ማኅበራዊ
በዘመናዊ ዕውቀት መታገዝ የሚሻው የማዕድን አወጣጥ

አበበ ፍቅር

ቀን: April 17, 2024

በቴክኖሎጂው የተራቀቁ አገሮች በአፍሪካ ምድር ያሉ ከርካሽ የሰው ጉልበት እስከ የተፈጥሮ ሀብት ለመቀራመት ሲፈልጉ በድርድር  ካልሆነ ደግሞ በብድር  እጅና እግራቸውን በመጠፍነግ ያሻቸውን ጥሬ ሀብት እየዛቁ ለፋብሪካቸው ግብዓት ሲያጓጉዙ ኖረዋል።

በተለይ ደግሞ አሁን ላይ እየደረሱበት ላለው የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ትልቁ ግብዓታቸው በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ የከበሩ ማዕድናት ስለመሆናቸው ከእነሱ በላይ ምስክርነት አይሻም።

ለአብነት ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በዓለም ከፍተኛውን የኮባልት ማዕድን የምታቀረብ ስትሆን፣ ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳና ሞዛምቢክ ደግሞ በዓለም የታንትለም ማዕድን ምርት  ሀብት አላቸው፡፡ አብዛኛው መገኛቸው የአፍሪካ አገሮች የሆኑት እነዚህ ማዕድናትም፣ ለዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ ዘርፍ እጅግ አስፈላጊ ከሚባሉት ንጥረ ነገሮች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

አኅጉሪቱ ከእነዚህ ጠቃሚ ማዕድናት በተጨማሪ በዓለም እጅግ  ተፈላጊነታቸው የጨመረው የፕላቲኒየምና ፓላዲየም ማዕድናት ዋነኛዋ መገኛ ስትሆን፣ እነዚህ የብረት ማዕድናትም ለታዳሽ ኃይል ልማትና ለኤሌክትሪክ መኪኖች ማምረቻ እጅግ ወሳኝ ናቸው፡፡

አፍሪካ በከበሩ ማዕድናት የከበረች ብትሆንም፣ በችግርና በረሃብ እየተገረፉ ለሚገኙ ዜጎቷ ጠብ ነገር የለም። ኢትዮጵያም የአፍሪካ ክፋይ እንደ መሆኗ በውስጧ ብዙ ዓይነት ማዕድናት ቢኖራትም፣ ለችግሯ አልደረሰላትም፡፡ 

ኦፓል፣ ኤምራልድ፣ ሩቢ፣ ሳፋየር፣ አኳመሪን፣ ቶርመሪን፣ አማዞናይት፣ ኳርትዝና ሌሎች ኢትዮጵያ አሏት ከሚባሉት የከበሩ ማዕድናት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ማዕድናት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚገኙም መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ማዕድናቷን ያደጉ አገሮች ጥቅም ላይ ከሚያውሉበት፣ ራሷም ልትጠቀምበት ከሚያስችል ደረጃ አላደረሰቻቸውም። ለዚህ ደግሞ በዘርፉ ላይ  ጥልቅ የሆነ ዕውቀት ያለው ባለሙያ በበቂ ሁኔታ አለመኖር፣ ለምርምሮች የሚቀርብ በጀት ማነስ እንዲሁም ማዕድናቱ የሚገኙበትን ቦታ ለመለየትና  በአግባቡ አውጥቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚረዱ መሣሪያዎች  አለመኖር  ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው።

በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሚገኙ ማዕድናት  ከተቀበሩበት ገና  አልወጡም ብሎ ለመናገር  ያስደፍራል። እየወጡ ያሉት ጥቂት ማዕድናትም፣ እጅግ አድካሚና ብዙዎችን ለሞትና ለአካል ጉዳት በሚዳርግ ባህላዊ ዘዴ የሚከናወኑ ናቸው።

በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ኦፓል የተባለውን ማዕድን ለማውጣት ዋሻ ውስጥ የነበሩ 20 ሰዎች በነበሩበት ተቀብረው መቅረታቸው  የቅርብ ትውስታ ነው፡፡ በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶችም ኢትዮጵያ በከርሰ ምድሯ ከያዘቻቸው የከበሩ ማዕድናት ውስጥ አሥር በመቶ የሚሆኘውን ብቻ በባህላዊ መንገድ በማውጣት  እንደተጠቀመች ኢጂሲ ግሎባል ትሬድንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር  አመልክቷል።

