ዮናስ አማረ

April 21, 2024

‹‹ሐሳብ ማቅረብ ባልተገባ መንገድ የሚያስበይን ከሆነ እንደ አገር በአጠቃላይ የሳትነው ነገር አለ ብዬ እገምታለሁ›› ደስታ ጥላሁን፣ የኢሕአፓና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

ቆይታ

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ‹‹እርስዎ ንጉሥ ነዎት ወይስ ጠቅላይ ሚኒስትር?›› የሚል ጥያቄ እንዳቀረበች በሰፊው ሲወራ ሰንብቷል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉት የቅርቡ የግማሽ ቀን ውይይት በአንድ ሰዓት ከ40 ደቂቃ ተመጥኖ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ብቻ በመተላለፉ፣ እሷን ጨምሮ ጠያቂ ፖለቲከኞች ለዓብይ (ዶ/ር) ያነሱትን ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ ለማወቅ ከባድ ነበር፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና ማኅበራዊ ዓምዶች ወጣቷ ፖለቲከኛ ደስታ ጥላሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩን አፋጠጠች እየተባለ ስለሚነገረውም ሆነ፣ በውይይቱ ወቅት ስለገጠማት ነገር በተመለከተ ሰፊ ቆይታ ከሪፖርተር ጋር አድርጋለች፡፡ ከዚህ ቀደም የሪፖርተር ቆይታ ዓምድ እንግዳ የነበረችው የኢሕአፓና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የሆነቸው ደስታ፣ ከዚህ በተጨማሪም ወቅታዊ አገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮችን በተመለከተ ለተነሱላት ጥያቄዎችም ምላሾችን ሰጥታለች፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የውይይት መድረክ ላይ የነበረውን ሁኔታ፣ እንዲሁም ስለሰላማዊ ፖለቲካ ሰፊ ገለጻ ያደረገችበት ከዮናስ አማረ ጋር ያደረገችው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ፈተና ምን ይመስላል?

ደስታ፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች ፈተና ብዬ ከምገመግማቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱና ዋናው የፖለቲካው ዓውድ በጣም መጥበቡ ነው፡፡ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ልብ ተንቀሳቅሰው፣ አባላት አደራጅተውና ሀብት አሰባስበው ራሳቸውን ለማጠናከርም ሆነ በነፃነት ሐሳባቸውን ለሕዝብ አቅርበው መንቀሳቀስ እየቻሉ አይደለም ብዬ ነው የማስበው፡፡ የፖለቲካ ዓውዱ ከቀደመውም ጊዜ በባሰ ደረጃ መጥበቡ አንዱ ችግር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከግለሰቦችም ሆነ ከሌሎች ምንጮች ፋይናንስ ማሰባሰብ አለመቻሉ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ፖለቲካ ፓርቲዎች ከባለሀብቶች፣ ከድርጅቶች ወይም ከሌላ የገንዘብ ምንጮች ሀብት ማሰባሰብ እንዳይችሉ በሕግ ተገድቧል፡፡ ይህ ደግሞ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከመሪው ፓርቲ ጋር ለመፎካከር ራሳቸውን ለማጠንከር አልቻሉም፡፡ መሪው ፓርቲ ደግሞ የመንግሥትንም ሀብት ይጠቀማል፡፡ ይህም በገዥውና በተፎካካሪ ድርጅቶች መካከል ያለውን የፉክክር ልዩነት ያሰፋዋል፡፡ በሌላ በኩል የፖለቲካው ከባቢ አየር መካረሩም ከባድ ጉዳት አለው፡፡ ወደ መካከል መጥተው ሐሳባቸውን ሰብሰብ አድርገው ተወያይተው የጋራ በሆኑ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት እንዳይፈጥሩ ይህ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ነባሩ የፖለቲካ ባህላችን ይዞት በመጣው ነውጠኝነት፣ እልህና ግጭት አዘውታሪነት የተሞላ እንጂ በሰከነ የጠረጴዛ ውይይት የሚመራ አለመሆኑም ትልቅ ችግር ነው፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ሁኔታዎች ለሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ፈተና ናቸው፡፡ ሆኖም መንግሥት በሆነው በገዥው ፓርቲ የሚፈጠሩ ጫናዎች ደግሞ በተፎካካሪ ድርጅቶች ላይ ተጨማሪ ተፅዕኖ አላቸው፡፡ ገዥው ፓርቲ የሚፎካከሩትን ፓርቲዎች በማሰር፣ ሐሳባቸውን በነፃነት እንዳይገልጹ በማድረግ፣ መግደልን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ጫና ያደርጋል፡፡ አንድ ሰው የተለየ ፖለቲካ ሐሳብ ይዞ ወደ ፖለቲካ መስክ መግባቱ በራሱ ለተለያዩ ጫናዎች ራስን ማጋለጥ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የኢሕአፓ ሊቀመንበርን ጨምሮ የአባሎቻችሁ መታሰርን በተመለከተ በምን ሁኔታ ላይ እንደምትገኙ ብትነግሪን?

ደስታ፡- ብዙ አባሎቻችን እየታሰሩ ነው ያሉት፡፡ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ጭምር በብዛት እየታሰሩ ነው፡፡ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንታችንም ከወራት እስራት በኋላ በቅርቡ ነው የተፈቱት፡፡ ብዙ አባሎቻችን መታሰር፣ መዋከብና መንገላታት እየገጠማቸው ነው፡፡ ፕሬዚዳንታችን ዝናቡ አበራ በታሰሩ ዕለት የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ስለነበረን ወደ ቢሮ እያመራሁ ነበር፡፡ ከረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢ ነው ከቢሮ የወሰዷቸው፡፡ ቢሮ ስደርስ ወስደዋቸዋል፡፡ ወደ እኛ ልደውልና ነገሩን ልናገር እያሉ ተከልክለው፣ እንዲሁም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሌለበት ሁኔታ ነው የተወሰዱት፡፡ ለተወሰኑ ቀናት አዲስ አበባ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ስለነበር እየሄድን እናያቸው ነበር፡፡ ጠበቃም ለማቆም የሞከርን ሲሆን ፍርድ ቤትም ቀርበው ነበር፡፡ ፖሊስ የ13 ቀናት ቀጠሮ ጠይቆባቸው ተፈቅዶለት የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ሰኞ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ቀጠሮ ነበር፡፡ በቀጠሮው ቀን ፍርድ ቤት የተገኘን ቢሆንም ሆኖም ሳያቀርቧቸው ቀርተዋል፡፡ በቦታው ስንጠይቅ ወደ አዋሽ አርባ እስር ቤት መወሰዳቸው ነው የተነገረን፡፡ ይህ አግባብ እንዳልሆነ በመጥቀስ ሊቀመንበራችን እንዲፈቱ በመጠየቅ ለሚዲያዎች መግለጫ ሰጥተናል፡፡ መሪያችን ከፍተኛ ደም ግፊትና ስኳር አለባቸው፡፡ አመጋገባቸውና የእስር ሁኔታቸው ለከፍተኛ የጤና ችግር ሊዳርጋቸው ስለሚችል ሁኔታው ያሳስበናል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት የፕሬዚዳንታችንን መፈታት እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ፣ ከብሔራዊ ምክክር ውይይት መድረኮች ልንወጣ እንደምንችል ጠቅሰን ለኮሚሽኑ አሳውቀናል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሕአፓ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቀነጨረ ድርጅት የሚል ስም ሲሰጠው ይሰማል፡፡ በእርግጥ ቀንጭሯል?

ደስታ፡- አንድ ድርጅት በ50 ዓመቱ እንዴት ይቀነጭራል? እንግዲህ ኢሕአፓ ከተመሠረተ 52 ዓመታት ገደማ እየሆነው ነውና እንደውም ቀነጨረ ሳይሆን አበበ ቢባል ነው የተሻለ የሚሆነው፡፡ ሞተ ወይም ጠፋ ከተባለበት ተነስቶ እንዲያውም ከቀደመው በበለጠ አባላት እያደራጀና ራሱን እያጠናከረ ነው፡፡ ለውጥ መጣ በተባለበት ወቅት ከውጭ ከተመለሱ ፓርቲዎች አንዱ ነው ኢሕአፓ፡፡ በስደት በነበረበት ወቅትም ቢሆን ለአገር መቆሙን ሳይተው መቀጠሉ ይታወሳል፡፡ ከሁሉም ተፎካካሪ ድርጅቶች ጀርባ ሆኖ ቅንጅትም በለው ኅብረትም ቢሆን፣ ሌሎችም ለዴሞክራሲ ሲታገሉ ለቆዩ ድርጅቶች በማማከር፣ በመርዳት፣ በማጠናከርና በገንዘብም ሆነ በሞራል በመደገፍ ነው የሚታወቀው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ግንባር ቀደም የአገሪቱ ፓርቲ እንደ መሆኑ መጠን በብዙ ውጣ ውረዶች አልፎ እስካሁን ድረስ መቆየት መቻሉ ነው እኔን  የሚያስገርመኝ፡፡ እንደገናም የትውልድ ሽግግርና ለውጥ አድርጎ አዲስ ሐሳብ ባነገቡ የአዲሱ ትውልድ ኃይሎች እየተንቀሳቀሰ ያለ ድርጅት መሆኑ እየታወቀ እንዴት ቀነጨረ እንደሚባል አላውቅም፡፡ እናንተ ጋዜጠኞችም እንደዚህ ያሉትን ሰዎች ነው መጠየቅ ያለባችሁ እንጂ እኛን አይደለም፡፡ እንደቀነጨርንና እንዳልቀነጨርን ለማወቅ ድርጅታችንን መጥቶ መጎብኘት ይቻላል፡፡ አባላቶቻችንን ማየት ያስፈልጋል፡፡ በአመራርም በአባላትም ጠንካራ ስብጥር ያለው ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ለገጠሟት ከባድ ችግሮች መፍትሔ የሚላቸውን ሐሳቦች በማዋጣት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ኢሕአፓ ቀነጨረ የሚባለው እኔ አይገባኝም፣ አይዋጥልኝምም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሕአፓ ከሞተ ቆይቷል፣ አብቅቶለታል፣ ለዚህ ዘመን የሚመጥን አጀንዳም የለውም ይባላል እኮ?

ደስታ፡- አንድ ድርጅት ሐሳብ ይዞ ነው የሚታገለው፡፡ ኢሕአፓ ለዚህ ዘመን የሚመጥን አጀንዳ የለውም ለሚለው የያዛቸውን ሐሳቦች ማየት ያስፈልጋል፡፡ ቀድሞ ሲታገል የነበረው ሶሻሊዝምን መሠረት አድርጎ ነው፡፡ ከተመሠረተ በአሥረኛ ዓመቱ ወይም በሦስተኛው ጉባዔ የሶሻሊዝም አስተሳሰቡን ወደ ሶሻል ዴሞክራሲ ቀይሮ ላለፉት 45 ዓመታት ሶሻል ዴሞክራሲን መሠረት አድርጎ ነው ሲታገል የቆየው፡፡ ስለዚህ ርዕዮተ ዓለማችን ለኢትዮጵያ ይመጥናል፡፡ በተለይ አሁን ኢትዮጵያ ላለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አዋጭ መንገድ ነው ብለን እናስባለን፡፡ የኢኮኖሚው ኢፍትሐዊነት፣ የፖለቲካውና የፕሬስ ነፃነት መታፈን፣ ማኅበራዊ መስተጋብራችን መላላቱ ሁሉ ሶሻል ዴሞክራሲን የሚጠይቅ መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ አንድነትንና መሰባሰብን ከማጠናከር አንፃር፣ የፍትሕ መጓደልን ከመቅረፍ አንፃር፣ እኩልነትንም ተመጣጣኝነትንም ከመተግበር አንፃር ሶሻል ዴሞክራሲን የተሻለ መፍትሔ ያለው ርዕዮተ ዓለም ነው እንላለን፡፡ ስለዚህ ኢሕአፓ ለአሁኑ ዘመን የሚመጥን አጀንዳ የለውም የሚለውን አልቀበለውም፡፡ ወደፊት በሰፋፊ  ግብርና ልማቶች ራሳችንን ካጠናከርን፣ ትልልቅ አገር በቀል ባለሀብቶችን ካፈራንና ኢኮኖሚውን ካጠናከርን በኋላ በኢንዱስትሪ የበለፀጉት አገሮች እንደሚያደርጉት ሁሉ ለዘብተኛ ሊበራሊዝም እያልን፣ ቀስ በቀስ ወደ ሊበራሊዝም ልንሸጋገር እንችላለን፡፡ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ግን ሶሻል ዴሞክራሲ አስፈላጊ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ከሰሞኑ ውይይት ነበራቸው፡፡ ውይይቱን እንዴት ገመገምሽው? ፍሬያማ ነበር? ፓርቲዎቹ አጋጣሚውን በሚገባ ተጠቅመውበታል? እሳቸውስ ለተነሱ ጥያቄዎች የአገሪቱን ችግር በሚመጥን መንገድ ምላሽ ሰጥተውባቸዋል?

ደስታ፡- ውይይቱ በግሌ አስፈላጊ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደ ኢሕአፓ አመራርም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ውስጥ እንደሚገኝ አመራር ውይይቱ አስፈላጊ መርሐ ግብር ነበር እላለሁ፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በተደጋጋሚ ጠያቂነት ነው የተዘጋጀው፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ጠይቀናል፡፡ አጀንዳችሁ ምንድነው ተብለን የሰላም ጉዳይ የሚል መልስ ስንሰጥ ከሰላም ሚኒስቴር ክቡር ሚኒስትሩ መጥተው አወያይተውናል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩና የገንዘብ ሚኒስትሩም መጥተው በኢኮኖሚ ጉዳዮች አወያይተውናል፡፡ ይሁን እንጂ የአገሪቱ ችግሮች ስላልተፈቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ብናደርግ፣ በተለይም ለአንገብጋቢ የሰላም ጉዳዮች አቅጣጫ ቢቀመጥ የሚል ውትወታ በተደጋጋሚ ስናቀርብ ቆይተናል፡፡ ይህን ተከትሎም ነው አጋጣሚው የተፈጠረው፡፡ አጋጣሚው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይቶች በሚያደርጉበት ወቅት የተከሰተ ቢሆንም፣ ነገር ግን በእኛ ጠያቂነት ነው የተፈጠረው፡፡ ውይይቱ በተፈለገው መንገድ የሄደ ነበር ወይ የሚለውን በተመለከተ ግን እኔ በግሌ ወይም ድርጅቴ የተሳካ ነበር ልንል እንችላለን፡፡ ሌላው ደግሞ ከራሱ ተነስቶ የራሱን አስተያየት ሊሰጥ ይችላል፡፡ እንደ አጠቃላይ በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ እንደሚንሸራሸረው ሥጋትና አገሪቱን ከከበቧት ችግሮች አንፃር ግን ውይይቱ ከሞላ ጎደል አልተሳካም ማለት ይቻላል፡፡ ወደ 68 ፖለቲካ ፓርቲዎች ነን በጋራ ምክር ቤቱ ውስጥ ያለነው፡፡ ሁላችንም የየራሳችንን ያገባናል የምንለውን ጉዳይ ይዘን እንቀርባለን፡፡ በየቦታው በሚካሄዱ ግጭቶች ምክንያት ከክልል የመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ አገራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየአካባቢው እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ ከመሥራት አኳያ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ቢሮ መክፈት ያልቻሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ በመሆኑ አጠቃላይ የአገር አስተዳደር ሥርዓትና የሕግ የበላይነትን የተመለከቱ ጥያቄዎች ያነሳሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱም በተጨባጭ እየተተገበረ አይደለምና ሥርዓትን የተከተለ የአስተዳደር ሁኔታ በአገሪቱ ከመዘርጋት አንፃር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ቁልፍ ጥያቄ እንደሚያነሱ ይገመት ነበር፡፡ እኔም ይኼው ግምት ስለነበረኝ ነው ወሳኝ የምላቸውን ጥያቄዎች ያቀረብኩት፡፡ ከሞላ ጎደል ውይይቱ የተሳካ አይደለም፡፡ ሆኖም እኔና ድርጅቴ ግን ያሰብናቸውን ጥያቄዎች ማቅረብ ችለናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ዕድሉን ስላገኘን ሊታለፉ አይገባም የምንላቸውን ጥያቄዎች አቅርበናል፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩስ ለቀረቡ ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ ሰጥተዋል?

