ታዋቂው ደራሲ ሰር ሳልማን ሩሽዲ

ከ 6 ሰአት በፊት

ታዋቂው ደራሲ ሰር ሳልማን ሩሽዲ ከሁለት ዓመት በፊት የገጠማቸውን ለቢቢሲ የገለጹት ቀዝቀዝ ባለ መንፈስ ነው። በዕለቱ መድረክ ላይ በስለት ተወግተዋል።

ደራሲው የቡከር ተሸላሚው ለመሆን የበቁ ስመ ጥር ናቸው። በዕለቱ በተፈጸመባቸው ጥቃት ዐይናቸው ላይ ከፉኛ ጉዳት እንደደረሰበቻው ያስታውሳሉ። ያ ሁኔታ እስከ ዛሬም ድረስ ያንገበግባቸዋል።

“የምሞት መስሎኝ እንደነበር ትዝ ይለኛል። እንደ ዕድል ሆኖ ተረፍኩ” ይላሉ።

ሰር ሳልማን ሩሽዲ አዲስ መጽሐፍ ለተደራሲያን ለማብቃት ደፋ ቀና እያሉ ነው። ‘ናይፍ’ (ቢላዋ) የሚል ርዕስ የሰጡትን መጽሐፋቸው የደረሰባቸውን ጥቃት እንደመታገያ ሊጠቀሙበት አቅደዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው እአአ ነሐሴ 2022 ኒው ዮርክ ውስጥ በሚገኝ አንድ የትምህርት ተቋም ለተማሪዎች ንግግር ለማድረግ በሚዘጋጁበት ወቅት ነበር።

ጥቃቱ ለ27 ሰከንዶች ብቻ የቆየ ነበር። ጥቃት አድራሹ “በፍጥነት” ወደ መድረኩ ሲንደረደር ያስተውሳሉ። በ27 ሰከንዶች ውስጥ አንገታቸውን እና ሆዳቸውን ጨምሮ 12 ጊዜ ተወግተዋል።

“ራሴን በፍጹም መከላከል አልቻልኩም። ሩጬም ላመልጠው አልተቻለኝም” ብለዋል ሁኔታውን ሲያስታውሱ።

ወለሉ ላይ ተዘርረው “ደማቸው እንደጅረት ፈሶ” አካባቢው ደም መልበሱን መቼም አይረሱትም።

በሄሊኮፕተር ወደ ሆስፒታል ተወስደው ለማገገምም ስድስት ሳምንታትን በዚያው ለመቆየት ተገደው ነበር።

ሕንድ የተወለዱት እና የእንግሊዝ እና የአሜሪካ ጥምር ዜግነት ያላቸው ሩሽዲ 76 ዓመታቸው ነው። በዘመናዊው ዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑት ደራሲያን መካከልም አንዱ መሆናቸው ይነገርላቸዋል።

እአአ በ1988 ለተደራሲያን ያበቁት ‘ዘ ሳታኒክ ቨርስስ’ [ሰይጣናዊ ጥቅሶች] ብዙ መዘዝ አስከትሎባቸዋል። በዚህ መጽሐፋቸው ሳቢያ በደረሰባቸው ተደጋጋሚ የግድያ ዛቻዎች ለዓመታት ተደብቀው ለመኖር ተገደዋል።

ሁሌም ግን የሚሰጉት ነገር ነበራቸው፤ አንድ ቀን “ከተሰብሳቢዎች መካከል አንዱ ዘሎ” ያጠቃኛል የሚል።

“ይህንን አለማሰብ ሞኝነት ነበር” ብለዋል።

“በየቀኑ ያንገበግበኛል”

ጥቃቱ በሩሽዲ ጉበት እና እጅ ላይ ጉዳት አድርሷል። የቀኝ ዐይናቸው ነርቭም ክፉኛ ጎድቷል።

“ዐይኔ በጣም የተወጠረ እና ያበጠ” ይመስላል። “ፊቴ ላይ ተንጠልጥሎ ጉንጬ ላይ የተቀመጠ ለስላሳ የተቀቀለ እንቁላል ይመስል ነበር። ማየትም ተሳነኝ” ብለዋል።

ሰር ሰልማን ሩሽዲ አንድ ዐይናቸውን ማጣቸውም “በየዕለቱ” ያንገበግባቸዋል። ደረጃ መውረድ፣ መንገድ ማቋረጥ ወይም ውሃ መቅዳት ቀላል ባለመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በአንጎላቸው ላይ ጉዳት አለመድረሱ ራሳቸውን እንደ ዕድለኛ እንዲቆጥሩ አድርጓቸዋል። “ይህ ማለት እኔ አሁንም ራሴን መሆን ችያለሁ ማለት ነው” ብለዋል።

ደራሲው በስለት የተወጉበት መድረክ ላይ ሥነ ሥርዓቱን ይመራ የነበረው ግለሰብ ጥቃቱን ለመከላከል ብችል ኖሮ ብሎ እንደሚጸጸት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ፈጣን እርምጃ ብወስድ ኖሮ ብዙ ነገር መከላከል ይቻል እንደነበር ይሰማኛል” ሲሉ የመድረኩ መሪ ኔነሪ ሪስ ተናግረዋል።

ሰር ሰልማን ሩሽዲ ሪስን ከማመስገን ግን አልቦዘኑም። የተንከባከቧቸው ሐኪሞችም ምሥጋናው ደርሷቸዋል። በአዲሱ መጽሐፋቸው መግቢያ ላይም ይህንኑ ገልጸዋል።

መጽሐፉ “ሕይወቴን ላዳኑት በሙሉ” ይሁንልኝ ሲሉ በአጭሩ አስፍረዋል።

በተለያዩ መድረኮች ላይ ንግግር የሚያደርጉት ሳልማን ሩሽዲ ከጥቃቱ በፊት
የምስሉ መግለጫ,በተለያዩ መድረኮች ላይ ንግግር የሚያደርጉት ሳልማን ሩሽዲ ከጥቃቱ በፊት

ለመግደል በቂ ምክንያት ነው?

