
ከ 3 ሰአት በፊት
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የማጭበርበር ክስ በሚታይበት ማንሃታን በሚገኘው ፍርድ ቤት አቅራቢያ አንድ ግለሰብ ራሱን አቃጠለ።
ፖሊስ እንዳለው ግለሰቡ ራሱ ላይ ተቀጣጣይ ፈሳሽ አርከፍክፎ ከማቃጠሉ በፊት በራሪ ወረቀቶችን በትኗል።
የግለሰቡ ዓላማ ምን እንደሆነ ግን አልታወቀም።
ትራምፕ የዳኞችን ምርጫ ለመታደም በሕንጻው ውስጥ የነበሩ ሲሆን ድርጊቱ በተፈፀመበት ወቅት ሕንጻውን ለቀው ወጥተዋል።
የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ባለሥልጣናት ክስተቱ የፍርድ ቤት ደኅንነትን እንዳልጣሰ ተናግረዋል።
ጉዳያቸውን የሚመለከቱ ተለዋጭ ዳኛ የመሰየሙ ሒደትም ከሰዓት በኋላ ቀጥሏል።
መርማሪዎች ክስተቱን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በ911 የአደጋ ጊዜ የጥሪ ማዕከል ተደውሎላቸው አንድ ግለሰብ ራሱን ሊያቃጥል እንደሆነ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።
ማክስዌል አዛሬሎ ተብሎ የተለየው የ37 ዓመቱ ግለሰብ ይኖርበት ከነበረው ፍሎሪዳ ወደ ኒው ዮርክ ያመራው ባለፈው ሳምንት ነበር።
ግለሰቡ ከዚህ በፊት በኒው ዮርክ የሰራው ወንጀል እንደሌለ እና በፍሎሪዳ የሚኖሩ ቤተሰቦቹ ወደ ኒው ዮርክ ማቅናቱን እንደማያውቁም ተገልጿል።
- ትራምፕ በማጭበርበር ክስ 354 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ተወሰነ17 የካቲት 2024
- ትራምፕ፤ ፕሬዝደንት ባይደን እጅና እግራቸው ተጠፍሮ የሚታዩበት ፎቶ መለጠፋቸውን ተከትሎ ወቀሳ ደረሰባቸው31 መጋቢት 2024
- ጆ ባይደን ከዶናልድ ትራምፕ፡ ለፕሬዝዳንትነት አሸናፊውን የሚለዩ አራት ወሳኝ ነጥቦች16 ሚያዚያ 2024

የኒው ዮርክ ፖሊስ አዛዥ ጀፍሪ ማድሬይ እንዳሉት አዛሬሎ ተቀጣጣይ ፈሳሽ እና በራሪ ወረቀቶችን ይዞ ወደ ሥፍራው ከማቅናቱ በፊት በአካባቢው በሚገኝ መናፈሻ ውስጥ ሲዘዋወር ነበር።
የበተናቸው በራሪ ወረቀቶች ፕሮፖጋንዳ ላይ የተመሰረቱ እንደሆኑ የገለጹት የፖሊስ አዛዡ፣ ‘የሴራ ፅንሰ ሐሳብ’ ያላቸው ናቸው ብለዋል።
በትራምፕ ችሎት ምክንያት በፍርድ ቤቱ አካባቢ በርካታ የፀጥታ አካላት የነበሩ ሲሆን የፖሊስ መኮንኖች እሳቱን ለማጥፋት ወደ መናፈሻው በፍጥነት ነበር ያመሩት።
በእሳት ክፉኛ የተቃጠለውን አዛሬሎን በማንሳት ወደ አካባቢው ወደሚገኝ የቃጠሎ ህክምና ማዕከል መወሰዱን ፖሊስ ገልጿል።
ሦስት የኒው ዮርክ ፖሊስ መኮንኖች እና አንድ የፍርድ ቤት ባለሥልጣን እሳቱን ለማጥፋት ሲሞክሩ ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ጁሊ በርማን የተባሉ የዓይን ምስክር “ . . . ምንም ትርጉም የሚሰጥ አይደለም፤ ሁሉም ነገር በፍጥነት የሆነ ነበር። ምን እየተካሄደ እንዳለ ለማወቅ 20 ሰከንድ ፈጅቶብኛል” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ከአደጋው በኋላ መርማሪዎች በሥፍራው ተገኝተው ግለሰቡ ራሱን ከማቃጠሉ በፊት የበተናቸውን ወረቀቶች ሲሰበስቡ ታይተዋል።
መርማሪዎቹ የዓይን እማኞችን እያነጋገሩ ሲሆን ግለሰቡ ራሱን ከማቃጠሉ በፊት የተናገረው ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።
በአሜሪካ ግለሰቦች ራሳቸውን ሲያቃጥሉ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
የካቲት ወር ላይ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ከሚገኘው የአስራኤል ኤምባሲ ፊት ለፊት አንድ የአሜሪካ የአየር ኃይል አባል ራሱን በእሳት ያቃጠለ ሲሆን በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል።