የአሜሪካ ሠራዊት አባላት በረዜስዞው-ጃሲኦንካ አየር ማረፊያ
የምስሉ መግለጫ,የአሜሪካ ሠራዊት አባላት በረዜስዞው-ጃሲኦንካ አየር ማረፊያ

ከ 4 ሰአት በፊት

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪን ለመግደል ከሩሲያ የደኅንነት አገልግሎት ጋር አሲሯል የተባለ ግለሰብ ፖላንድ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለ።

የፖላንድ ዐቃቤ ሕግ ፓዌል ኬ የተባለው ግለሰብ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ፖላንድ ውስጥ ያለ አብዝተው ስለሚጠቀሙበት አየር ማረፊያ መረጃ እንዲሰበስብ ከሩሲያ ኃላፊነት ተሰጥቶታል ብሏል።

ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው የዩክሬን የደኅንነት መሥሪያ ቤት ለፖላንድ መንግሥት ጥቆማ ከሰጠ በኋላ ነው።

ዐቃቤ ሕግ ግለሰቡ አየር ማረፊያውን በተመለከተ ለሩሲያ ያቀበለው መረጃ ስለመኖሩ ያለው ነገር የለም።

ፓዌል ኬ ጥፋተኛ ሆኖ የሚገኝ ከሆነ 8 ዓመታትን በእስር ሊያሳልፍ ይችላል።

ከፖላንድ መንግሥት የተሠጠ መግለጫ እንደሚለው ከሆነ ተጠርጣሪው የስለላ ሥራውን ለመስጠት ለሩሲያ ደኅንነቶች ጥያቄ በቀጥታ አቅርቧል።

“በዩክሬን ጦርነት ውስጥ በቀጥታ እየተሳተፉ ያሉ” ሩሲያውያንን አነጋግሯል ተብሏል።

የሩሲያ የደኅንነት ተቋምም ፓዌል ኬ በደቡብ ምሥራቅ ፖላንድ የሚገኘውን ረዜስዞው-ጃሲኦንካ አየር ማረፊያን የተመለከተ መረጃ እንዲሰበስብ ኃላፊነት ሰጥቶታል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ ከመፈጸሟ በፊት ይህ አየር ማረፊያ ብዙ እንቅስቃሴ የሌለበት አነስተኛ አየር ማረፊያ ነበር።

ከወረራው በኋላ ግን ምዕራባውያን ለዩክሬን ጦር መሳሪያ የሚያስተላልፉበት መሆኑን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ዓመታት የማስፋፊያ ሥራ ተሠርቶለታል።

መነሻቸውን አሜሪካ እና አውሮፓ ያደረጉ የጦር እና ዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ጭነታቸውን በዚህ አየር ማረፊያ ያራግፋሉ።

ወታደራዊ ቁሶቹም በከባድ ተሸከርካሪዎች 100 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው የዩክሬን ድንበር ይጓጓዛል።

ከዚህ በተጨማሪ ወደ ዩክሬን የሚጓዙ መሪዎች ይህን አየር ማረፊያ ይጠቀማሉ። በአሁኑ ወቅት የዩክሬን የአየር ክልል ለብዙ በረራዎች ዝግ በመሆኑ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ መሪዎች ወደ ዩክሬን በሚጓዙ ወቅት ይህን አየር ማረፊያ ይጠቀማሉ።

መሪዎች አብዛኛውን ጊዜ ፖላንድ ደርሰው ከፖላንድ ወደ ዩክሬን መዲና ኪዬቭ በባቡር ጉዟቸውን ይቀጥላሉ።

ዜሌንስኪ ከዚህ ቀደም ለውጪ ጉብኝት ከአገር ሲወጡ ረዜስዞው-ጃሲኦንካ አየር ማረፊያን ነበር የተጠቀሙት።

በዚህ አየር ማረፊያ ላይ ሩሲያ ስለላ ታደርጋለች ሲባል ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ከአንድ ዓመት በፊት የፖላንድ መንግሥት በአየር ማረፊያው ዙሪያ ካሜራዎችን ተከትለው ሲሰልሉ ነበሩ ያለቻቸውን በርካታ የውጭ አገር ዜጎች በቁጥጥር ስር አውላለች።