አያቶላ ኾሜኒ እና ቤንያሚን ኔታኒያሁ
የምስሉ መግለጫ,አያቶላ ኾሜኒ እና ቤንያሚን ኔታኒያሁ

ከ 4 ሰአት በፊት

ምንም እንኳን የሰነዘረችው የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃት ጉዳት ባያደርስም፣ ኢራን ከርቀት በእስራኤል ላይ ጥቃት የመፈጸም ብቃት እንዳላት አሳይታለች።

ይህም ሁለቱ አገራት ለረጅም ጊዜ በእጅ አዙር ሲያደርጉት የነበረው ፍልሚያ ወደ ቀጥታ ግጭት ማምራቱን ያሳያል። ኢራን በምትደግፋቸው ቡድኖች እስራኤልን ስታስጠቃ፣ እስራኤል ደግሞ ከኢራን ጋር የሚገናኙ ዒላማዎችን ስትመታ በቀጥታ ከመጋጨት ተቆጥበው ነበር።

ጋዛ ውስጥ ከሐማስ ጋር፣ ከሊባኖሱ ሂዝቦላህ ጋር ደግሞ ድንበር በሚሻገር ግጭት ውስጥ የምትገኘው እስራኤል፤ ከኢራን ጋር የቀጥታ ፍጥጫ ውስጥ ከገባች ቀውሱ የበለጠ ይባባሳል ተብሎ ተሰግቷል።

የእስራኤል ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌተናንት ኮሎኔል ሄርዚ ሃሌቪ ኢራን ለፈጸመችው ጥቃት አገራቸው አጸፋውን እንደምትመልስ በደፈናው አስጠንቅቀው ነበር።

የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ባግረሄሪ ካኒ በበኩላቸው እስራኤል ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ ምላሹ በሰዓታት ሳይሆን በሰከንዶች ውስጥ ይደርሳታል ሲሉ ዝተዋል።

የኢራን ሚሳኤል ግንባታ የጦር ኃይሏ ዋነኛ ተግባር ነው
የምስሉ መግለጫ,የኢራን ሚሳኤል ግንባታ የጦር ኃይሏ ዋነኛ ተግባር ነው

ማን ወታደራዊ የበላይነት አለው?

ቢቢሲ ሁለቱ አገራት ያላቸውን ወታደራዊ ብቃት ለማወቅ የተለያዩ ምንጮችን ተጠቅሟል። ነገር ግን አገራቱ ከዚህም በላይ የተደበቀ ወታደራዊ አቅም ሊኖራቸው ይችላል።

ዓለም አቀፉ የስትራተጂክ ጥናት ተቋም (አይአይኤስኤስ) እስራኤል እና ኢራን ያላቸውን የጦር መሳሪያ አቅም ለመገመት የተለያዩ መንግሥታዊ እንዲሁም ማንም ሊያገኛቸው የሚችሉ የመረጃ ምንጮችን እና ዘዴዎችን ተጠቅሟል።

የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ ሰላም ተቋምን የመሳሰሉ ድርጅቶችም የአገራቱን ወታደራዊ አቅም ለማወቅ ጥናቶች አድርገዋል። ነገር ግን ትክክለኛ አሃዝ በማግኘት በኩል አገራት መረጃዎችን ስለማይሰጡ ልዩነቶች ይታያሉ።

የኦስሎ የሰላም ጥናት ተቋም (ፒአርአይኦ) ባልደረባ ኒኮላስ ማርሽ እንደሚሉት ግን የዓለም አቀፉ የስትራተጂክ ጥናት ተቋም (አይአይኤስኤስ) መረጃ በዓለም ዙሪያ ያሉ አገራትን ወታደራዊ ጥንካሬ ለማውቅ እንደ መነሻ ሊወሰድ ይችላል።

ተቋሙ እንደሚለው እስራኤል ከኢራን በላይ ከፍተኛ ገንዘብ ለመከላከያ ስለምትመድብ በየትኛውም ግጭት ውስጥ ከፍተኛ ጥንካሬ እንዲኖራት ያስችላታል።

