አቡነ ማር ማሪ ኢማኑኤል
የምስሉ መግለጫ,አቡነ ማር ማሪ ኢማኑኤል

ከ 4 ሰአት በፊት

ባለፈው ሰኞ በአውስትራሊያ ሲድኒ ከተማ በቀጥታ በሚተላለፍ ሰብከት ላይ ሳሉ በስለት ጥቃት የደረሰባቸው አቡነ ማር ማሪ ኢማኑኤል በፍጥነት እያገገሙ እንደሆነ ገልጸው፣ ጥቃቱን እንዳደረሰ ለተጠረጠረው ግለሰብም ይቅርታ እንዳደረጉ ተናግረዋል።

ጳጳሱ በተቀረጸ ድምጽ ባስተላለፉት መልዕክት ኅብረተሰቡ እንዲረጋጋም ጥሪ አቅርበዋል።

በዚህ ሳምንት መግቢያ ላይ በተፈጸመው ጥቃት አራት ሰዎች ተጎድተዋል። ፖሊስ ጥቃቱ ሃይማኖታዊ መነሻ ያለው የሽብር ድርጊት ነው ብሏል።

ከክስተቱ በኋላ ጳጳሱ በሚያገለግሉበት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ሁከት ተፈጥሮ ነበር።

ጥቃቱን እንዳደረሰ የተጠረጠረ እና ራሱም የተጎዳው የ16 ዓመት ታዳጊ በቁጥጥር ስር የዋለ ቢሆንም፤ እስካሁን ክስ አልተመሠረተበትም። ባለሥልጣናት የታዳጊውን እምነት ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

ታዳጊው በአረብኛ ሲጮህ እና “ነብዩ” የሚልበትን ቪዲዮ የአገሪቱ የስለላ ቢሮ እየመረመረው እንደሆነ የተቋሙ ኃላፊ ተናግረዋል።

አራት ደቂቃ ርዝማኔ ባለው እና በቤተክርስቲያኑ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጨው ድምጽ ላይ ጳጳሱ “ማንም ይሁን ማን” ይህንን ላደረገው ግለሰብ ይቅርታ አድርጌያለሁ ሲሉ ይደመጣሉ።

“እናም ለአንተ ሁልጊዜ እጸልያለሁ። ይህንን እንድታደርግ የላኩህ ማንም ይሁኑ ማን በኃያሉ ኢየሱስ ስም ይቅርታ አድርጌላቸዋለሁ” ብለዋል።

ጨምረውም በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ እና ስላሉበት ሁኔታ ሰዎች ሊጨነቁ እንዲሁም ሊያስቡ እንደማይገባ ተናግረዋል።

ፖሊስ የኦርቶዶክስ ጳጳሱ ከዚያ ጥቃት መትረፋቸው ዕድለኛ ያስብላቸዋል ብሎ ነበር።

ይህ እጅግ አሰቃቂ የጥቃት ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ከተሠራጨ እና ሁከት ካስከተለ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ቤተክርስቲያኑ ተጉዘዋል።

በተፈጠረው አለመረጋጋት ሁለት የፖሊስ መኮንኖች የተጎዱ ሲሆን፣ 10 የፖሊስ ተሽከርካሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። የአደጋ ጊዜ የጤና ባለሙያዎችም ለደኅንነታቸው ሲፈሩ ታይቷል።

ፖሊስ በዚህ ሁከት ላይ የተሳተፉትን ተከታትሎ ለፍርድ እንደሚያቀርባቸው ቃል ገብቷል።

ትላንት ረቡዕ ምሽት ከክስተቱ ጋር በተገናኘ አንድ የ19 ዓመት ወጣት ለመጀመሪያ ጊዜ በቁጥጥር ስር አውለዋል።

በከተማዋ ከፍተኛ ስጋት ያንዣበብ ሲሆን፣ ባለሥልጣናት እና ዜጎች ተመሳሳይ ጥቃት ይከሰታል የሚል ስጋት ውስጥ ናቸው።

ጳጳሱ በመልዕክታቸው ዜጎች ከፖሊስ ጋር እንዲተባበሩም ጠይቀዋል።

“የክርስቶስን ተግባር እንድትፈጽሙ እፈልጋለሁ። ጌታችን ክርስቶስ እንድንጣላ በፍጹም አላስተማረንም። መጥፎ ሥራ እንድንሠራም አላስተማረንም” ብለዋል።