ደስታ፡- አንደኛ በቂ የመጠየቅ ዕድል አልተሰጠም እላለሁ፡፡ የተሰጠው ዕድል ራሱ ተሽሯል፡፡ ከዚህ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአቶ አደም ፋራህ [የብልፅግና ምክትል ፕሬዚዳንት] ጋር ትወያያላችሁ በሚል አቅጣጫ ነበር ፕሮግራሙ የተፈለገውን ያህል ሳይሄድ የተቋጨው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በሚደረግ ውይይት መድረክ ላይ ለመሪውም ሆነ ለመድረኩ በማይመጥኑ ቃላት ጥያቄዎችን አንስታችኋል የተባለውስ?

ደስታ፡- ይህ በፍጹም አልነበረም፡፡ እኔ ለምሳሌ ያቀረብኳቸውን ጥያቄዎች በሦስት መሠረታዊ ነጥቦች ከፋፍለን ማየት እንችላለን፡፡ ጥያቄዎቹ ደግሞ የመርህ ናቸው፡፡ እኔ በጀብደኝነት ማንንም ለመስደብ፣ ለመዝለፍም ሆነ ለማኮሰስ ብዬ ጥያቄ አልጠየኩም፡፡ ጥያቄዎቼን በተደራጀ ሁኔታ ነው ያቀረብኩት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በግሌ ባገኛቸውና ብጠይቃቸው የምላቸውን ጥያቄዎች፣ እንዲሁም ከድርጅቴ ጥያቄዎች ጋር አካትቼ ነው የጠየቅኩት፡፡ በጣም ሥነ ሥርዓት ባለው እንዲሁም ክብር በማያጓድል መንገድ ነው ጥያቄዎቼን ያቀረብኩት፡፡ በአዋጅ ማንም ሰው መርህ ይዞ መንቀሳቀስ አይችልም ከተባለ ይህን ልቀበል እችላለሁ፡፡ ከዚያ ውጪ ግን እኔ በግሌ የመርህ ጥያቄዎችን አቀረብኩ እንጂ፣ ማንንም የዘለፍኩበትም ሆነ ያልተገቡ ቃላት የተናገርኩበት ጊዜ የለም፡፡ አይ አለ ከተባለ ግን አለ የሚባለውን ጥፋት ማቅረብ ይቻላል፡፡ የእኔ ጥያቄዎች በሦስት ክፍሎች ተለይተው የሚታዩ ናቸው፡፡ አንደኛው የሕግ ማዕቀፍን የተመለከቱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ከዚህ መካከል ዋነኛው ጥያቄ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን ሕጋዊ ሰውነት የተመለከተ ጥያቄ ነው፡፡ የጋራ ምክር ቤቱ ህልውና ሕጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ ነው የጠየቅኩት፡፡

ሌላው በዚህ ሥር የሚቀመጡ ሕገ መንግሥቱን የተመለከቱ ጥያቄዎች አንስቻለሁ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይከበር፣ የሐሳብ ነፃነት፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብ የመሳሰሉ ነፃነቶች እየተከበሩ አይደለም የሚል ጥያቄ አቅርቤያለሁ፡፡ በሁለተኝነት ደግሞ የፖሊሲ ጥያቄዎችን አንስቻለሁ፡፡ በዚህ ውስጥ የፋይናንስ ፖሊሲን የተመለከተ ጥያቄ አንስቻለሁ፡፡ የማኅበረሰባችን ማኅበራዊ መስተጋብርን የተመለከተ ጥያቄም አንስቻለሁ፡፡ ሕግና ሕግ ነክ የሆኑ ጥያቄዎች ነበረኝ፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች መደራጀት በተለይም በፋይናንስና በሌላም ራሳቸውን ከማጠናከር መቻላቸው ጋር የተገናኙ ጥያቄዎችንም አንስቻለሁ፡፡ አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶችና ሌሎች የሚገለሉ የኅብረተሰቡ ክፍሎች በፖለቲካ ውስጥ በስፋት ስለሚወከሉበት ሁኔታ የተመለከተ ጥያቄ ጠይቄያለሁ፡፡ የምርጫ ሕጉ በተለይም በአንድ አውራ ፓርቲ የበላይነት የተሞላ ምክር ቤት የሚፈጥር በመሆኑ የተለያዩ ፓርቲዎች ውክልና ያለበት ቅይጥ የምርጫ ሥርዓት ብንከተል የሚሉ ዋና ዋና እሳቸውን የሚመለከቱ ሕግ ነክ ጉዳዮችን አንስቻለሁ፡፡ በሌላም በኩል መርህን መርህን የተመለከቱ ጥያቄዎች አቅርቤያለሁ፡፡ ለምሳሌ የሕግ የበላይነት በዚህ አገር እየተከበረ አይደለምና የሕግ የበላይነት እንዲከበር ጠይቄያለሁ፡፡

ተቋሞቻችን በተለይም የፍትሕ ተቋሞቻችን በመዳከማቸው የተነሳ ሰዎች በፍርድ ቤት ነፃ ተብለው ከእስር የማይፈቱበት ሁኔታ መፈጠሩን አንስቻለሁ፡፡ ሰዎች ከቤት ታፍነው፣ ከመንገድ ተይዘው የሚወሰዱበት ሁኔታ መፈጠሩን፣ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች በዘፈቀደ የሚታሰሩበት ሁኔታን የተመለከተ ጥያቄ አቅርቤያለሁ፡፡ ከዚህ በፊት መንግሥት ሳይጣራ ማንም ሰው አይታሰርም ማለቱን በማስታወስ አሁን ያለውን ሁኔታ ጠይቄያለሁ፡፡ ይህን የመለሱልኝ እናንተ የግብፅ ተላላኪ መሆናችሁን አላወቅኩም ነበር፡፡ እንደዚያ መሆናችሁን ሳውቅ ግን ምንም ማድረግ አልችልም ማሰር ጀመርኩ የሚል ይዘት ያለው ምላሽ ነበር የሰጡት፡፡ ሌላው የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲን የተመለከተ ጥያቄ አንስቻለሁ፡፡ በተለይ ከባህር በር ጉዳይ ጋር ተያይዞ ከጎረቤት አገሮች ጋር ችግር መፈጠሩን በማስታወስ የባህር በር ጉዳይ እኔም ድርጅቴም ሆነ ሌሎች አካላት ቢያሳስበንም፣ ነገር ግን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማግኘት አስፈላጊ ነው የሚለውን እንደሚጎላ በማስታወስ መንግሥት በዚህ ላይ ምን ዓይነት የውጪ ግንኙነት እየተከተለ እንደሆነ ጠይቄያለሁ፡፡ የተቀመጡ ሕጎችንና መርሆችን ካለማስፈጸም አንፃር ጥያቄዎችን አንስቻለሁ፡፡ በተለይም ፍልስፍናዊ ብዬ የለየኋቸውና በሚዲያዎች በተሳሳተ መንገድ ከቀረቡት መካከል የጫካ ፕሮጀክትን የተመለከተ ይገኝበታል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት አሥር ቢሊዮን ዶላር መድበዋል፡፡ ይህን በተመለከተ ሲጠየቁ ደግሞ በፓርላማው ሳይቀር ካልፈለግኩ ወደ ጦርነት አዞረዋለሁ ብለው ስለተናገሩ፣ አንደኛ ንግግሩ አግባብነት ያለው ነው ወይ? አገራችን ልማት እንጂ ጦርነት አትሻም፡፡ ስለዚህ ይህን በፓርላማው መናገሩ አግባብ ነው ወይ ብዬ ጠይቄያለሁ፡፡

ሌላው ሙስናን በሚመለከት የቀረበ ሲሆን፣ እሳቸው በተደጋጋሚ እኔ አንድም ብር አልሰርቅም እንደሚሉ በመጠቆም ስንት ሲሰረቅ ነው አንድ ብር የሚሞላው የሚል ጥያቄ ጠይቄያቸዋለሁ፡፡ ሌላው ደግሞ በአገራችን ያለውን ሁኔታ እንዴት እንደሚያዩት፣ በተለይም ጦርነቱን እንደ አክሽን ፊልም ትርዒት፣ እንደ ትርዒቱ ተሳታፊ አክተር ወይስ እንደ ሥልጣን ሚዛን ማስጠበቂያ ነው የሚያዩት በማለት ጠይቄያለሁ፡፡ ሌላኛውና በሚዲያዎች በጣም በተዛባ መንገድ የቀረበው ጥያቄዬ ደግሞ እርስዎ ንጉሥ ነዎት ወይስ ጠቅላይ ሚኒስትር ነኝ ይላሉ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ቢረዱትም እኔ ይህን የጠየቅኩበት መነሻ የአገር ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ፕሬዚዳንት በአንድ አገር ሕገ መንግሥት እስካለ ድረስ ራሱን ጨምሮ ሁሉም ሰው በዚያ ነው የሚገዛው፡፡ የሕጎች ሁሉ የበላይ ከሆነው ሕግ በላይ መሆን አይቻልም፡፡ ስለሆነም እሳቸው ለዚህ እየተገዙ ነው ወይስ በበዓለ ሲመታቸው ቀን እንደነገሩን አንድ ቀን ይነግሣሉ እንደተባሉት ሁሉ የንጉሥነት ሥነ ልቦና ነው ያለዎት የሚል ጥያቄ ጠይቄያለሁ፡፡