ማኅበሩ የማዕድናት አወጣጥና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ሰዎችንና ድርጅቶችን በማሰባሰብ በዘርፉ በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ እንደሚሠራ የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይትባረክ ነጋ ተናግረዋል።

ድርጅቱ ቅዳሜ መጋቢት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ለአራተኛ ዙር ያሠለጠናቸውን  ከ80 በላይ የዘርፉ ተዋንያን አስመርቋል፡፡ የከበሩ ማዕድናትን በማውጣት ረገድ ትኩረት ተሰጥቶ ብዙ ስላልተሠራበት በዘርፉ ላይ ዕውቀቱ ያላቸውን ሰዎች ፈልጎ ማግኘት አስቸጋሪ ነው ያሉት አቶ ይትባረክ፣ በመሆኑም በዘርፉ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግና  ውጤታማ ሥራን ለመሥራት እንደ አገር አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ ይትባረክ፣ በማዕድን ዘርፉ ያለውን ዕምቅ ሀብት በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ፣ ከችግር መውጣት አልተቻለም፡፡ 90 በመቶ የሚሆነውን የማዕድን ሀብት የሚጠቀሙትም የውጭ ባለሀብቶች ናቸው፡፡

ቀሪዋን አሥር በመቶ  በማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩት ደግሞ የአገር ውስጥ ማዕድን አውጭዎች ናቸው።

ግንዛቤው ያላቸው ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ወደ ዘርፉ ለመግባት ይፈራሉ ያሉት አቶ ይትባረክ፣ ችግሩን  ለመቅረፍና ለማቃለል እንዲሁም አገሪቱን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ የከበሩ ማዕድናትን በማውጣት ሥራ የተሰማሩና በሌሎች ዘርፎች ያሉ ሰዎችን አሠልጥኖ  ወደ ዘርፉ ማስገባት ተገቢ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

በባህላዊ መንገድ የሚወጡ ማዕድናት ተጓዳኝ ችግሮችን ከማስተናገድም በላይ   በመስኩ ለተሰማሩ ሰዎች የሚሰጠው ጥቅም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፣ እነዚህ ሰዎች በሠሩት ልክ እንዲጠቀሙና አገሪቱም የሚገባትን እንድታገኝ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች  እንዲሠለጥኑና በቂ ዕውቀት እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነም ያክላሉ፡፡

‹‹የማዕድን ቁፋሮ እንደ ሌሎች ዘርፎች በሳይንስ ተደግፎ የተሠራበት ዘርፍ አይደለም፤››  ያሉት አቶ  ይትባረክ፣ ይህ ለምን ሆነ ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ዜጎችም በብዙ የአፍሪካ አገሮች እንዳደረጉት በቅኝ ግዛት  ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ቴክኖሎጂን በመጠቅም ማዕድናትን የመዝረፍ ዕድሉን ባለማግኘታቸው ዛሬም ድረስ ያልተበሉና የከበሩ ማዕድናት  መኖራቸው ባያጠራጥርም፣  በዚሁ ልክ አውጥቶ የመጠቀም ደረጃ ላይ አለመደረሱን አመላክተዋል፡፡

ሳይንስና ቴክኖሎጂ የደረሰባቸው የከበሩ ማዕድናት ማውጫ ማሽነሪዎች  ተሳትፈውበት ሳይሆን፣ በባህላዊ  መንገድ  እየተመረቱ መሆኑ፣ አገርን ቀርቶ  በዘርፉ ተሰማርተው የሚሠሩትን ተጠቃሚ አያደርግም፣  ይህንን  ክፍተት ለመሙላት በባህላዊ መንገድ የሚያወጡ ሰዎችንና  በዘርፉ መሳተፍ የሚፈልጉ አካላትን ሥራ በዕውቀት የተመረኮዘ በማድረግ የበለጠ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ማስቻል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