በአይአይኤስኤስ መረጃ መሠረት በአውሮፓውያኑ 2022 እና 2023 የኢራን የመከላከያ በጀት 7.4 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ የነበረ ሲሆን፣ የእስራኤል ግን ከእጥፍ በላይ 19 ቢሊዮን ዶላር ነበር። ከምጣኔ ሃብት አንጻርም የእስራኤል አጠቃላይ አገራዊ ምርት ከኢራን በእጥፍ የሚበልጥ ነው።

ሰንጠረዥ

የቴክኖሎጂ የበላይነት

የአይአይኤስኤስ አሃዞች እንደሚያመለክቱት እስራኤል ለውጊያ ዝግጁ የሆኑ 340 ወታደራዊ አውሮፕላኖች ሲኖሯት፣ ይህም ዒላማ የለዩ ጥቃቶችን የመፈጸም ብቃትን ይሰጣታል።

ካሏት የጦር ጄቶች መካከልም ረጅም ርቀት ተጉዘው ጥቃት የሚፈጽሙት ኤፍ-15 አውሮፕላኖች፣ እጅግ ዘመናዊዎቹ ኤፍ-35 አውሮፕላኖች ደግሞ ከራዳር ዕይታ ውጪ የሚጓዙ ሲሆኑ፣ ፈጣን አጥቂ ሄሊኮፕተሮችም አሏት።

ኢራን ደግሞ 320 የሚደርሱ የውጊያ ብቃት ያላቸው አውሮፕላኖች ባለቤት ናት። ጄቶቿ የ1960ዎቹ ስሪቶችን ጨምሮ ኤፍ-4፣ ኤፍ-5 እና ኤፍ-14 የጦር አውሮፕላኖች እንዳሏት አይአይኤስኤስ ገልጿል።

የኦስሎ የሰላም ጥናት ተቋሙ ኒኮላስ ማርሽ እንደሚሉት ኢራን ካሏት አሮጌ የጦር አውሮፕላኖች መካከል ምን ያህሉ መብረር እንደሚችሉ ማወቅ አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም የአውሮፕላኖቹን መለዋወጫ በአሁኑ ጊዜ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ ነው ይላሉ።

የጦር አውሮፕላን

የሚሳኤል ጥቃት መከላከያዎች

አይረን ዶም እና አሮው የተባሉት የሚሳኤል ጥቃት መከላከያ ሥርዓቶች እስራኤል እራሷን ለመጠበቅ የሚያስችሏት የጀርባ አጥንቶቿ ናቸው ሊባሉ ይችላሉ።

የሚሳኤሎች ኢንጂኒየር የሆኑት ኡዚ ሩቢን በእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኘው የእስራኤል የሚሳኤል የመከላከያ ድርጅት መሥራች ናቸው።

አሁን ደግሞ በኢየሩሳሌም የስትራተጂ እና ደኅንነት ተቋም ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ ሲሆኑ፣ ባለፈው ቅዳሜ በኢራን የተተኮሱትን ሚሳኤሎች እና ድሮኖች አይረን ዶም እና የእስራኤል አጋሮች ሲያከሽፏቸው ሲመለከቱ “ደኅንነት ነው የተሰማኝ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“የጥቃት መከላከያዎቹ ሚሳኤሎችን በማምከን እንከን የማይወጣለች ናቸው. . . በጣም ደስታ እና እርካታ ነው የተሰማኝ። መከላከያዎቹ የአጭር ርቀት የሚሳኤል ጥቃቶችን የሚያመክኑ ሲሆኑ፣ እነሱን የሚመስል ሌላ ዘዴ የለም።”

ምስል

ኢራን ከእስራኤል ምን ያህል ትርቃች?