ይህን ደግሞ ያነሳሁት አውቶክራት (ፈላጭ ቆራጭ) እየሆኑ ነው የሚል ስሞታ መኖሩን በማስታወስ ነበር፡፡ ያም ቢሆን ግን ከጥያቄው መካከል ብዙ ነገሮች ተቀነጣጥበው ቁንጽል ሐረግ ብቻ ስለቀረበ፣ ሰዎች ዘንድ በትክክል ባለመድረሱ የተፈጠረ አለመረዳት ከሆነ ለዚያ እኔ ማብራሪያ መስጠት እችላለሁ፡፡ ለጥያቄዎቼ በቂ ምላሽ ቢሰጥም ባይሰጥባቸውም በሥፍራው የነበሩ ተወያዮችም ሆነ እሳቸው የሕግ፣ የመርህና የፍልስፍና ጥያቄዎችን ማንሳቴን ተረድተውኛል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ከዚያ ውይይት በሚዲያ መሠራጨት በኋላ ግን ጥያቄዎቼን ባልተገባ መንገድ የመመልከት ነገር ብዙ ሰዎች ዘንድ መኖሩን ታዝቤያለሁ፡፡ እኔ እዚያ የሄድኩት ሐሳብ ይዤ ነው፡፡ ነገር ግን ምን እንደተፈለገ አልገባኝም፡፡ ሐሳብ ማቅረብ ባልተገባ መንገድ የሚያስበይን ከሆነ እንደ አገር በአጠቃላይ የሳትነው ነገር አለ ብዬ እገምታለሁ፡፡ እኔ አሁንም ሆነ ወደፊትም ቢሆን ሐሳቤን ይዤ ነው ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የገባሁት፣ ባገኘሁት ዕድል ሁሉ ሐሳቦቼን ማቅረብ እቀጥላለሁ፡፡ በዚህ ሒደት ደግሞ ማንንም ክብረ ነክ ነገር መናገር በፍጹም አልፈልግም፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገራችን መሪ ናቸው፡፡ በትክክል እየመሩ ነው/አይደለም የሚለው ሌላ የምንወያይበት ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም እሳቸው የእኛ የሁላችንም መሪና ተወካይ ናቸው፡፡ በዚያ አግባብ እኔም አከብራቸዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በስብሰባው ወቅት አለመግባባቶች ነበሩ? አንቺ ያነሳሻቸውን ጥያቄዎች ተከትሎ የተፈጠረ ነገር አለ?

ደስታ፡- በፍጹም አልነበረም፡፡

ሪፖርተር፡- ለጥያቄዎቹ በተለየ ሁኔታ ምላሽ አልሰጡም?   

ደስታ፡- እንግዲህ የተወሰነ ዘለግ ባለ ሁኔታ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ምናልባት ጥያቄዎቹ ይቀርባሉ ብለው አልጠበቁ ይሆናል፡፡ ጫካንም ሆነ ሌሎችን ፕሮጀክቶች ጎብኝተን ነበር ወደ ውይይቱ የመጣነው፡፡ በዚህ የተነሳ እሳቸው በተወሰነ ሁኔታ አድናቆት ጠብቀው ሊሆን ይችላል፡፡ ፕሮጀክት መገንባቱንና ልማቱን እኛም አንቃወምም፡፡ ግን በሒደቱ የሚያሳስበን ምንለውን የሙስና ተጋላጭነትና ሌላም ሊፈጠር የሚችል ችግር ያልነውን ነገር ነው የጠየቅነው፡፡ በግል ግን ከእኔ ጋር የተፈጠረ አለመግባባት ወይም ሌላ ነገር አልነበረም፡፡ እንዲያውም መጨረሻ በግል ጠርተው አናግረውኝ አድራሻም ሰጥተውኝ ነው የተለያየነው፡፡ እኛ የፋይናንስ ኦዲት እናደርጋለን የምንሠራቸውን ፕሮጀክቶች በተመለከተ ቢሮ መጥተሽ ማየት ትችያለሽ ብለውኝ ነው የተለያየነው፡፡ ከእኔ ጋር የተፈጠረ ሌላ ነገር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህን ግብዣ በመጠቀም ፕሮጀክቶቹን ትጎበኛለሽ ወይስ ትተይዋለሽ?

ደስታ፡- ባሉኝ መሠረት ሄጄ ሁኔታውን ለመመልከት ዕቅዱ አለኝ፡፡ እነሱ በትክክል እየሠሩ ከሆነና እኔ የተሳሳተ መረጃ ይዤ ከሆነ ጥያቄዎቹን ያነሳሁት ራሴንም ለማረም ስለሚረዳኝ አጋጣሚውን ልጠቀምበት እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ ስንገባ በአገራችን ብዙ ችግሮች እንዳሉባት የታወቀ ነው፡፡ ምን ዓይነት የፖለቲካ አማራጭ ነው ለዚህች አገር የሚበጀው? እናንተስ ምን ዓይነት አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦችን ነው የምታቀርቡት?

ደስታ፡- ቅድም እንዳልኩት ኢሕአፓ ሶሻል ዴሞክራሲ ነው የሚከተለው፡፡ በዚህ ርዕዮተ ዓለም ማዕቀፍ ደግሞ የተለያዩ ጥናቶችን ሠርተን፣ የመፍትሔ ሐሳቦችን አጠናቅረንና ማኒፌስቶ አዘጋጅተን የጨረስናቸው ሰነዶች አሉ፡፡ ጥምረት ከፈጠርናቸው ድርጅቶች ጋርም ሆነ አብረውን መሥራት ከሚፈልጉ ጋር በሙሉ እነዚህን ሰነዶች ለማጋራትም ሆነ፣ በሐሳብ ተደጋግፈን ለመሥራት ሁሌም እንጥራለን፡፡ ለዚህች አገር የሚያስፈልገውና እኛም እንደ ድርጅት ይዘን የመጣነው ይህንኑ የመሀል ፖለቲካ ነው፡፡ ቁጭ ብሎ መነጋገር የሚቻልበት የሰከነና የተረጋጋ ዓውድ በመፍጠር፣ በፊት ከለመድነው ቁጡ ፖለቲካ በመውጣት ወደ ሰከነ ፖለቲካ እንድንገባ ነው ፍላጎታችን፡፡ አንዱ በሌላኛው ጫማ ውስጥ በመቆም ችግሮቻችንን በመነጋገር ሰላማዊ የፖለቲካ ሁኔታ መፍጠር እንዳለብን እናምናለን፡፡ በመነጋገር ችግሮቻችንን እንፍታ ነው የምንለው፡፡ በተለይ መሪው የፖለቲካ ድርጅት ለዚህ ተነሳሽነት መውሰድ አለበት ብለን እናምናለን፡፡ የምንታገልበት ዓላማ አለን ብለው የተነሱ ክልላዊም ሆነ አገራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ ተቀምጠው የሚነጋገሩበት ዓውድ መፍጠር ያስፈልጋል ብለን እናምናለን፡፡ እኛ ከተወሰኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ሰብሰብ ለማለት እየሞከርን ነው፡፡ በምንግባባባቸው ጉዳዮች ላይ በጋራ የምንሠራበት መንገድ እያመቻቸን ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲሰባሰቡ ከሚፈጠሩ ችግሮች አንዱ ማን ይምራ የሚለው ፉክክር ነው፡፡

