መርካቶ

ከ 4 ሰአት በፊት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከወሰዷቸው ጉልህ እርምጃዎች መካከል የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለውጭ ገበያ ክፍት ማድረግ ሊጠቀስ ይችላል።

ከሦስት ዓመት በፊት የቴሌኮም ዘርፉ መከፈትን ተከትሎ፣ ሳፋሪኮም የኢትዮጵያን ገበያ መቀላቀሉ ይታወሳል።

በተመሳሳይ ከአንድ ዓመት ከስምንት ወራት በፊት የባንክ ዘርፍን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ የቀረበ ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የእነዚህ ተከታታይ ውሳኔዎች ተከታይ የሆነ ሌላ የፖሊሲ ውሳኔ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል።

ይህም ውሳኔ የውጭ ባለሃብቶች በወጪ ንግድ፣ በገቢ ንግድ፣ በጅምላ ንግድ እና በችርቻሮ ንግድ ላይ እንዲሳተፉ የሚፈቅድ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የኢንቨስትመንት ቦርድ ይህን ውሳኔ ወደ መሬት የሚያወርድ መመሪያ አውጥቷል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርም ሐሙስ ሚያዚያ 10/2016 ዓ.ም. በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዘርፎቹ ከውጭ ባለሃብቶች ተከልለው መቆየታቸውን ተቋማቱ በሰጡት መግለጫ እና በመመሪያው መግቢያ ላይ ተጠቅሷል።

መግለጫው የዘርፎቹን መከለል አመክንዮ “የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ከውጭ ባለሃብቶች ውድድር ጫና እንዲጠበቁ በማድረግ ካፒታል እንዲያፈሩ ዕድል ለመስጠት፤ ከዓለም አቀፉ የንግድ ትሥሥር ሥርዓት ጋር እንዲተዋወቁ እና ልምድ እንዲቀስሙ የታለመ እና በውስጥ አቅም ላይ የተመሠረተ ዘለቂ ኢኮኖሚ የመገንባት አገራዊ ዓላማ የያዘ ነው” ይላል።

መግለጫው አክሎም ዘርፎቹን ለውጭ ተሳታፊዎች የመዝጋት ፖሊሲ “በተገቢው መጠን የሚፈለገውን ዓላማ አሳክቷል ማለት አይቻልም” ይላል።

በተጨማሪም “ከለላ በተሰጣቸው ዘርፎቹ ሰፊ የአገልግሎት ተደራሽነት፥ የጥራት እና የብቃት ችግሮች አጋጥመዋል” ሲል መግለጫው የታሰበው ውጤት አለመሳካቱን ያትታል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊርማ የጸደቀው መመሪያም “እስካሁን የተመዘገቡ ውስን ውጤት ቢኖሩም የፖሊሲው ዓላማ በተጠበቀው መጠን” አለመሳካቱን ይገልጻል።

ይህን ተከትሎም ፍቃደኛ ለሆኑ እና አቅም ላላቸው የውጭ ባለሃብቶች ዘርፉን መክፈት እንዳስፈለገ ያትታል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ለዚህ የመንግሥት ውሳኔ የተለያየ አስተያየት ይሰጣሉ።

የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉ እና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ፤ “መከፈቱ ራሱ የሚባለውን ችግር ለመቅረፉ እርግጠኛ መፍትሔ አይደለም” ይላሉ።

“በኢትዮጵያ የሚታየው ገበያን ለውጭ [ባለሀብት] ክፍት ማድርግ የሁሉም ነገር መፍትሔ ነው የሚል አመለካከት በጣም ችግር ነው” የሚሉት ባለሙያው፤ “መክፈትን የነገሮቻችን ሁሉ መፍቻ ቁልፍ አድርገን መመለከታችን ትልቅ ስህተት ነው” ሲሉ ይሞግታሉ።

የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ባለሙያ የሆኑት አብዱልመናን መሐመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በመመሪያው የተጠቀሱት ችግሮች በሁለት መንገድ ሊፈቱ ይችላሉ ይላሉ።

ከእነዚህ መፍትሔዎች መካከል አንደኛው ውድድር መሆኑን የሚያነሱት አብዱልመናን (ዶ/ር) ሌላኛው መፍትሔ የመንግሥት ቁጥጥር መሆኑን ያነሳሉ።

አብዱልመናን “ምንም ጥሩ ሕግ ቢኖርም እንኳን፣ ውድድር በሌለበት ገበያ ችግር አለ። ውድድር በተወሰነ ደረጃ ችግሮችን ይፈታል” ሲሉ በገበያው ውስጥ የውድድር መኖርን አስፈላጊነት ያብራራሉ።

ዘርፎቹ ለውጭ ባለሃብቶች ተዝግተው መቆየታቸውን የሚያስታውሱት አብዱልመናን፤ “ምንም ያመጡት የረባ ለውጥ እንኳን የለም። መክፈቱ ተገቢ ነው ግን ውጤት ያመጣል፣ አያመጣም ሌላ ጉዳይ ነው” ይላሉ።

መርካቶ

የውጭ ባለሃብቶች መግባት በረከት ወይስ መርገምት?

የአገሪቱ ኢኮኖሚ ለውጭ ባለሃብቶች መከፈት “በረከት ይዞ ይመጣል ወይስ መርገምት?” የሚለው ክርክር በተደጋጋሚ ይሰማል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሌሎች ሹመኞቻቸው የመንግሥት ውሳኔ “ኢኮኖሚውን ለማሻሻል” የሚደረግ እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣሉ።

በወጪ እና ገቢ ንግድ ላይ የውጭ ባለሃብቶች መግባት ምን ያህል የተፈለገውን ውጤት ያመጣል የሚለው ዋነኛ ጥያቄ ነው።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋነኛ መገለጫ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንደኛው የወጪ እና ገቢ ንግድ አለመመጣጠን ነው።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የኢኮኖሚ ባለሙያ የዚህ አለመመጣጠን ዋነኛ ምክንያት፤ “የምርት ሰንሰለቱ ላይ ያለ ችግር ነው። ግን ደግሞ ኤክስፖርት ማድረግ ያለመቻላችን መሠረታዊ ችግር በምርታማነት ዙሪያ ያከናወንናቸው ሥራዎች ያን ያህል ስኬታማ መሆን ባለመቻላቸው የተነሳ የመጣ ነው” ይላሉ።

ባለሙያው የውጭ ባለሃብቶች ወደ አገር ውስጥ መግባት በወጪ ንግዱ ላይ ይህ ነው የሚባል ጉልህ ለውጥ ላያመጣ ይችላል የሚል እምነት አላቸው።

ባለሙያው “ከፍ ያለ ካፒታል ያላቸው ኢንቨስተሮች ሊመጡ ይችላሉ፤ ነገር ግን አገሩ ማምረት ካልቻለ በጣም አስቸጋሪ ነው። ያለችውን ምርት ወደ መቀራመት የሚያመራ ሊሆን ይችላል” ይላሉ።

የእነዚህን የውጭ ባለሃብቶች ፍላጎት ለማሟላት የምርት ሥርዓቱ የተወሰነ ዓይነት ምርቶች ላይ ሊያተኩር ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ባለሙያው ይገልጻሉ።

“ይህ ምናልባት በአጭር ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኝ ይችላል” የሚሉት ባለሙያው፤ “በረዥም ጊዜ ግን የኤክስፖርት ዘርፉን ይጎዳዋል። አሁን ካለው የምርት ዓይነት እየቀነሰ ነው የሚሄደው” ሲሉ ስጋታቸውን ለቢቢሲ አጋርተዋል።

አብዱልመናን መሐመድም በተመሳሳይ ወጪ ንግድ ዋነኛ ችግሩ የባለሃብቶች ብቻ ሳይሆን “የምርት ችግር ነው” ባይ ናቸው።

መመሪያው በወጪ ንግድ ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ ባለሃብቶች ሊያሟላቸው የሚገቡ መስፍረቶችን በዝርዝር አስፍሯል።

ጥሬ ቡናን ለውጭ ገበያ ለማቅርብ የሚፈልግ የውጭ ባለሃብት፤ ላላፉት ተከታታይ ዓመታት በዓመት በአማካይ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቡና ከኢትዮጵያ የገዛ መሆን አለበት። በተጨማሪም ፈቃዱን ባገኘበት ዓመት 10 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቡናን ለመላክ ውል መግባት አለበት።

የቅባት እህልን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚፈልግ ባለሃብት ባለፉት ሦስት ዓመታት በየዓመቱ አምስት ሚሊዮን የሚያወጣ የቅባት እህል የገዛ መሆን እንዳለበት መመሪያው ላይ ሰፍሯል።

በጫት ንግድ ለሚሰማራ ባለሃብት ደግሞ የገንዘብ መጠኑ ወደ አንድ ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ይላል። በመመሪያው መሠረት የቁም እንስሳትን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚፈልግ የውጭ ባለሃበት የግዢ ታሪክ እንዲኖረው አይገደድም።

ነገር ግን የአገሪቱ የማምረት አቅም ዝቅተኛ መሆን የውጭ ባለሃብቶች የገቢ ንግድ ላይ እንዲያተኩሩ ሊያደርጋቸው እንደሚችል የኢኮኖሚ ባለሙያው ይናገራሉ።

የውጭ ባለሃብቶች ከወጪ ንግድ በተጨማሪ ከማዳበሪያ እና ከነዳጅ በስተቀር በገቢ ንግድ ላይ እንዲሳተፉም በመመሪያው ተፈቅዶላቸዋል።

መርካቶ

የመርካቶ ዘመን እያበቃ ይሆን?

መመሪያው የውጭ ባለሃብቶች በጅምላ እና ችርቻሮ ንግድ ላይ እንዲሳተፉ ይፈቅዳል። ከማዳበሪያ የጅምላ ንግድ በስተቀር ማንኛውም የውጭ ባለሃብት ለአገር ውስጥ ተከልለው የነበሩ የጅምላ ንግድ መስኮች ላይ መሰማራት ይችላል።

ስማቸው ሳይጠቀስ ለቢቢሲ ሃሳባቸውን ያጋሩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያ “የጅምላ እና ችርቻሮ ንግድ ዋናው ችግር የአቅርቦት ሰንሰለት ትስስር ነው” ይላሉ።

ባለሙያው የአቅርቦት ሰንሰለቱን አቀናጅቶ አገልግሎት መስጠት የሚችል ሥርዓት መፍጠር አዳጋች መሆኑንም ያነሳሉ። ይህን ችግር ለመቅረፍ የኢትዮጵያ መንግሥት ያቋቋመው “አለ! በጅምላ” በአጭር መቅረቱን ያስታውሳሉ።

በጅምላ ንግድ ላይ ለመሳተፍ የሚመጡ የውጭ ባለሃብቶች፤ “የአቅርቦት ሰንሰለቱን ሊያቀናጁት ይችላሉ” ይላሉ። ነገር ግን በእነዚህ ባለሃብቶች መግባት የአገር ውስጥ የጅምላ ነጋዴዎች “ከጨዋታ የሚወጡበት ዕድል በጣም ሰፊ ነው” የሚል ስጋት አላቸው።

አብዱልመናንም በተመሳሳይ የ“አለ! በጅምላ”ን ተሞክሮ አስታውሰው፤ ነገር ግን “ምንም ሳያሳካ የት እንዳለ እንኳን አይታወቅም” ይላሉ።