እስራኤል ከኢራን ከ2,100 ኪሎ ሜትር በላይ በሚሆን ርቀት ላይ ነው የምትገኘው። ዲፌንስ አይ የተባለው መጽሔት አርታኢ ቲም ሪፕሌይ ለቢቢሲ ሲናገር፣ ኢራን እስራኤልን ለማጥቃት ዋነኛው መሳሪያዋ ሚሳኤል ነው።

ለዚህም ኢራን የምታካሂደው የሚሳኤል ግንባታ ፕሮግራም በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ካሉት መካከል ትልቁ እና የተለያየ አቅም ያለው መሆኑ ይነገራል።

ከአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ጄኔራል ኬኔት ማኬንዚ በአውሮፓውያኑ 2022 እንደተናገሩት ኢራን “ከ3,000 በላይ” ተወንጫፊ ሚሳኤሎች አሏት።

ሲኤስአይኤስ ሚሳኤል ዲፌንስ ፕሮጀክት ባወጣው መረጃ መሠረት ደግሞ እስራኤል ከራሷ አልፋ ለበርካታ አገራት ሚሳኤሎችን ሸጣለች።

ኢራን ወደ እስራኤል ከተኮሰቻቸው ተወንጫፊ ሚሳኤሎች አንዱ በሙት ባሕር ዳርቻ ላይ ወድቆ
የምስሉ መግለጫ,ኢራን ወደ እስራኤል ከተኮሰቻቸው ተወንጫፊ ሚሳኤሎች አንዱ በሙት ባሕር ዳርቻ ላይ ወድቆ

የኢራን ሚሳኤል እና ድሮኖች

ኢራን ከጎረቤቷ ኢራቅ ጋር ከአውሮፓውያኑ 1980 ጀምሮ ለስምንት ዓመታት የቆየ ጦርነት ካደረገችበት ጊዜ አንስቶ መጠነ ሰፊ የሚሳኤል እና የድሮን ግንባታ ሥራዎችን ስታከናውን ቆይታለች።

በዚህም ኢራን የአጭር እና የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ለመገንባት ችላለች፤ አብዛኞቹንም በእስራኤል ላይ በቅርቡ በፈጸመችው ጥቃት ወቅት ጥቅም ላይ አውላቸዋለች።

የየመን ሁቲዎች በሳዑዲ አረቢያ ላይ የተኮሷቸውን ሚሳኤሎች ያጠኑ ተንታኞች በደረሱት ድምዳሜ መሠረት፣ ሚሳኤሎቹ ኢራን ውስጥ የተሠሩ ናቸው ብለዋል።

አሜሪካ ኢራን የየመን ሁቲዎችን ድሮን ታስታጥቃለች በማለት ትከሳታለች
የምስሉ መግለጫ,አሜሪካ ኢራን የየመን ሁቲዎችን ድሮን ታስታጥቃለች በማለት ትከሳታለች

‘ከርቀት መቅጣት’

ቲም ሪፕሌይ እስራኤል ከኢራን ጋር በእግረኛ ወታደሮች የሚደረግ ጦርነት ውስጥ የመግባት ዕድሏ ዝቅተኛ ነው ይላል፤ “እስራኤል ያላት የአየር ኃይል እና ውጤታማ ተወንጫፊ የጦር መሳሪያዎቿ የበላይነትን ይሰጣታል። ስለዚህም ኢራን ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎች ላይ የአየር ጥቃት የመፈጸም ብቃት አቅም።”

ጨምሮም እስራኤል በምትፈጽማቸው የአየር ጥቃቶች ዋነኛ ዓላማዋ የኢራን ባለሥልጣናትን መግደል እና የነዳጅ ተቋማቷን ማውደም ሊሆን ይችላል ይላል።

“’መቅጣት’ የሚለው ቃል በእስራኤል ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ መሪዎች መካከል ዘወትር ጥቅም ላይ የሚውል ነው። ይህም የፍልስፍናቸው አካል ሲሆን፣ በዚህም ከባድ ጉዳትን በማድረስ ጠላታቸው እስራኤል ላይ እጁን ከማንሳቱ በፊት ሁለት ጊዜ እንዲያስብ የማድረግ ዓላማ አለው።”

