
ከ 3 ሰአት በፊት
ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተፈረመ የመግባቢያ ስምምነት ውዝግብ ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ሁሉንም የውይይት መንገዶች ክፍት እንዲያደርጉ የቡድን ሰባት አገራት ጠየቁ።
በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው ውጥረት እንዳይባባስ ለማድረግ የውይይት መንገዶች እንዲከፍቱ የተጠየቀው የቡድን ሰባት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አርብ ሚያዝያ 11/2016 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ ነው።
አገራቱ በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል ከአራት ወራት በፊት የተፈረመው የባሕር በር የማግኘት የመግባቢያ ስምምነት ስጋት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመካከላቸው ያለውን ውጥረት ለማርገብ በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ፣ ከቀጣናው አጋሮች ጋር በመተባበር በሁለትዮሽ መገናኛ መንገዶች ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
አገራቱ የዓለም አቀፍ ሕግ እና በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር ላይ በተደነገገው የሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መርሆዎች መሠረት ልዩነታቸውን ሊፈቱ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የቡድን ሰባት አገራት ይህንን መግለጫ ያወጡት ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማቋረጥ የኢትዮጵያ አምባሳደር እና ዲፕሎማቶች አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ፣ እንዲሁም አምባሳደሯን ወደ ሞቃዲሾ በቅርቡ ከመለሰች በኋላ ነው።
የቡድን ሰባት አገራትን የውይይት መንገዶች ክፍት አድርጉ ጥሪ ተከትሎ መግለጫ ያወጣችው ሶማሊያ በበኩሏ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም እና ደኅንነትን ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መሆኗን አርብ ዕለት ባወጣችው መግለጫ ገልጻለች።
ነገር ግን ሶማሊያ ግዛቴ ናት ከምትላት ሶማሊላንድ ጋር ኢትዮጵያ የገባችውን ስምምነት ማፍረሷን ለውይይቱ እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣለች።
“ኢትዮጵያ ከሰሜናዊ የሶማሊያ ክልል [ሶማሊላንድ] ጋር የፈረመችውን ሕገወጥ የመግባቢያ ስምምነት እስካላፈረሰች ድረስ እንዲሁም የሶማሊያን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት መርህ እስካላከበረች ድረስ ውይይት የማይቻል ነው” ብላለች ሶማሊያ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በቡድን ሰባትም ሆነ በሶማሊያ መግለጫዎች ላይ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
- ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ውጥረት ለማርገብ ኬንያ ያቀረበችው የባሕር ጠረፍ ስምምነት ሃሳብ የለም አለች13 ሚያዚያ 2024
- ሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ከሞቃዲሾ በ72 ሰዓት እንዲወጡ አዘዘች፣ አምባሳደሯን ከአዲስ አበባ ጠራች4 ሚያዚያ 2024
- የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ውዝግብ ለምን ተካረረ?6 ሚያዚያ 2024
ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።
ኢትዮጵያ በዚህ ስፍራ የባሕር ኃይል ሰፈር እንደምታቋቁም እና በምትኩ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ትሰጣለች መባሉን ተከትሎም እንደ ግዛቷ አካል የምታያት ሶማሊያ ጉዳዩን ወደ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች እስከ መውሰድ አድርሷታል።
ከሶማሊያ በኩል ተደጋጋሚ ክሶች እና መግለጫዎች ከመቅረባቸው በተጨማሪም ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትም ወስዳዋለች።
የቡድን ሰባት አገራት ከሁለቱ አገራት ውጥረት በተጨማሪ ኢትዮጵያንም አስመልክቶ በአገሪቱ የተለያዩ ማዕዘናት እየተፈጠሩ ያሉ የማያቋርጡ ግጭቶች ስጋት እንደጫረባቸውም ገልጸዋል።
በኢንዱስትሪ የበለጸጉት አገራቱ በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረገው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት እንደ በጎ ቢያዩትም፤ በአገሪቱ አሁንም ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ እና የምግብ ዋስትና እጦት መስፋፋት እንዳሳሰባቸውም ገልጸዋል።
በአገሪቱ በሰብዓዊ መብቶች፣ የሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ፣ ውጥረቶችን ለመፍታት የሚደረጉ ፖለቲካዊ ውይይቶች፣ እርቅ እና ብሔራዊ ውይይት፣ የሽግግር ፍትህ እንዲሁም በግጭቱ ወቅት ለተፈጸመው ወንጀሎች ተጠያቂነትን ማስፈን ዘላቂ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እንደሚያበረታቱ ጠቅሰዋል።
በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች በግጭት የሚሳተፉ አካላት ሰላምን በውይይት ለማምጣት ተመሳሳይ ቁርጠኝነት እንዲያሳዩም ጠይቀዋል።
በግጭት የተጎዱ ሕዝቦች የሚያገገግሙበት እና የመልሶ ግንባታ ድጋፍ እንዲጠናከር፣ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታታት እና መልሶ ከማኅበረሰቡ ጋር በማዋሃድ እንዲሁም ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሄ በማበጀትም ከተገኘው ሰላም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በጣሊያኗ ኬፕሪ ደሴት ከሚያዝያ 9 – 11/2016 ዓ.ም. ድረስ በተደረገው የቡድን ሰባት አገራት ጉባኤ የካናዳ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የጃፓን፣ የዩናትድ ኪንግደም እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ተወካይ ተሳትፈዋል።
አገራቱ በውጥረት ላይ ካሉት ሁለቱ የአፍሪካ ቀንድ አገራት በተጨማሪ በሊቢያ፣ በሱዳን፣ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ያሉ ግጭቶችን እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን አንስተው መወያየታቸው ተገልጿል።