እኛ በፈጠርነው ጥምረት ውስጥ ግን አሁን አሥር ወራት እየሞላው ይገኛል በየስድስት ወራት አመራር እንዲቀያየር በጋራ ወስነናል፡፡ እኛን ጨምሮ እናት ፓርቲ፣ መኢአድ፣ እንዲሁም አማራ ግዮናዊ ፓርቲ የተሰባሰብንበት ጥምረት በምርጫ ቦርድ ዕውቅና ያለውና በየስድስት ወራት አመራሩ ከየፓርቲው የሚቀያየር ነው፡፡ መጀመሪያ ከእኛ ዝናቡ ነበሩ የመሩት፡፡ ከስድስት ወራት በኋላ የእናት ፓርቲው ሰይፈ ሥላሴ (ዶ/ር) የተተኩ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ እየመሩት ነው፡፡ ይህን የእኛን መጠነኛ ተሞክሮ ለመጋራት የሚፈልግ ካለ ወደ ጥምረቱ እንዲቀላቀል እየጋበዝን ነው፡፡ ሌላም የተሻለ አሰባሳቢ መንገድ ካለ ለመቀላቀልና ሰብሰብ ብሎ ለመሥራት ሁሌም ዝግጁ ነን፡፡ በእኛ በኩል ወደ መሀል ፖለቲካ መምጣት አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ሶሻል ዴሞክራሲ አሁን አገራችን ላለችበት የመበታተንና የመለያየት ፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ምዝበራ፣ የመንቀሳቀስና የደኅንነት ዋስትና ማጣት ችግር በተሻለ ሁኔታ መፍትሔ ያለው ርዕዮተ ዓለም ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡

ሪፖርተር፡- ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ በቅርቡ ያቀረበው ኢትዮጵያ በልጆቿ ትታረቅ የሚል በጎ ዓላማ ያነገበ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ እናንተስ?

ደስታ፡- እኛም ይህን መሰሉን የተቀደሰ ሐሳብ እንደግፋለን፡፡ እናም በሚፈለገው አብረን ለመሥራት ዝግጁነታችንን አሳይተናቸዋል፡፡ በየወሩ የመጽሐፍ ዳሰሳ አላቸው፣ እሱ ላይ ከመሳተፍ ጀምሮ ይኼኛውን ጥሪያቸውንም ተቀብለናል፡፡

ሪፖርተር፡- አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑና ሒደቱ ያለው ተስፋ ብዙ ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በኢትዮጵያ ተመናምኖ በሩ እየተዘጋ ነው የሚል ተስፋ ማጣት በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ይታያል፡፡ ይህን ሰላማዊ መንገድ አሁንም ቢሆን መጠቀም አስፈላጊ ነው ብላችሁ ታስባላችሁ?

ደስታ፡- እኔ እንግዲህ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የማደርግ ሰው ነኝ፡፡ ሁልጊዜ የማቀርበውም ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሐሳብን ነው፡፡ በጦር ምንም ዓይነት ችግር አንፈታም ብዬ አምናለሁ፣ መቼም፡፡ ለጊዜው አንዱ ሌላውን ሊያጠቃ ይችላል፣ ጦሱ ግን ለትውልድ ሊተርፍ ይችላል፡፡ ሁልጊዜ መነጋገር የተሻለ ነው፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል መቀጠል ደግሞ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው፡፡ እኔም ሆነ ድርጅቴ፣ እንዲሁም አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ጭምር ይህንኑ አማራጭ ብቻ ነው የምናስቀድመው ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡ ነገር ግን እነዚህ የድርድር፣ የንግግርና የውይይት ሒደቶች ሁሉ የራሳቸው አዝጋሚ ኡደት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እኛ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑን በሚመለከት የተዓማኒነት ጥያቄ ነው ያለን፡፡ ከመጀመሪያው ኮሚሽኑ ሲመሠረት ጀምሮ ከአዋጁ ጀምሮ፣ ከኮሚሽነሮች መረጣ ጀምሮ ባሉ ሒደቶች እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት አሉን የምንላቸውን ሐሳቦች ስንሰጥ ቆይተናል፡፡ ያም አልፎ ኮሚሽኑ ሲቋቋም ደግሞ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ውስጥ የተከፋፈሉ ሐሳቦች ሲራመዱ ቆይተዋል፡፡ አንዳንዶች ሒደቱ ውስጥ የለንበትም ብለው ሲወጡ ብዙዎች ደግሞ አሉን የምንላቸውን ቅሬታዎች እያነሳን ድክመቱን እያረሙ መቀጠል ይሻላል ብለን ስንሳተፍ ቆይተናል፡፡ ኮሚሽኑን ስለማናምነው አንቀጥልም ያሉ ድርጅቶች የራሳቸውን ኮከስ መሥርተው ከኮሚሽኑ ጋር ሲነጋገሩ ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ 16 ድርጅቶች ውስጥ ደግሞ ሦስቱ በሒደቱ እንሳተፋለን  ብለው ተመልሰዋል፡፡ 13 ያህሉ አሁንም ራሳቸውን እንዳገለሉ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እኛ አሁን  እየደረሰብን ካለው ችግር አንፃር ቅድመ ሁኔታ ወደ ማስቀመጥ ገብተናል፡፡ ምክንያቱም ስንታሰር የማያስፈታን፣ እንዲሁም ችግር ሲፈጠርብን የማይደርስልን ከሆነ እኛም ቢሆን ከብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሒደት ራሳችንን ለማግለል ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠናል፡፡ ሰሞኑን በዚህ ላይ ስብሰባ ነበረን፡፡ ስለዚህ መሪያችን ካልተፈቱ ከሒደቱ ለመውጣት ነው ያሰብነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢዜማ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረው ውይይት በብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሒደት ላይ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ የውይይት ሒደቶችን በብልፅግና ፓርቲ አደረጃጀቶች የመዋጥ አዝማሚያ እየታየ ነው የሚል ቅሬታ ነው ያቀረበው፡፡ ይህን መሰሉን አቋም ትጋሩታላችሁ? ወይስ ችግሩ የለም ትላላችሁ?