ቀደም ሲልም እስራኤል በምትፈጽማቸው የአየር ጥቃቶች ከፍተኛ የኢራን ወታደራዊ እና ሲቪል ባለሥልጣናት ተገድለዋል።

በቅርቡም ሶሪያ ውስጥ የሚገኘውን የኢራን ቆንስላ በማጥቃት በርካታ ወታደራዊ መኮንኖችን ገድላለች። ምንም እንኳን እስራኤል ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ባትወስድም ኢራን ጥቃት እንድትፈጽም ምክንያት ሆኗል።

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የባሕር ኃይል በፈጣን ጀልባዎች ልምምድ ሲያደርግ
የምስሉ መግለጫ,የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የባሕር ኃይል በፈጣን ጀልባዎች ልምምድ ሲያደርግ

የባሕር ኃይል

አይአይኤስኤስ እንደሚለው ዘመናትን ያስቆጠረው የኢራን ባሕር ኃይል 220 መርከቦች ሲኖሩት፣ እስራኤል ደግሞ 60 የሚሆኑ መርከቦች አሏት።

እስራኤል እና ኢራን የሚጋሩት የውሃ አካል ስለሌለ በባሕር ኃይሎቻቸው አማካይነት ግጭት ውስጥ የመግባት ዕድለቸው ጠባብ ነው።

ነገር ግን በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቲ ታጣቂዎች በኤደን ባሕረ ሰላጤ እና በቀይ ባሕር በኩል በሚያልፉ የእስራኤል እና የምዕራባውያን መርከቦች ላይ ጥቃት እያደረሱ ነው።

የበይነ መረብ ጥቃት

በበይነ መረብ (ሳይበር) በኩል ሁለቱ አገራት አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ጥቃት ቢፈጽሙ ከኢራን ይልቅ እስራኤል ከባድ ጉዳት ይደርስባታል።

ኢራን ከእስራኤል ጋር ስትነጻጸር ያላት የመከላከያ ሥርዓት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የሚጠቀመው በዝቅተኛ ደረጃ ነው። ስለዚህም በእስራኤል ላይ የሚፈጸም የኤሌክትሮኒክስ ጥቃት ከባድ ጉዳትን ሊያደርስባት ይችላል።

የእስራኤል መንግሥት ብሔራዊ የሳይበር ክፍል በአገሪቱ የተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚፈጸሙ የበይነ መረብ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን ጠቅሶ “በጦርነቱ ወቅት በኢራን እና በሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሂዝቦላህ መካከል ያለው ትብብር ጨምሯል” ብሏል።

በሐማስ እና በእስራኤል መካከል ጦርነት ከተጀመረ አንስቶም በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ 3,380 የበይነ መረብ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ዘግቧል።

በኢራን በኩል ደግሞ የአገሪቱ ሲቪል መከላከያ ድርጅት ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ጎላምሬዛ ጃላሊ እንዳሉት፣ በቅርቡ በኢራን ምክር ቤታዊ ምርጫ ከመደረጉ ከአንድ ወር ቀደም ብሎ 200 የሚደርሱ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፋቸውን ገልጸዋል።

ባለፈው ታኅሣሥ በኢራን ላይ በተፈጸመ የበይነ መረብ ጥቃት፣ በመላው አገሪቱ በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ከባድ የአገልግሎት መስተጓጎል ገጥሟቸው እንደነበረ የነዳጅ ሚኒስትሩ ጃቫድ ኦውጂ ተናግረዋል።

የኢራን ፕሬዝዳንት የነበሩት ማህሙድ አህመዲነጃድ በ2008 (እአአ) አገራቸው የኑክሌር ኃይል ግብዓት የሆነውን የዩራኒየም ምርቷን መጨመሯን አስታውቀው ነበር
የምስሉ መግለጫ,የኢራን ፕሬዝዳንት የነበሩት ማህሙድ አህመዲነጃድ በ2008 (እአአ) አገራቸው የኑክሌር ኃይል ግብዓት የሆነውን የዩራኒየም ምርቷን መጨመሯን አስታውቀው ነበር

