንደነበርም የሚታወስ ነው።
አቶ መንግሥቱ፣ ‹‹የጥሪ መስመሩ ከመጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ ነው ቁጥሩን ወደ 9503 በመቀየር ነው በድጋሚ ሥራ የጀመረው፡፡ ከዚህ ጋር የግንዛቤ መፍጠር ሥራ ስናክልበት የአቤቱታ አቅራቢዎች በመጪው ወራት ውስጥ ከፍ ይላል ብለን እንጠብቃለን፤›› ብለዋል።
የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂው በመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም. ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ ድርጅቶች፣ የአበባ እርሻዎችና ፋብሪካዎች አቤቱታ ከሚቀርብባቸው የግል ተቋማት ተጠቃሾች መሆናቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም።