ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ፍራንሲስ ኦጎላ
የምስሉ መግለጫ,ጀኔራል ኦጎላ ኢታማዦር ሹም ሆነው የተሾሙት ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ነበር።

ከ 2 ሰአት በፊት

የኬንያ መንግሥት የአገሪቷን ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ፍራንሲስ ኦጎላ እና ሌሎች ዘጠኝ መኮንኖችን የገደለውን የሄሊኮፕተር አደጋ መንስኤ ለማወቅ ወደ ሥፍራው መርማሪ ቡድን ላከ።

እስካሁን የአደጋው ምክንያት ግልጽ አይደለም።

ሐሙስ ዕለት ከሰዓት በኋላ ለመብረር ከተነሳ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወዲያውኑ በተከሰከሰው ሄሊኮፕተር ውስጥ ተሳፍረው ከነበሩ 12 መኮንኖች መካከል ጀኔራል ኦጎላ አንዱ ነበሩ።

በአደጋው ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች አስክሬን ወደ ናይሮቢ የተላከ ሲሆን ከአደጋው የተረፉት ሁለት መኮንኖችም በሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው ይገኛል።

ባለ አራት ኮከብ ማዕረጉ ጀኔራል የቀብር ሥነ ሥርዓትም ነገ እሑድ በትውልድ ቀያቸው በምዕራብ ሲያ ካውንቲ እንደሚፈፀም ቤተሰቦቻቸው አሳውቀዋል።

አደጋውን ተከትሎ የሦስት ቀን ብሔራዊ የሐዘን ቀን ያወጁት ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ “ ህልፈታቸው ለአገሪቷ ትልቅ ሐዘንን የፈጠረ ነው” ብለዋል።

ፕሬዚደንቱ ዋና የጦር አማካሪያቸው በግዳጅ ላይ እያሉ ሕይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል።

“ እናት አገራችን ጀግና የሆኑ ጀነራሎቿን፣የጦር መኮንኖቿን፣ ወታደሮቿን አጥታለች” ሲሉ ለኔሽን ጋዜጣ ተናግረዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ራይላ ኦዲንጋም አደጋውን “ የኬንያ አሳዛኝ ቀን” ሲሉ ገልጸውታል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት አሳዛኙን የሄሊኮፕተር አደጋ ተከትሎ ለኬንያ ፕሬዝዳንት፣ መንግሥት እና ሕዝብ” ሐዘናቸውን ገልጸዋል።

ጀኔራል ኦጎላ የኬንያ መከላከያ ኃይል ኢታማዦር ሹም ሆነው የተሾሙት ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ነበር።

በኬንያ መከላከያ ሚኒስቴር ድረ ገጽ ላይ እንደሰፈረው መረጃ ከሆነ ጀኔራል አጎላ እንደ አውሮፓውያኑ ሚያዝያ 24፣1984 ነበር የመከላከያ ኃይልን የተቀላቀሉት።

በዚህም በሚቀጥለው ሳምንት በጦሩ ውስጥ ያሳለፉትን 40ኛ ዓመት ይደፍኑ ነበር።

ጀኔራል ኦጎላ ሥራቸውን የጀመሩት በአገሪቱ አየር ኃይል ውስጥ ሲሆን፣ ከአሜሪካ አየር ኃይል ጋር በተዋጊ አውሮፕላን አብራሪነት መሰልጠናቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ የቀድሞ ጀኔራሉ የምስል መረጃ ደኅንነት ፣ የፀረ ሽብር ጥቃት እና አደጋ ምርመራን በተመለከተ ሥልጠና ወስደዋል።

ከዚያም እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 የአየር ኃይል ኮማንደር ሆነዋል።

ፕሬዚደንት ሩቶ ባለፈው ዓመት ግንቦት በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የበርካቶችን ምክር በመቃወም ጀኔራል ኦጎላን የአገሪቷ ኢታማዦር ሹም አድርገው እንደሾሙ ተናግረዋል።

ፕሬዚደንቱ ከሁለት ዓመት በፊት የተካሄደው የኬንያ ምርጫ ውጤት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ከሞከሩ ቡድኖች ጀኔራሉ አንዱ እንደነበሩም ገልጸዋል።

ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ፍራንሲስ ኦጎላ ወታደራዊ ትዕይንት ላይ

የኬንያ ኢታማዦር ሹም በኃላፊነት ላይ እያሉ ሕይወታቸው ሲያልፍ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ከጀኔራሉ በተጨማሪ በአደጋው ሕይወታቸው ያለፉ መኮንኖች ብርጋዲየር ጀነራል ስዋሌ ሴዲ፣ ኮሎኔል ዱንካን ኬታኒ፣ ሌተናንት ኮሎኔል ዴቪድ ሳዌ፣ ሜጀር ጀኔራል ጆርጅ ቤንሰን ማጎንዱ፣ አብራሪ ሶራ መሐመድ፣ አብራሪ ሒላሪ ሊታሊ፣ ኮንስታብል ክሊፎንስ ኦሞንዲ እና ኮንስታብል ሮስ ያዊራ መሆናቸው ተገልጿል።

የጦር መኮንኖቹ ተደጋጋሚ ጥቃት የሚደርስበትን ሰሜን ኬንያን ጎብኝተው ሲመለሱ ነበር አደጋው የደረሰባቸው።

በሽፍቶች ጥቃቶችን ምክንያት የተዘጉ አንዳንድ ትምህርት ቤቶችን ለማስከፈት ተልዕኮ ላይ ነበሩም ተብሏል። አካባቢውን ለማረጋጋት የተሰማሩ የጦር መኮንኖችንም መጎብኘታቸው ተገልጿል።

በኬንያ ወታደራዊ ሄሊኮፕተር ሲከሰከስ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።

እንደ አውሮፓውያኑ ሰኔ 2021 በዋና ከተማዋ ናይሮቢ አቅራቢያ ሊያርፍ የነበረ ሄሊኮፕተር ተከስክሶ ቢያንስ 10 ወታደሮች መሞታቸው ይታወሳል።