ደስታ፡- እኔ የምክክር ኮሚሽኑ ውይይት ከጀመረበት ጊዜ የአቶ አበበ አካሉን [ከኢዜማ] ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ በእኛ በኩል ይህን ስንገመግመው ነበር ችግሩ መኖሩን ቀድመንም ተረድተናል፡፡ በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሒደት በየክልሉ ከሚሳተፉ ከሰባቱ አመቻቾች ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አንዱ በመሆኑ፣ በየቀጣናው አንድ ተወካይ እንልካለን፡፡ በዚህም እንደገመገምነው በውይይቶቹ ተዋናይ ከሚሆኑት መካከል የወረዳ አስተዳዳሪ፣ ዳኛና ሌላም የመንግሥት አደረጃጀት ውስጥ ያሉ አካላት ሆነው አግኝተናል፡፡ ስለዚህ በዚህ መሰሉ በመንግሥት መዋቅር ሰዎች በተሞሉ የውይይት ሒደቶች የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ወሳኝ ባለድርሻ አካላት የመሳተፋቸው ዕድል የጠበበ መሆኑን ተረድተናል፡፡ ይህ ችግር እንዲስተካከል እኛም ጠይቀናል፡፡

ሪፖርተር፡- የብሔራዊ ምክክር ውይይት ሒደቶችን የሚመሩ አመቻቾችና አወያዮች ሲመረጡና ከዚያም ቀደም ብሎ በተገቢው ሁኔታ ሆደቱን በተመለከተ አለ የምትሉትን ሐሳብ ሰጥታችኋል?

ደስታ፡- ይህንኑ ችግር አቅርበናል፡፡ እኛ እንደ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የመምህራን ማኅበርን፣ ዕድሮችን፣ ሲቪክ ማኅበራትን ጨምሮ አምስት አካላትን አሰባስበን አንድ የጋራ መድረክ አለን፡፡ በዚህ የጋራ መድረክም ቢሆን የገመገምነው ተመሳሳይ ችግር ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዕድሮች በአዲስ አበባ እንዲበተኑ እየተደረገ ነው፡፡ የምስክር ወረቀት የላችሁም እየተባለ ብዙ ዕድሮች እንዲፈርሱ እየተደረገ ነው፡፡ እኛ በዕድሮችና በመምህራን ማኅበራት በመሳሰሉ አደረጃጀቶች በኩል በውይይቱ ጠንካራ ተሳትፎ ለማድረግ ዕቅድ ይዘን እንደነበር መንግሥትም የምክክር ኮሚሽኑም ያውቃል፡፡ ይሁን እንጂ የውይይት ተካፋዮች መረጣ ሊጀመር ሲል ዕድሮችን የማፍረስና የመንግሥት አደረጃጀቶች እንዲቆጣጠሩ የማድረግ የመሳሰሉ ችግሮች ገጥመውናል፡፡ ስለዚህ ይህ ችግር የሁላችንም ወሳኝ እንቅፋት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመጨረሻም ጠንካራ ጥያቄዎችን ያቀረብሽበት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ከተደረገው የውይይት መድረክ በኋላ ምን ገጠመሽ?

ደስታ፡- ምንም የገጠመኝ ነገር የለም፡፡ መደበኛ ሕይወቴን ቀጥያለሁ፡፡ መማሬን፣ መሥራቴን፣ ቤተሰቤን መምራቴን ቀጥያለሁ፡፡ ግን ከውይይቱ በኋላ አንዳንድ ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለጥፉትን መረጃ ሳይ ያነሳሁትን ጥያቄ በተመለከተ አለመረዳት እንዳለ ተረድቻለሁ፡፡ እንዲህ ዓይነት ዕድል ባገኘሁ ቁጥር ልል የፈለግኩትን ሐሳብ በቅጡ ማብራራቴን እቀጥላለሁ፡፡