የኑክሌር ስጋት

እስራኤል የራሷ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎች እንዳሏት ቢነገርም፣ በመንግሥት ደረጃ ግን በይፋ እንዳይገለጽ በማድረግ መሳሪያው እንዳላት በሁሉም ዘንድ ጥርጠሬ እንዲፈጠር ስታደርግ ቆይታለች።

ምንም እንኳን ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ አላት ተብላ ብትከሰስም ምንም ዓይነት ማረጋገጫ አስካሁን የለም። ኢራን የምታካሂደው የኑክሌር ፕሮግራም ለሰላማዊ አገልግሎት የሚውል ነው ብላ ትከራከራለች።

እስራኤል እና ምዕራባውያን ግን ይህንን ባለመቀበል አንድ ቀን ኢራን ኑክሌር የታጠቀች አገር ሆና ብቅ ትላለች የሚል ስጋት አላቸው።

መልከዓ ምድር እና የሕዝብ ብዛት

ወደ 89 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት ኢራን፣ ከእስራኤል አንጻር ትልቅ አገር ናት። አስር ሚሊዮን ሕዝብ ያላት እስራኤል ዘጠኝ ጊዜ ከኢራን የሚያንስ ዜጋ ነው ያላት።

በተጨማሪም ኢራን እስራኤል ካሏት የመደበኛ ሠራዊት አባላት ስድስት እጥፍ የሚበልጡ ወታደሮች አላት።

በዚህም ኢራን 600,000 መደበኛ ወታደሮች ሲኖሯት፣ የእስራኤል ደግሞ 170,000 መሆናቸውን የአይአይኤስኤስ መረጃ የሳያል።

ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት በፈጸመችበት ጊዜ የሚሳኤል ማምከኛው አይረን ዶም ሲተኮስ
የምስሉ መግለጫ,ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት በፈጸመችበት ጊዜ የሚሳኤል ማምከኛው አይረን ዶም ሲተኮስ

እስራኤል ኢራንን እንዴት ትበቀላታለች?

በእስራኤል ጎረቤት አገራት ውስጥ የሚገኙት በኢራን የሚደገፉት ታጣቂዎች በእስራኤል ላይ መደበኛ ጥቃቶችን እየሰነዘሩ ሲሆን፣ በምላሹ እነሱን ዒላማ ልታደርጋቸው ትችላለች።

የመካከለኛው ምሥራቅ የመከላከያ ባለሙያው ጄሬሚ ቢኔ እንደሚያምኑት “እስራኤል አጸፋ ለመመለስ ከፈለገች ሊባኖስ እና ሶሪያ ውስጥ የሚገኙ ቦታዎችን የመሳሰሉ በርካታ አማራጮች አሏት።”

ነገር ግን መደበኛ የሆነ ጦርነት በሁለቱ አገራት መካከል ይቀሰቀሳል የሚለውን ስጋት ግን ቤኔ ይጠራጠሩታል። ለዚህም ኢራን እና እስራኤል የሚጋሩት የየብስ ድንበርም ሆነ ባሕር ጠረፍ ስለሌለ ፊት ለፊት የመዋጋት ዕድል የላቸውም ይላሉ።

ስለዚህም ረጅም ርቀት ተወንጫፊ የጦር መሳሪያዎችን እና የአየር ጥቃቶችን መጠቀም በሁለቱም በኩል ያሉ ዋነኛው አማራጮች ናቸው። ይህ ደግሞ በሁለቱ አገራት መካከል የሉትን የሶሪያን፣ የዮርዳኖስን ወይም የኢራቅን የአየር ክልል መጣስን ይጠይቃል።

በእስራኤል በኩል ከዚህ በፊት እንደምታደርገው ሁሉ ሰላዮቿን በምሥጢር ተልዕኮ አሰማርታ ኢራን ውስጥ ያልተጠበቁ ጥቃቶችን ልትፈጽም የምትችልበት ዕድልም አለ።

