
ከ 6 ሰአት በፊት
በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እያለፉ የሚገኙ ዜጎች መደፈር፣ የጎሳ ጥቃት እና በየጎዳናው ላይ ግድያ እየገጠማቸው መሆኑን ለቢቢሲ ምስክርነታቸውን ገልጸዋል።
ግጭቱ አገሪቱን “በቅርብ ጊዜ ታሪኳ ውስጥ ከታዩት አስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ አዘቅት አንዱ ውስጥ ከቷታል” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። በዓለም ላይ ትልቁን የረሃብ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችልም ተናግረዋል።
በአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል በምትገኘው ዳርፉር ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ከ20 ዓመታት በፊት የዘር ማጥፋት ወንጀል ያለችው ክስተት ድጋሚ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ ስለ አካላዊ እና ወሲባዊ ጥቃት የሚጠቅሱ ገለጻዎችን ይዟል
ከየት የመጣ እንደሆነ የማይታወቅ ፍንዳታ የኦምዱርማን ጎዳናን ይንጠዋል። ሰዎች በየአቅጣጫው መሮጥ ጀመሩ። “ተመለሱ፣ ተመለሱ ሌላም ፍንዳታ ይኖራል” የሚል ድምጽ ተሰማ። ጥቅጥቅ ያለ ጭስ አካባቢውን ሸፈነው።
ከፍንዳታው በፊት እንደገና ሥራ በጀመረው የገበያ ስፍራ ነዋሪዎች ሩዝ፣ ዳቦ እና አትክልት እየገዙ ነበር።
በናይል ወንዝ ዳርቻ ላይ ከተንጣለሉት እና ካርቱምን ከመሠረቱት ሦስት አካባቢዎች አንዷ ኦምዱርማን ናት። በየካቲት ወር አጋማሽ ላይም በሱዳን ጦር እጅ በድጋሚ ወድቃለች።
ነዋሪዎችም መመለስ ጀምረዋል። በከተማዋ ጎዳና የወደቀው የዓይነት ሞርታር ጥቃት ግን አሁንም ያጋጥማል።
ዓመት የደፈነውን የእርስ በርስ ጦርነት ለመዘገብ ለዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን አስቸጋሪ ነው። ቢቢሲ ግን ወደ ጦር ግንባር ለመድረስ ፈቃድ አግኝቷል።
በአንድ ወቅት ደማቅ ነበረችው ኦምዱርማን ጥቂት ሰዎች ብቻ ቤቴ ወደሚሏት ምድረ በዳ ተለውጣለች።
- የተረሳው ግጭት እና ከአስከፊ የረሃብ ቀውስ አፋፍ ላይ የምትገኘው ሱዳን14 ሚያዚያ 2024
- አንድ ዓመት በሞላው ጦርነት ለውስብስብ ችግር የተጋለጡት ሱዳናውያን ክርስቲያኖች18 ሚያዚያ 2024
- ‘ከእናቴ አስከሬን ጋር በረሃ ላይ ቀረሁ’ – ወደ ግብፅ የሚሰደዱ ሱዳናውያን ሰቆቃ28 የካቲት 2024

በአገሪቱ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) መካከል የተፈጠረው የሥልጣን ሽኩቻ ወደ በተሸጋገረው ጦርነት በትንሹ 14 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል።
ሁለቱ ኃይሎች ለዓመት ገደማ በካርቱም እና በአካበቢዋ ውጊያ ገጥመው ቆይተዋል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ደቡባዊ ካርቱምን እና ለዓመታት በግጭት ሲታመስ የቆየውን አብዛኛውን ዳርፉር ተቆጣጥሯል።
ከዳርፉር ወደ ቻድ የሸሹ ሴቶች በሚሊሻዎች ጥቃት ፆታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው እና አንዳንዴም በተደጋጋሚ መደፈራቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። በካምፑ ተጠለሉ ወንዶች ደግሞ ጎዳና ላይ ከመገደል እና ከመታፈን እንዳመለጡ ነግረውናል።