“የኢትዮጵያ መንግሥት ዘርፉን መክፈቱ ጥሩ ሆኖ ሳለ በሕግ ብቻ በመቀመጡ ለውጥ ይመጣል ማለት አይደለም” የሚሉት አብዱልመናን “መመሪያው ስለወጣ ብቻ ባለሃብቶች ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ ማለት አይደለም” ይላሉ።

በመመሪያው መሠረት የውጭ ባለሃብቶች ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች በተከለሉ ሁሉም የችርቻሮ ንግድ ሥራዎች ላይ መሳተፍ ይችላሉ። በዚህ ዘርፍ ላይ ለመሳተፍ ባለሃብቶች በመንግሥት የተቀመጠውን ወለል ስፋት እና አጠቃላይ የሚመለከቱ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።

የኢኮኖሚ ባለሙያው የውጭ ባለሃብቶች በችርቻሮ ንግድ ላይ መሳተፍ “በአጭር ጊዜ የዋጋ ልዩነት ሊያመጡ ይችላሉ” ይላሉ። ነገር ግን በጊዜ ሂደት “እነዚህ ትልልቅ የችርቻሮ ነጋዴዎች አቅርቦቱን እና ሸማቹን አንድ ጊዜ ከጠቀለሉ በኋላ ግን እነሱ በሚያስቀምጡት ዋጋ ነው ሰዉ የሚገዛው” ሲሉ የውሳኔውን ሌላ መልክ ያስረዳሉ።

“የዋጋ መረጋጋት ይመጣል ቢባልም የሚመጣው ለአጭር ጊዜ ነው፤ እነሱ የአቅርቦት ሰንሰለቱን እስከሚጠቀልሉት ድረስ ነው” የሚል ስጋታቸውንም አጋርተዋል።

ባለሙያው አክለውም፤ “ይህ ነገር መከፈቱ፣ የመርካቶ ዘመን እያበቃ ሊሆን ይችላል” ሲሉ የአገሪቱ የችርቻሮ ንግድ እምብርት የሆነው መርካቶ እና ነጋዴዎች ከገበያ ሊወጡ የሚችሉበት ዕድል መኖሩን ያስረዳሉ።

ባለሙያው አክለውም “የመርካቶ ነጋዴ በኢምፖርት [ገቢ] ንግድ ላይ ነው የተሰማራው። ኢንፖርተሮች [አስመጪዎች] ሲመጡ መርካቶ ብዙ ከጨዋታ የሚወጡ ተዋናዮች ይኖሩታል” ሲሉ ይሰጋሉ።

አብዱልመናን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ “ለሸማቹ በቅርብ ጊዜ የሚመጣ መፍትሔ ይኖራል ብለን ተስፋ ባናደርግ ጥሩ ነው” ይላሉ።

አነስተኛ የችርቻሮ ሱቅ

የውጭ ባለሃብቶች ወደ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ በሚኖረው ውድድር፤ “አንደኛ ተጠቃሚው ሸማቹ ነው” የሚሉት አብዱልመናን፤ “ውድድር በሚኖርበት ጊዜ ደግሞ የአገሪቱ ኢኮኖሚም ይጠቀማል። መንግሥትም ይጠቀማል ታክስ ያገኛል” በማለት ሌላኛውን ገጽ ያስረዳሉ።

የአገር ውስጥ ነጋዴዎችን በተመለከተም፤ “በቀላሉ ከገበያ ይወጣሉ ብዬ አላስብም” ይላሉ።

ዶ/ር አብዱልመናን “ማንም ሰው ሕይወቱን በውድድር እንደሚመራው ንግዱም በውድድር መሆን አለበት፤ ጥበቃ እየተደረገላቸው ዘላለም መቆየት ያለባቸው አይመስለኝም” ሲሉ ያክላሉ።

