የጀርመን ሰንደቅ ዓላማ

18 ሚያዚያ 2024, 12:36 EAT

ጀርመን ለዩክሬን የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ ለማደናቀፍ ሲያሴሩ ነበር የተባሉ በስለላ የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ደቡባዊ ግዛቷ ባቫሪያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋሉ።

የጀርመን ዐቃቤ ሕግ እንዳስታወቀው የጀርመን እና የሩሲያ ጥምር ዜግነት ያላቸው ሁለቱ ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ለሩሲያ እየሰለሉ ነው በሚል ጥርጣሬ ነው።

ከሁለቱ ተጠርጣሪዎች መካከል አንዱ የሆነው የ39 ዓመቱ ግለሰብ የፈንጂ እና የእሳት ቃጠሎ ጥቃትን ለመፈጸም እንዲሁም ከሩሲያ የስለላ ተቋም ጋር ግንኙነት በመፍጠር እና በወረራ በተያዘው ምሥራቃዊ ዩክሬን ውስጥ ለሩሲያ ቅጥረኛ ቡድን ተሰልፎ ተዋግቷል በሚል ተከሷል።

ሁለተኛው ተጠርጣሪ ደግሞ ለአንደኛው ተባባሪ በመሆን ጥቃት ሊፈጸምባቸው የሚችሉ ዒላማዎችን ባለፈው ወር በመጠቆም አግዞታል ተብሏል። ዛሬ ሐሙስ ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ ለዩክሬን ከፍተኛውን ወታደራዊ ድጋፍ በማቅረብ ጀርመን አሜሪካንን ተከትላ ሁለተኛዋ ናት። አስካሁንም 28 ቢሊየን ዩሮ የሚያወጣ ወታደራዊ ድጋፍን ሰጥታለች።

የጀርመን ዐቃቤ ሕግ እንዳለው ዲተር ኤስ. የተባለው ዋነኛው ተጠርጣሪ ካለፈው ጥቅምት ጀምሮ ከሩሲያ የስለላ ሠራተኞች ጋር ለዩክሬን የሚሰጡ ወታደራዊ ድጋፎችን ለማደናቀፍ ሊፈጸሙ ስለሚችሏቸው አሻጥሮች ሲወያይ ነበር ብሏል።

በውይይቱም ወታደራዊ እና ኢንዱስትሪያዊ መሠረተ ልማቶችን ዋነኛ ዒላማዎች በማድረግ መለየታቸውም ተገልጿል። ተጠርጣሪዎች በጀርመን የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማትን ጨምሮ ዋነኛ ዒላማዎችን በመቃኘት ፎቶ እና ቪዲዮዎችን ማንሳቱን፤ እንዲሁም እነዚህን መረጃዎች ለሩሲያ አሳልፎ ሰጥቷል ተብሏል።

የጀርመን ፍትሕ ሚኒስትር ማርኮ ቡሽማን ለአገራቸው የዜና ወኪል ዲፒኤ እንደተናገሩት፣ የሁለቱ ተጠርጣሪዎች መያዝ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን የአሻጥር እና የስለላ መዋቅርን በመዋጋት በኩል “ሌላ ወሳኝ የምርመራ ስኬት ነው” ሲሉ አወድሰውታል።

በአሁኑ ወቅት በዩክሬን ጉብኝት ላይ የሚገኙት የጀርመን ምክትል መራሄ መንግሥት ሮበርት ሃቤክ ዛሬ ኪዬቭ ውስጥ “ዩክሬን ለነጻነቷ በምታደርገው ፍልሚያ ወቅት የምትፈልገውን ድጋፍ ሁሉ ታገኛለች” በማለት የጀርመን ድጋፍ እንደሚቀጥል አሳውቀዋል።

የጀርመን መንግሥት ለዩክሬን እያደረገ ካለው ወታደራዊ ድጋፍ በተጨማሪ የዩክሬንን የአየር ጥቃት መከላከያ ሥርዓትን ለማጠናከር በመሪነት እየተንቀሳቀሰ ነው።

የአገሪቱ መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ትናንት ረቡዕ እንደተናገሩት፣ የአውሮፓ ኅብረት አገራት ፓትሪዮት ፀረ ሚሳኤል መከላከያን ጨምሮ የዩክሬንን የአየር መከላከያ ሥርዓትን የበለጠ ለመጠናከር ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

አስካሁን ጀርመን ሁለት የአየር ጥቃት መከላከያ ፓትሪዮት ፀረ ሚሳኤል ዘመናዊ መሳሪያዎችን የሰጠች ሲሆን፣ ሦስተኛውን ደግሞ በቅርቡ ለመስጠት ቃል ገብታለች።