የቢቢሲ ባልደረቦች ከአገሪቱ ጦር ጋር ከመንቀሳቀስ ባለፈ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲቀርጹ አልተፈቀደላቸውም።
ሠራዊቱ እንቅስቃሴውን በተመለከ መረጃ ይፋ ይሆናል የሚል ስጋት አለው።
የኦምድሩማኑን የሞርታር ፍንዳታ ተከትሎ የካሜራ ባለሙያው መቅረጽ ሲጀምር ሲቪል የለበሱ ታጣቂዎች ከበቡት። አንዱ ደግሞ ሽጉጡን ጭንቅላቱ ደገነበት።
ወታደራዊ ደኅንነቶች ነበሩ። ይህም በአካባቢው ምን ያህል ከፍተኛ ውጥረት እንዳለ ምልክት ነው።
የሱዳን ጦር ሠራዊት በቅርቡ ኦምዱርማንን በእጁ ቢያስገባም አልፎ አልፎ አሁንም የተኩስ ልውውጥ ይደረጋል።

አሁን የጦርነት ቀጠና ሆነው የናይል ወንዝን ይዞ ያለው አካባቢ ነው። ከካርቱምን በምሥራቅ አቅጣጫ ከኦምድሩማን የሚለየው ምዕራባዊው የወንዙ ክፍል ነው።
ሁለቱ ኃይሎች ከወንዙ በተለያየ አቅጣጫ ሆነው ተፋጠው ይገኛሉ።
የኦምዱርማን አሮጌ ገበያ ፈርሷል። ሱቆቹ ተዘርፈዋል። መንገድ ላይ ወዲያ ወዲህ ሚሉት በአብዛኞቹ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ናቸው።
ባለፉት 11 ወራት ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ካርቱም ለቀው ተሰደዋል። አንዳንድ የኦምዱርማን ነዋሪዎች ግን ከተማዋን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆኑም። አብዛኞቹ ደግሞ አረጋውያን ናቸው።

ሙክታር አል-ቃድሪ ሞኸዲን ጦርነት ከሚካሄድበት ግማሽ ኪሎሜትር ብቻ ርቆ ወደሚገኘው እና በከፊል ወደ ወደመው መስጊድ ይመላለሳሉ።
በቅርብ ርቀት የሚገኘው ባዶ ቦታ አሁን የመቃብር ስፍራ ሆኗል።
“እዚህ 150 ሰዎች ተቀብረዋል። አብዛኞቹን አውቃቸዋለሁ። ሞሐመድ፣ አብዱላህ. . . ጃላል” ካሉ በኋላ አንድ ታዋቂ ስምም ጠሩ ዶ/ር ዩሴፍ አል-ሃብር። ታዋቂ የአረብኛ ቋንቋ ፕሮፌሰር ናቸው።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና ሲቪሎች ባሉበት አካባቢ የአገሪቱ ጦር ከፍተኛ አየር ጥቃት ፈጽሟል በሚል ቢተችም “አስፈላጊውን ጥንቃቄ” ማድረጉን ይገልጻል።
ነዋሪዎች በመዲናዋ ለደረሰው ጉዳት ሁለቱንም ወገኖች ተጠያቂ ያደርጋሉ።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች አካበቢውን በተቆጣጠረበት ጊዜ ዝርፊያ እና ጥቃት ፈጽመዋል በሚል በብዙዎች ይከሰሳሉ።
“ቤቶችን ዘርፈዋል። መኪና እና ቴሌቭዥን ሰርቀዋል። ሰዎችን ደብድበዋል” ሲሉ ሙሐመድ አብድል ሙታሊብ ገልጸዋል።
“አንዳንዶች በረሃብ ምክንያት ቤታቸው ውስጥ ሲሞቱ ሬሳቸው እንዳይሸት አውጥቻለሁ” ብለዋል።
ሴቶች በቤታቸው ውስጥ መደፈራቸውም “በደንብ ይታወቃል” ሲሉ አክለዋል።

ዕድሜያቸው በ50ዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገኙት አልፋ ኡሐመድ ሳሌም ነዋሪነቷ ካርቱም ነበር።
የፈጥኖ ደራሽ ተዋጊዎች ቤታቸውን ዘርፈው ወንድማቸው እግሩን በጥይት በመምታቱ ወንዙን ተሻግረው ኦምዱርማን መኖር ጀመሩ።
“ሰዎችን እየደበደቡ ሴቶችን ያስፈራሩ ነበር” ብለዋል።
በሱዳን በግልጽ ስለማይወራው የፆታ ጥቃት እየገለጹ ነው።
