በሌሎች ክልሎች ልዩ ኃይልና ታጣቂዎች ሲበተኑ ለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተሰጠው መብት ለአሁኑ ቀውስ መነሻ ነው- ኢዜማ
ባለፉት ጥቂት ቀናት በአላማጣ እና አከባቢው የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ታጣቂዎች “የኃይል እርምጃ እየወሰዱ” መሆኑን ተከትሎ መንግሥት “ጦርነት የሚጎስመውን የሕወሓት ስብስብ በፕሪቶሪያው ሥምምነት መሠረት ትጥቅ እንዲፈታ” በማድረግ ሕግ እና ሥርዓት እንዲያስከብር ሲል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ አሳሰበ።
መግለጫው ቡድኑን [ህወሓት] ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ ዛሬም ቢሆን ከአጎራባች ክልሎች አልፎ ለአገር ሉዓላዊነት ጠንቅ ሊሆን እንደሚችል መታሰብ ይኖርበታል ብሏል።
መንግስት ቡድኑ በፈረመው ሥምምነት መሠረት በሰላሳ ቀናት ውስጥ መሣሪያ አስረክቦ ወደ ሰላም አስተሳሰብ እንዲመጣ ሊደረግ ሲገባ ይበልጥ እራሱን አደራጅቶ ዛሬም ንፁሀን ዜጎችን ለመከራ ለእንግልት እና ከቀያቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ እንዲወድቁ እያደረገ ይገኛል ሲል ኢዜማ ህወሓትን ተችቷል።
ኢ-ሕገ መንግስታዊ አደረጃጀት የነበረው የክልል ልዩ ኃየል ትጥቅ በማስፈታት መዋቅሩ እንዲፈርስ ሲደረግ፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ እውቅና የሌለው “ፓርቲ” ከመሆኑ ባሻገር “መሣሪያ የታጠቁ የራሱ ኃይሎች ያሉት ብቸኛ ስብስብ” ነው ሲል ኢዜማ መግለጹን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተመልክታለች።
በተለይ በሌሎች ክልሎች ያሉ ልዩ ኃይሎች እና ታጣቂዎች ሁሉ ፈርሰው ወጥ በሆነ የጸጥታ አመራር ሥር ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ቢደረግም “ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ልዩ መብት በማጎናፀፍ በሌሎች ክልሎች በሌለ እና ፈጽሞ በማይታሰብ መልኩ ታጣቂ ኃይል የማሠማራት መብት በመሰጠቱ” አሁን በአማራ ክልል ያለው ቀውስ እንዲቀጣጠል መነሻ መሆኑን ጠቁሟል።
ሕወሓት አንዴ “ትጥቅ ፈትተናል” ሌላ ጊዜ ደግሞ “የምንፈልገውን ለማድረግ በቂ ኃይል አለን” በማለት ከፕሪቶሪያው ሥምምነት ባፈነገጠ መልኩ “ሲያምታቱ”፤ የፈደራል መንግሥቱ እያሳየ ያለው ኃላፊነቱን በአግባቡ ያለመወጣት፣ ደካማ መረጃ አሰጣጥ፣ ቸልተኝነት እና መሰል ግዴለሽነት የተሞላ ተግባር በእጅጉ የሚያሳዝነን፣ በፅኑ የምናወግዘውም ነው” ብሏል።
አሁን የተከሰተውን አለመረጋጋት እና ችግር ለመፍታት የፌደራል መንግስት “የአንበሳውን ድርሻ” እንደሚወስድ የገለጸው ኢዜማ፤ መንግሥት የፕሪቶሪያውም ሥምምነት ተከብሮ በአስቸኳይ ትጥቅ እንዲፈታ እና “ጦርነት የሚጎስመውን ስብስብም ሥርዓት እንዲያሲዝ” በማለት ፓርቲው አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ እንድገለጸው ይኽ መሆን ካልቻለ “ህወሓት ሰሞኑን የጀመረው ዳግም ወረራ በዜጎች ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ለሚደርሰው ውድመት እና ምስቅልቅል መንግሥት ሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስድ ይሆናል”።
የአማራ እና ትግራይ ክልሎች ከሚወዛገቡባቸው የራያ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ራያ አላማጣ ወረዳ በትጥቅ የተደገፈ ግጭት መጀመሩን አዲስ ማለዳ ከተለያዩ ወገኖች የሚሰጡ መረጃዎችን እያቀረበች መዘገቧ አይዘነጋም።
“የህወሓት ኃይሎች ጀምረውታል” ከተባለው ጥቃት ተከትሎ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በዚህ ጉዳይ ላይ “ህወሓት እጁ የለበትም” ያለ ሲሆን በአንጻሩ የአማራ ክልል መንግስት “ህወሓት አራተኛ ዙር ወረራ ፈጽሞብናል” በማለት የሚቃረን መግለጫ ማውጣታቸው አይዘነጋም።