
ከ 4 ሰአት በፊት
እስራኤል ባለፈው ቅዳሜ ኢራን ለፈጸመችባት የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃት ዛሬ ማለዳ ላይ የአጸፋ ጥቃት መፈጸሟን የኢራን መገናኛ ብዙኃን እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ዛሬ አርብ ጎህ ከመቅደዱ በፊት በማዕከላዊቷ የኢራን ከተማ ኢስፋሃን ፍንዳታዎች መሰማታቸውን የኢራን የመገናኛ ብዙኃን የዘገቡ ሲሆን፣ የአሜሪካ ባለሥልጣናትም ይህን አረጋግጠዋል።
እስራኤል በኢራን ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሟን የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ቴሌቪዥን አረጋግጠዋል።
የኢራን መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ሦስት የእስራኤል ድሮኖች በኢራን የአየር መከላከያ ሥርዓት መውደማቸውን ዘግበዋል።
ጥቃቱ ተፈጽሞባታል የተባለችው የኢራን ከተማ ኢስፋሃን የአገሪቱ አየር ኃይል መቀመጫ ስትሆን፣ በርካታ ወታደራዊም ተቋማት በውስጧ ይገኛሉ።
ጥቃቱ ከተፈጸመ ጥቂት ሰዓታት ብቻ ያለፉት በመሆናቸው አስካሁን ዒላማ ስለሆኑ ቦታዎች እና ስለደረሰ ጉዳት የወጣ መረጃ የለም። የኢራን መገናኛ ብዙኃንም የአገሪቱ የኑክሌር ተቋማት ላይ ምንም ጉዳት አለመድረሱን አመልክተዋል።
- ኢራን እና እስራኤል ለምን ደመኛ ጠላቶች ሆኑ?18 ሚያዚያ 2024
- ኢራን በእስራኤል ላይ በፈጸመችው ጥቃት ማን አተረፈ? ማንስ ከሰረ?17 ሚያዚያ 2024
- ኢራን በእስራኤል ላይ ስላዘነበችው የድሮን እና የሚሳዔል ጥቃት አስካሁን የሚታወቀው15 ሚያዚያ 2024
ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካታ በረራዎች በኢራን በኩል የሚያደርጉትን ጉዞዎች በመተው ሌላ አቅጣጫን መምረጣቸውን የበረራ መከታተያ ድረ ገጾች ያሳያሉ።
የእስራኤል ጦር ሠራዊት እና የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት ፔንታገን ጥቃቱን በተመለከተ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አይደሉም።
ይህ የእስራኤል የአጸፋ ጥቃት የተፈጸመው ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ኢራን ከ300 በላይ ሚሳኤሎችን እና ድሮኖችን በማስወንጨፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከሰነዘረች በኋላ ነው።
ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃቱን የፈጸመችው ሶሪያ ውስጥ በሚገኘው የቆንስላ ጽህፈት ቤቷ ላይ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ከፍተኛ ወታደረዊ መኮንኖችን ጨምሮ 13 ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት ለመበቀል መሆኑን ገልጻለች።
የኢራን ጥቃት በእስራኤል እና በምዕራባውያን ወዳጆቿ እንዲከሽፍ በመደረጉ ይህ ነው የሚባል ጉዳት አለመድረሱን ሪፖርቶች አመልክተዋል።
እስራኤልም ለተፈጸመባት ጥቃት የአጸፋ ምላሽ በመስጠት ኢራን ዳግም ጥቃት እንዳትፈጽምባት እንደምታደርግ ስትዝት የቆየች ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን ሁለቱም አገራት ከግጭት እንዲቆጠቡ ጥሪ ሲያደርግ ነበር።