

ዜና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከለጋሾች የሚያገኙት ገንዘብ የታክስ ሥርዓቱን እንዲከተል መመርያ ተዘጋጀ
ቀን: April 17, 2024
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከለጋሾች የሚያገኙት ገንዘብ የታክስ ሥርዓቱን ካልተከተለ ምርመራ እንደሚደረግበት፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን መመርያ ተዘጋጀ፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በተመዘገቡበት ዓላማ መሠረት ሥራቸውን ማከናወናቸውን ለመከታተል፣ ለመቆጣጠርና ምርመራ ለማድረግ የሚያስችል መመርያ ነው የተዘጋጀው፡፡ በመመርያው መሠረት ከለጋሾች የሚገኝ ገንዘብ ታክስ ካልተደረገ፣ በሕጋዊነቱ ላይ ምርመራ ለማድረግ ለባለሥልጣኑ ኃላፊነት ተሰጥቷል፡፡
በመመርያው ውስጥ የተጠቀሰውን ጉዳይ በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት (NGO) ኃላፊ፣ ታክስ መክፈል የዜግነት ግዴታ መሆኑንና ለመንግሥትም ዋና የገቢ ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የታክስ ሥርዓቱ ፍትሐዊ መሆን እንዳለበት ተናግረው፣ ዜጎችም በሥርዓቱ መክፈል አለባቸው ብለዋል።
ለትርፍ ያልተቋቋሙና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የገቢ ታክስ ቢከፍሉም፣ ትርፍ ስለማያገኙ የትርፍ ታክስ የመክፈል ግዴታ ሊጫንባቸው እንደማይገባ አስረድተዋል፡፡
በመመርያው ውስጥ ከተጠቀሱ ሌሎች ጉዳዮች መካከል በአንድ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት የሚንቀሳቀስ ገንዘብ በፋይናንስና በግዥ ሥርዓት መሠረት እንደሆነ ከተረጋገጠ፣ የሠራተኞች አስተዳደር የአሠራር ችግሮች ካሉ፣ ሕግ በሚጣስበት ወቅት መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል ሥርዓት ከሌለና የሚገኙ ገንዘቦች ሕገወጥ መሆናቸው ካጠራጠረ ክትትል ሊደረግ ይችላል የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
ሕገወጥ የሆኑ ድርጊቶችን መፈጸም፣ በባለሥልጣኑ የማይታወቅ የባንክ አካውንት መክፈትና መጠቀም፣ የድርጅት የሒሳብ እንቅስቃሴን በግለሰብ ስም ማንቀሳቀስ፣ የውጭ ዜጎችን አግባብ ያለው የሥራ ፈቃድ ሳይዙ በድርጅቱ ማሠራት፣ ከዕቃ ግዥና ንብረት አስተዳደርና ንብረት ማስተላለፍ ጋር የተያያዙ ሕገወጥ አሠራሮች በሚኖሩበት ጊዜ ምርመራ እንደሚደረግ በመመርያው ተጠቅሷል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ድርጅቶቹ ሥራቸውን በሕግ አግባብ ማከናወናቸውን ማረጋገጥ፣ በሚደርሰው ጥቆማ መሠረት ምርመራ ማድረግ፣ ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ ሕገወጥ ድርጊት ከተፈጸመ ምርመራ በማካሄድ ማስተካከያዎች እንዲረጉ መመርያው ያብራራል፡፡
የድርጅቶቹ ዓመታዊ የሥራ እንቅስቃሴ፣ የኦዲት ሪፖርት፣ የፕሮጀክት ሰነዶችና ስምምነቶች፣ ከድርጅቱ፣ ከመንግሥት፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከሦስተኛ ወገኖች በተለያዩ መንገዶች የሚገኙ ሰነዶችና መረጃዎች ላይ የክትትል ሥራ ማከናወን እንደሚቻል በመመርያው ተካቷል፡፡
የክትትል ሥራ በሚከናወንበት ወቅት የሚመለከታቸውን አመራሮችና ሠራተኞች ሐሳባቸውን በነፃነት እንዲገልጹ ማድረግ፣ እንዲሁም የድርጅቶቹን የሥራ እንቅስቃሴ ሳያስተጓጉል መካሄድ አለበት ሲል መመርያው ያብራራል።
በምርመራ ወቅት መወሰድ የሚገባቸው የጥንቃቄ ዕርምጃዎችና መርማሪው ሊከተላቸው ስለሚገባ ሥነ ምግባር በመመርያው የተመለከተ ሲሆን፣ በድርጅት ላይ በተደረገ ምርምራ ሕጎች ከተጣሱ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር የእርምት ዕርምጃ እንዲወስድ፣ ወይም በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የታየውን ጉድለት እንዲያስተካክል ለድርጅቱ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጠጥ መመርያው ዘርዝሯል፡፡
በተሰጠው ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መሠረት ድርጅቱ አሠራሩን የማያስተካክል ከሆነ፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር የዕገዳ ውሳኔ ማስተላለፍ እንደሚችል ተገልጿል።
የመመርያውን አዘገጃጀትና ሒደት ለማወቅ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ባለሥልጣን ለማነጋገር የተደረገው ጥረት፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊ ሊገኙ ባለመቻላቸው ምክንያት አልተሳካም።