“የአገር ውስጥ [ባለሃብት] ከገበያ ቢወጣ ሌላው የውጭ ኢንቨስተር ይመጣል” የሚሉት ዶ/ር አብዱልመናን፤ የውጭዎቹ ዋጋ መጨመር በሚጀምሩበት ጊዜ የአገር ውስጡ አሁንም ወደ ገበያው መግባት ይችላል” ይላሉ።

ከዚህ በተጫማሪም “የማይገባ ውድድሮች በሚስተዋሉበት ወቅት” የመንግሥት ጠንካራ ቁጥጥር ያስፈልጋል ሲሉም ያክላሉ። ይህን የመንግሥትን ቁጥጥር ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ፤ “የመንግሥት የተቋማት ላይ ማሻሻያ መደረግ አለበት።”

ስማቸው አንዳይጠቀስ የጠየቁት ባለሙያ፤ “እኔ እንደ ባለሙያ ኢኮኖሚው ተዘግቶ ይቆይ የሚል ሃሳብ የለኝም፤ ነገር ግን ሌሎች ከከፈቱ ኢኮኖሚዎች፣ ከፍተው ማስተዳደር ካቃታቸው ኢኮኖሚዎች፣ አቅቷቸው ብቻ ሳይሆን በጫና ውስጥ ከሚኖሩ ኢኮኖሚዎች መማር አለብን። ምን ዓይነት ነገሮች ነው ማድረግ ያለብን? አገሬው ኢኮኖሚውን ተቆጣጥሮት እንዲቀጥል ምንድን ነው ማድረግ የሚገባን? የሚለውን በጥንቃቄ ማየት አለብን” ሲሉ ያሳስባሉ።

ለዚህም የሚያቀርቡት አንዱ ምክረ ሃሳብ፤ “ትልልቅ የችርቻሮ ባለሀብቶች ሲመጡ ከአገር ውስጥ የጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት እንዲገዙ የሚያስገድዱ ወይም ደግሞ ጫና የሚያሳድሩ የሕግ ማዕቀፎችን ማስቀመጥ” የሚል ነው።

የአገሪቱ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ሁኔታ የሚኖረው ሚና

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለቱም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች መመሪያው ተግባራዊ መሆን ጀምሮ የውጭ ባለሃብቶች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መሻሻል ያለባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ያነሳሉ።

አብዱልመናን (ዶ/ር)፤ “የውጭ አገር ባለሃብት ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ ኢንቨስት ለማድረግ የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ ይጠይቃል” ይላሉ።

“እነዚህ ነገሮች ባልተሟሉበት ሁኔታ ወረቀት ላይ ነገሮች ስለሰፈሩ ለውጥ ይመጣል ማለት አይደለም” ሲሉም በአንድ ጀንበር የውጭ ባለሃብቶች ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ ማለት እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

ሌላኛው የኢኮኖሚ ባለሙያ ደግሞ፤ እንደ ኢኮኖሚ የውጭ ባለሃብቶች እንዲመጡ “የማያበረታቱ ሁኔታዎች” መኖራቸውን ያነሳሉ።

ከእነዚህ ሁኔታዎች መካከል አንደኛው የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ነው። “እነሱ ያተረፉትን በቀላሉ ማውጣት የሚችሉበት የፋይናንስ ዘርፍ አይደለም ያለው።

“ይህ ሁኔታ ካልተቀየረ የውጭ ባለሃብቶች በቀላሉ መምጣት አይችሉም” የሚሉት ባለሙያው፤ “እኛ ደግሞ እነሱን መቀየራችን የገንዘብ ፍልሰትን በመቆጣጠር ረገድ ያለንን አቅም ይቀንሳል” ሲሉ ይናገራሉ።

አብዱልመናንም ከዚህ ሀሳብ ጋር በመስማማት “አንድ ባለሃብት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ኢንቨስት ካደረገ በኋላ ገንዘቤን ላውጣ ሲል የውጭ ምንዛሬ ሁኔታ የምናውቀው ነው ትልቅ ራስ ምታት ሆኗል” ይላሉ።