በአደጋው የሞቱት ጄኔራል ፍራንሲስ ኦሞንዲ ኦጎ (ከቀኝ) ከፕሬዝዳንት ዊሊያን ሩቶ ጋር (ከግራ)
የምስሉ መግለጫ,በአደጋው የሞቱት ጄኔራል ፍራንሲስ ኦሞንዲ ኦጎ (ከቀኝ) ከፕሬዝዳንት ዊሊያን ሩቶ ጋር (ከግራ)

ከ 4 ሰአት በፊት

የኬንያ ጦር አዛዥ ጄኔራል ፍራንሲስ ኦሞንዲ ኦጎላ በምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ይበሩበት የነበረው ወታደራዊ ሄሊኮፕተር ተከስክሶ ሕይወታቸው ማለፉን ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ አስታወቁ።

ኦጎላ ከሌሎች 11 ወታደራዊ መኮንኖች ጋር ሆነው በሄሊኮፕተሩ ሲጓዙ ነው አደጋው የደረሰው። ከአደጋው የተረፉት ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው።

ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሐሙስ ምሽት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አደጋው ለአገሪቱ “ትልቅ ሐዘን” ነው ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ቀደም ብለው የአገሪቱ የፀጥታ ምክር ቤት አባላቶቻቸውን ለአስቸኳይ ስብሰባ ጠርተው ነበር።

አደጋው የደረሰው ሐሙስ ሚያዝያ 10/2016 ዓ.ም. ከቀን 8፡20 ላይ መሆኑን ሩቶ ተናግረዋል። የኬንያ አየር ኃይል የአደጋውን መንስኤ ለማጣራት የምርመራ ቡድን አሰማርቷል።

ሄሊኮፕተሯ ከተነሳች ከደቂቃዎች በኋላ የተከሰከሰችው ከዋና ከተማዋ ናይሮቢ በስተሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኤልጌዮ ማራክዌት መሆኑን ፕሬዝዳንት ሩቶ ተናግረዋል።

የአየር ኃይል አዛዥ እና የመከላከያ ሠራዊት ምክትል አዛዥ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት ጀነራል ኦጎላ ከአንድ ዓመት በፊት ነበር የጦር አዛዥ ሆነው የተሾሙት።

ሩቶ ዋና የጦር አማካሪያቸውን በግዳጅ ላይ እያሉ ሕይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል።

ጀነራል ፍራንሲስ ኦሞንዲ ኦጎ

“እናት አገራችን ከጄኔራሎቿ መካከል አንዱ የሆነውን ጀግናዋን አጥታለች” ሲሉ ዊሊያም ሩቶ ለአገራቸው ሕዝብ ተናግረዋል።

በኬንያ ከዛሬ አርብ ጀምሮ ሦስት የብሔራዊ ሐዘን ቀናት ታወጁ ሲሆን፣ የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማም ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ይደረጋል።

ጄኔራል ኦጎላ ለመጀመሪያ ጊዜ የኬንያ መከላከያ ሠራዊትን የተቀላቀሉት ሚያዝያ 1976 (እአአ) እንደነበር የኬንያ መከላከያ ሚኒስቴር ድረ-ገጽ ዘግቧል።

ሥራቸውን የጀመሩት በአገሪቱ አየር ኃይል ውስጥ ሲሆን፣ ከአሜሪካ አየር ኃይል ጋር በተዋጊ አውሮፕላን አብራሪነት ሠልጥነዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት “አሳዛኙን የሄሊኮፕተር አደጋ ተከትሎ ለኬንያ ፕሬዝዳንት፣ መንግሥት እና ሕዝብ” ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

ከአደጋው የተረፉት ሁለት ግለሰቦች በአስጊ ሁኔታ ላይ መሆናቸው እና ሕክምና እየተከታተሉ እንደሆነ ተገልጿል።

የጦር መኮንኖቹ ተደጋጋሚ ጥቃት የሚደርስበትን ሰሜን ኬንያን ጎብኝተው ሲመለሱ ነው አደጋው የደረሰባቸው።

በሽፍቶች ጥቃቶችን ምክንያት የተዘጉ አንዳንድ ትምህርት ቤቶችን ለማስክፈት ተልዕኮ ላይ ነበሩም ተብሏል። አካባቢውን ለማረጋጋት የተሰማሩ የጦር መኮንኖችንም መጎብኘታቸው ተገልጿል።

እአአ ሰኔ 2021 በዋና ከተማዋ ናይሮቢ አቅራቢያ ሊያርፍ የነበረ ሄሊኮፕተር ተከስክሶ ቢያንስ 10 ወታደሮች ሞተዋል።