“ክብርን መንካት ገንዘብ ከመዘረፍ በላይ ጉዳት ያስከትላል” ብለዋል።

‘የበቀል መሣሪያ’
አስገድዶ መደፈር ደረሰባቸው ከቤተሰቦቻቸው ጀምሮ መገለል ይገጥማቸዋል። በዚህ ምክንያት በርካታ የኦምዱርማን ነዋሪዎች ስለጉዳዩ አስተያየት አይሰጡም።
አንድ ሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኘው የቻድ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ግን ስለጉዳዩ የሚናሩ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል።
ማንነቷ አንዳይታወቅ ስሟ የተቀየረው አሚና በድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን ክሊኒክ የተገኘችው ጽንስ ለማቋረጥ ነው።
ከዳርፉር ተሰደደችው የ19 ዓመቷ ወጣት እርጉዝ መሆኗን ያወቀችው ከአንድ ቀን በፊት ነበር። ቤተሰቦቿ ስለጉዳዩ እንዲያውቁ በፍጹም አትፈልግም።
“አላገባሁም። ድንግልም ነበርኩ” ስትል በተዳከመ ድምጽ ገልጻለች።
ከአክስቷ እና ከአክስቷ ልጆች ጋር ወደ ሌላ ከተማ ሲሰደዱ ነው ሚሊሻዎች ያገኟቸው።
“ሌሎች ሲያመልጡ እኔን አቆዩኝ። ሁለት ነበሩ። አንዱ ደጋግሞ ደፈረኝ” ብላለች።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በአረብ ሚሊሻዎች ተደግፎ በዳርፉር የበላይነቱን አጠናክሯል። በጥቁር አፍሪካውያን በተለይም በማሳሊት ጎሳ አባላት ላይ ዘር ተኮር ጥቃት ደርሷል።
ኃይሉ ኅዳር ወር ላይ አርዳማታ የሚገኘውን የአገሪቱን ጦር ሰፈር ሲቆጣጠር፣ ከአሚና ጋር ተመሳሳይ ታሪኮች መፈጸማቸው ተነግሯል።
ካለፈው ዓመት ወዲህ በአካባቢው ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ያሳያል።
ድርጅቱ ከ120 በላይ ፆታዊ ጥቃቶች መፈጸማቸውን መዝግቧል።
ከ80 በመቶ በላይ ለሚሆነው ጥቃት ተጠያቂዎቹ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አባላት እና ደፊዎች ናቸው ብሏል። አገሪቱ ጦርም ግን በፆታዊ ጥቃት ላይ ተሳታፊ ሆኗል።
ከስደተኞች መጠለያው ውጪ በሚገኝ ስፍራ ከ30 በላይ ሰዎች ተገኝተዋል። ሴቶቹ ስለደረሰባቸው ጾታዊ እና አካላዊ ጥቃት ሲገልጹ እያነቡ ነበር።

ማርያሙ (ስሟ ተቀይሯል) የአረብ ታጣቂዎች የሚለብሱትን ዓይነት ደንብ ልብስ በሚለብሱ ሰዎች ተደፍራለች። በኋላ ላይም መራመድ እንኳን አልቻለችም ነበር።
ሌሎች እየሮጡ ሲሸሹ “አያቴ ስላረጀች እኔ ደግሞ ደም ስለሚፈሰኝ መሮጥ አልቻልንም” ብላለች።
ራሷ በጎ አድራጊ የሆነችው ስደተኛዋ ዛሃራ ኻሚስ ከጥቁር አፍሪካውያን የሆኑት የማሳሊት ጎሳ አባላት አሚና እና ማርያሙ ዒላማ ተደርገዋል ብላለች።
ከ20 ዓመት በፊት በወቅቱ ፕሬዝዳንት ኦማርሐሰን አል-በሽር የሚደገፉት የጃንጃዊድ የአረብ ሚሊሻ አባላት ዳርፉር ውስጥ አማጺያኑን አረብ ያልሆኑ ጎሳዎችን አጥቅተዋል። ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉም መነሻው ከዚሁ ከጃንጃዊድ ሚሊሻ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 300 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል ብሏል። ጥቁር አፍሪካውያን ላይ አስገድዶ መድፈርም እንደ መሣሪያ ጥቅም ላይ ውሏል። ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አል-በሽር እና አንዳንድ የጃንጃዊድ መሪዎችን ተጠያቂ ቢያደርግም ሁሉም ክሱን አስተባብለዋል።
ኻሚስ እንደምትለው በዚህ ጦርነት አስገድዶ መስፈር “እንደበቀል መሣሪያ” ጥቅም ላይ ውሏል።
“ሴቶችን የሚደፍሩት ጥቃቱ ሕብረተሰቡ ላይ በሚያሳድረው ጠባሳ ምክንያት ነው” ብላለች።
አንድ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ “አዛዥ” ከወራት በፊት አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አጋርቶ ነበር።
“ልጆቻችሁን ከደፈርን ብድር በምድር እያልን ነው። ይህ አገራችን ነው። አጋጣሚውን ስናገረ እንጠቀምበታለን” ብሏል አሁን በተሰረዘው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ።
የአገሪቱ ጦር “ሰዎችን በመቅጠር የእኛን ዩኒፎርም አስለብሶ ሕብረተሰቡ ላይ ወንጀል በመፈጸም ስማችንን እያጠፋ ነው” ሲል ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በጉዳዩ ላይ ምላሹን ለቢቢሲ ሰጥቷል።
“አንድ ወይም ሁለት አጋጣሚዎች ቢኖሩ ነው እነሱንም ተጠያቂ እናደርጋለን” ሲሉ የቡድኑ መሪ ቢሮ አባል የሆኑት ኦማር አብዱላህ ሐሰን ተናግረዋል።
አርኤስኤፍ በአባላቱ ተፈጸሙ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንደሚያጣራ ቢያሳውቅም እስካሁን ምንም መረጃ እንዳልተሰጠ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

‘ማሳሊት ከሆንክ ይገድሉሃል’
በሌላኛው መጠለያ ጣቢያ ቢቢሲ ያጣራው እና አርዳማታ ውስጥ ታጣቂዎች ወጣቶችን ደርድረው የሚታይበትን ቪዲዮ የሚመለከተው አህማት እጁ እየተንቀጠቀጠ ነበር።
“ሁሉንም እጨርሳቸዋለሁ” የሚል ድምጽ ከተሰማ በኋላ የተኩስ እሩምታ ተከፈተባቸው።
“ይህ አሚር ነው፣ ይኼኛው ደግሞ አባስ. . .” እያለ አህማት በማልቀስ ለያቸው።
ምስሉን ስትመለከት የመጀመሪያዋ ነው። ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አካበቢውን በተቆጣጠረ በሁለተኛው ቀን ከታጣቂዎቹ በአንዱ የተቀረጸ ነው።
ዘመዱ አሚር እና ጓደኛው አባስ ወዲያ ሲሞቱ እሱ እና ሌሎች ሁለት ተርፈዋል።
ጥይቱ የመታው ጀርባው ትልቅ ጠባሳ አለው። እሱ መምህር የነበረ ሲሆን፣ አምስታቸውም ሲቪሎች እንደነበሩ አስታውቋል።
“እንደሞተ ሰው ሆነን ተኛን። የመጨረሻዬ ነው ብዬ ስጸልይ ነበር” ብሏል።
አህማት ከቤቱ አቅራቢያ ነበር በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎቹ እና በደጋፊዎቻቸው የተያዘው። በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የሚታዩት ታጠቂዎችም የቡድኑን ዩኒፎርም ለብሰዋል።
በተመሳሳይ ወቅት በአርዳማታ ሁለት ሰዎች በቡድኑ ታጣቂዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የ55 ዓመቱ ዩሱፍ አብደላህ ከተያዘ በኋላ ማምለጡን አስታውቋል። እናት እና ልጅ ሲገደሉ ማየቱንም ተናግሯል።
“ከማሳሊት ጎስ መሆህን ጠይቀው፤ ከሆንክ ይገድሉሃል” ብሏል።
ሱዳን ወደ አለመረጋጋት የገባቸው እአአ በ2019 ለሦስት አስርት ዓመታት ገደማ የዘለቀውን የአል-በሽርን አገዛዝ በመቃወም ነው።
ሲቪል እና ሠራዊቱን ያጣመረ መንግሥት ቢመሠረትም ጦሩ እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ተቆናጠጡ።
ሁለቱም ግን ሥልጣን እንዴት ወደ ሲቪሎች እጅ ይገባል እና የፈጥኖ ደራሽ አባላት እንዴት ከሌላው ጦር ጋር ይዋሃዳሉ በሚለው ጉዳይ መግባባት አልቻሉም።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አባላቱን በመላው አገሪቱ ማሠማራቱን የአገሪቱ ጦር እንደስጋት ቆጠረው። ሁለቱም ሥልጣናቸውን መልቀቅ አለመፈለጋቸው ተጨምሮበት ወደ ለየለት ግጭት አመሩ።

‘ረሃብ አፋፍ ላይ’
አንዳንድ የእርዳታ ድርጅቶች ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ እየወጣ ነው ብለዋል። ዩኒሴፍ ደግሞ አንዳንድ ማኅበረሰቦች በረሃብ አፋፍ ላይ ይገኛሉ ብሏል።
የሦስት ዓመቷ ማናሴክ በተመጣጠነ ምግብ እጦት ከሚሰቃዩት በመቶ ሺህዎች ከሚቆጠሩ ሕጻናት መካከል ናት። መንቀሳቀስም ሆን ጭንቅላቷን ቀና ማድረግ አትችልም።
እናቷ ኢክራም አቅፋ ፖርት ሱዳን ወደሚገኘው የዩኒሴፍ ሆስፒታል ወስዳታለች። ከተማዋ አብዛኛው የመንግሥት ተቋማት እና ነዋሪዎች የሸሹባት ናት።
ማናሴክ ሌላ በሽታ እንዳለባት ለማወቅ ለሚያስፈልገው ምርመራ የመክፈል አቅም የላትም።
“ሕይወታችንን እና ሥራችንን አጥተናል” ስትል እያለቀሰች ተናግራለች። ባለቤቷ የግብርና ሥራ ፍለጋ ሌላ ቦታ ሲሆን፣ የኑሮ ውድነቱ ደግሞ አልቀመስ ብሏታል።
በፖርት ሱዳን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች አሁን መጠለያ ጣቢያ ሆነዋል። ሕጻናት ከሚጫወቱበት ሜዳ ጎን ፈሳሽ ቆሻሻ ይወርዳል። አምስት ሰዎች በኮሌራ ምክንያት መሞታቸው ተነግሯል።
ዙቤይዳ አማር ሙሐመድ የደም ካንሰር (ሉኬሚያ) መድኃኒቷ ከጨረሰችበት ያለፉት ወራት ጀምሮ በከፍተኛ ህመም ውስጥ ናት።
ባለቤቷ በፈቃደኝነት ለሱዳን ጦር ልዝመት ብሎ ከወጣ ወዲህ ስለእሱ መረጃ የላትም። እያደር ጤና ማጣቷን ከማየት ውጭ ቤተሰቦቿ ምንም ሊረዷት አልቻሉም።
ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጥቃት እና ከጦሩ አየር ድብደባ የሚሸሹ ኮፕቲክ ክርስቲያኖችንም ቢቢሲ አግኝቶ ነበር።
ሳራ ኤሊያስ “ካርቱም ውስጥ የአየር ኃይሉ አውድሞናል” ብላለች።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በመኖሪያ አካባቢዎች በመደበቃቸው የአገሪቱ ጦር ባደረሰው የአየር ጥቃት ባለቤቷ እና ከጎረቤት ደግሞ ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል።
ሁለቱም ወገኖች የጦር ወንጀል ፈጽመዋል ያለችው አሜሪካ፤ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና ደጋፊዎቹ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እና የዘር ማጽዳት ፈጽመዋል ብላለች።
ሁለቱም ወገኖች ክሱን አስተባብለዋል።
ከአንድ ዓመት በኋላም ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን ለማስቆም ምንም ፍንጭ አላሳዩም።
የሚችሉት አገሪቱን ጥለው ተሰደዋል።
ግጭት፣ ረሃብ እና በሽታ በተስፋፋበት በአሁኑ ወቅት የትኛው ወገን አሸነፍኩ ሊል እንደሚችል ብዙዎች በግርምት እየተጠባበቁ ነው።