ካርታ

‘የኢራን ካርድ’

የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት ታሪቅ ሱሌይማን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግጭት ይባባሳል የሚል ዕምነት የላቸውም።

ነገር ግን በኢራን ላይ የሚደረግ ጦርነትን የሚደግፉ የፓርላማ እና የካቢኔ አባላት ስላሉ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ላይ ጫና ሊያሳድሩ ይችላሉ ይላሉ።

እንዲሁም በተለዋዋጩ የእስራኤል ፖለቲካ ውስጥ “ኔታኒያሁ ፖለቲካዊ መዳከም ባጋጠማቸው ጊዜ የኢራንን ካርድ ሊመዙት ይችላሉ” ሲሉም ያስጠነቅቃሉ።

የእስራኤሉ ሂብሩ ዩኒቨርስቲ ባካሄደው የሕዝብ አስተያየት መለኪያ፣ ሦስት አራተኛ የሚሆኑ እስራኤላውያን አገራቸው በኢራን ላይ የአጸፋ እርምጃ የምትውስድ ከሆነ ከወዳጆቿ ጋር ያላትን የደኅንነት ስምምነትን ስለሚጎዳው ይቃወሙታል።

የሁቲ ተዋጊዎች በቀይ ባሕር ላይ የሚጓዙ የእስራኤል እና የምዕራባውያንን መርከቦች ዒላማ እያደረጉ ነው
የምስሉ መግለጫ,የሁቲ ተዋጊዎች ቀይ ባሕርን በሚያቋርጡ የእስራኤል እና የምዕራባውያን መርከቦችን ዒላማ እያደረጉ ነው

የእጅ አዙር ጦርነት

ምንም እንኳን አስራኤል እና ኢራን እስካሁን ድረስ መደበኛ ጦርነት አድርገው ባያውቁም ሁለቱም አገራት ይፋ ያልወጣ ግጭት ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

ለዚህም በሌሎች አገራት ውስጥ የሚገደሉ የኢራን ቁልፍ ሰዎች በእስራኤል እንደተገደሉ በተደጋጋሚ ይነገራል፤ ኢራን ደግሞ በምትደግፋቸው ቡድኖች አማካይነት እስራኤልን ዒላማ ስታደርግ ቆይታለች።

ወታደራዊው እና ፖለቲካዊው ቡድን ሂዝቦላህ ከሊባኖስ ሆኖ በእስራኤል ላይ ትልቁን የኢራን ጦርነት በእጅ አዙር እያካሄደ ነው። ኢራንም ሂዝቦላህን እንደምትደግፍ አንድም ጊዜ አስተባብላ አታውቅም።

በጋዛ ለሚገኘው ሐማስም የምትሰጠው ድጋፍ ተመሳሳይ ነው። መስከረም 26 ከባድ ጥቃት እስራኤል ላይ የፈጽሞ የለየለት ጦርነት ውስጥ የገባው ሐማስ ለዓመታት ከጋዛ ሰርጥ በእስራኤል ላይ ሮኬቶችን ሲያስወንጭፍ ቆይቷል።

እስራኤል እና ምዕራባውያን አገራትም ለሐማስ የጦር መሳሪያ፣ ተተኳሽ እና ሥልጠና የምትሰጠው ኢራን ናት ብለው ያምናሉ።

በየመን የሚገኙት የሁቲ ታጣቂዎችም ሌላኞቹ የኢራንን የእጅ አዙር ጦርነት የሚያካሂዱ ቡድኖች ናቸው። ሳዑዲ አረቢያም ከሁቲዎች በኩል የሚተኮሱባት ሚሳኤሎች በኢራን የተሠሩ ናቸው ትላለች።

በተጨማሪም በኢራን የሚደረገፉ ቡድኖች በኢራቅ እና በሶሪያ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን አላቸው። ኢራን የሶሪያ መንግሥትን የምትደግፍ ሲሆን፣ በእስራኤል ላይ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች የሶሪያ ግዛት ጥቅም ላይ እንደሚውል ይነገራል።