የናይጄሪያ ሠራዊት ያሰራጨው ነጻ የወጣችው ሴት ከአንደኛው ልጇ ጋር ሆና የሚያሳይ ፎቶ
የምስሉ መግለጫ,የናይጄሪያ ሠራዊት ያሰራጨው ነጻ የወጣችው ሴት ከአንደኛው ልጇ ጋር ሆና የሚያሳይ ፎቶ

ከ 2 ሰአት በፊት

ከአስር ዓመት በፊት በቦኮሃራም ታጣቂዎች ታግተው ከነበሩ ሴቶች መካከል አንዷ የሦስት ልጆች እናት ሆና በናይጄሪያ መንግሥት ወታደሮች ነጻ ወጣች።

በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 2014 ቦርኖ ከምትባለው ከተማ የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች 276 ተማሪ ሴቶችን ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤታቸው አፍነው መውሰዳቸው ይታወሳል።

እነዚህ የቺቦክ ትምህርት ቤት ሴት ልጆች መታገት መላው ዓለምን አስደንግጦ በወቅቱ የአሜሪካ ቀዳማዊ እመቤት የነበሩትን ሚሼል ኦባማን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የማስለቀቅ ዘመቻ እንዲጀመር ምክንያት ሆኖ ነበር።

ታፍነው ተወስደው ከነበሩት 280 ከሚጠጉት ልጃገረዶች መካከል አስካሁን ድረስ 100 የሚሆኑት በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ስር ናቸው ወይም የደረሱበት አልታወቀም።

ትናንት ሐሙስ ደግሞ የናይጄሪያ ሠራዊት ከአስር ዓመት በፊት ከታፈኑት ተማሪዎች መካከል አንዷን ከሦስት ልጆቿ ጋር ከታጣቂዎቹ ነጻ ማውታቱን አስታውቋል።

ታጋቿ ሦስት ልጆቿ በተጨማሪም የአምስት ወራት ነፍሰ ጡር መሆኗን ሠራዊቱ ገልጿ።

በቦኮ ሃራም ቡድን ታፍነው ከተወሰዱ ሴት ተማሪዎች መካከል አስካሁን ከ180 በላይ የሚሆኑት በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ውስጥ ከምትገኘው ቦርኖ ግዛት የቡድኑ መደበቂያ ሳምቢሳ ጫካ በፀጥታ ኃይሎች ነጻ ወጥተዋል ወይም ከቡድኑ አምልጠዋል።

አስካሁን ከቡድኑ ነጻ ከወጡ ልጃገረዶች መካከል አንዳንዶቹ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ ማርገዛቸው ወይም ልጅ መውለዳቸው ተዘግቧል።

የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች ጠልፈው የሚወስዷቸውን ተማሪዎች በወሲብ ባርነት ስር ያቆይዋቸዋል የሚሉ ዘገባዎች በተደጋጋሚ ሲወጡ መቆየታቸው ይታዋል።

ወደ ቤታቸው ከተመለሱት መካከልም የተወሰኑት የናይጄሪያ ባለሥልጣናት የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ እና ድጋፍ እንዳላደረጉላቸው በመግለጽ መንግሥትን ይታቻሉ።

በናይጄሪያ ውስጥ አሁንም የጅምላ አፈና ተማሪዎችን እና ወላጆችን የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል። የተለያዩ ወሮበላ ቡድኖች ተማሪዎችን ዒላማ በማድረግ ጠልፈው እየወሰዱ ማስለቀቂያ እንዲከፈላቸው መጠየቃቸው የተለመደ ነው።

በሴቭ ዘ ችልድረን በጎ አድራጎት ድርጅት መረጃ መሠረት ከአውሮፓውያኑ 2014 አስከ 2022 ድረስ በናይጄሪያ ውስጥ ከ1,680 በላይ ተማሪዎች ታግተዋል።

ባለፈው መጋቢት ወር ከናይጄሪያዋ ሰሜን ምዕራብ ግዛት ካዱና ትምህርት ቤት ከ130 በላይ ተማሪዎች በታጣቂዎች ተጠልፈው የተወሰዱ ሲሆን፣ ይህም በቅርብ ዓመታት ውስጥ የተፈጸመ ከፍተኛው ጠለፋ ነው ተብሏል።

ነገር ግን የናይጄሪያ ጦር ሠራዊት ተማሪዎቹ ወደ አጎራባቿ ዛምፋራ ግዛት ተወስደው ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነጻ መውታቸውን የገለጸ ሲሆን፣ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደተለቀቁ ግን ዝርዝር መረጃ አልወጣም።