ሰር ሳልማን ሩሽዲ ለመጀመሪያ ጊዜ ጉዳት ላደረሰባቸው ሰው የሚሰማቸውን ገልጿል።

የኒው ጀርሲው ነዋሪ የ26 ዓመቱ ሃዲ ማታር በስለት ጉዳሰት በማድረስ ተከሷል። ማታር ጥፋተኛ አይደለሁም ብሎ ክሱን አስተባብሏል። ዋስትና በመከልከሉም በእስር ላይ ይገኛል።

ማታር ከእስር ቤት ሆኖ ከኒውዮርክ ፖስት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ የሰር ሰልማንን ቪዲዮዎችን ዩቲዩብ ላይ መመልከቱን ተናግሯል። “እንዲህ አይነት መጥፎ የሆኑ ሰዎችን አልወድም” ብሏል።

ሰር ሰልማን ራሽዲ አጋጣሚውን ተንተርሶ የተጻፈው አዲስ መጽሐፍ ከመታተሙ በፊት ከአላን የንቶብ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ህይወታቸውን ሊነጥቅ ስለነበረው የቢላዋ ጥቃት ተናግረዋል።

‘ናይፍ’ በተሰኘው መጽሐፍ ሰር ኣልማን ከጉዳት አድራሹ ጋር ምናባዊ ውይይት ያደርጋሉ። ለዚህም ምላሽ ይሰጣሉ።

“በአሜሪካ ውስጥ ብዙ ሰዎች ሐቀኛ መስለው ቢታዩም ግን ጭንብል ለብሰው ይዋሻሉ። እና ያ ሁሉንም ለመግደል ምክንያት ይሆን?” ብለው ይጠይቃሉ።

ሰር ሰልማን እና ማታርን ተገናኝተው አያውቁም። ችሎቱ ጉዳዩን ማየት ሲጀመር ፊት ለፊት ሊተያዩ ይችላል።

ችሎቱ የዘገየዉ የተከሳሽ ጠበቆች ማስረጃ ሊሆን ስለሚችል በሚል የሰር ሰልማንን መጽሐፍ ለመመልከት መብት አለን ሲሉ በመከራከራቸው ነው።

‘ሰይጣናዊ ጥቅሶች’ ለምን አከራካሪ ሆነ?

ሰልማን ራሽዲ በ1981 ለተደራሲያን ባበቁት ሚድናይትስ ቺልደረን በሚለው ሥራቸው የዝናን እርካብ ለመውጣት ቻሉ። በዩናይትድ ኪንግደም ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቅጂዎችን ለመሸጥም ችለዋል።

አራተኛው መጽሐፋቸው ግን ተቃውሞም አስነሳ። “ሰይጣናዊ ጥቅሶች” ነቢዩ መሐመድን መግለጹ እና ሃይማኖትን መነካካቱ እንደ ስድብ ተቆጥሮ በብዙ ሙስሊም አገሮች ታግዷል።

ወቅቱ የኢራን መሪ አያቶላህ ሩሆላህ ካሚኒ እአአ በ 1989 ፈትዋ (ሃይማኖታዊ ድንጋጌ) አውጀዋል። ራሽዲ እንዲገደል እና ለዚህም 3 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፍሉ አስታወቁ። ፈትዋው ከዚያ ወዲህም አልተሳም።

በዚህ ምክንያት ራሽዲ ለአስር ዓመታት ያህል ለመደበቅ ተገደደዋል። በሚደርስባቸው የግድያ ዛቻ ምክንያት የታጠቀ ጠባቂ አስፈልጓቸዋል።

ሳልማን ሩሽዲ ታዋቂነትን እና የጥቃት ስጋት ካስከተለባቸው 'ዘ ሳታኒክ ቨርስስ' ጋር
የምስሉ መግለጫ,ሳልማን ሩሽዲ ታዋቂነትን እና የጥቃት ስጋት ካስከተለባቸው ‘ዘ ሳታኒክ ቨርስስ’ ጋር

ሃይማኖታቸውን ከማይተገብሩ ሙስሊሞች ተወለዱት ራሺድ ኢአማኒ ናቸው። ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተሟጋች ሆነው ቆይተዋል።

ይህ “በጣም አስቸጋሪ” ሆኗል ሲሉ ግን አስጠንቅቀዋል።

የመናገር ነጻነትን መከላከል እጅግ አስቸጋሪ ሆኗል የሚሉት ሩሽዲ “በርካታ ወጣቶችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች የንግግር ነፃነትን መገደብ ብዙ ጊዜ ጥሩ ሃሳብ ነው የሚል አመለካከት ይዘዋል” ይላሉ።

“የመናገር ነፃነት ዋናው ነጥብ እርስዎ ያልተስማሙበትን ሃሳብ እንዲጸባረቅ መፍቀድ አለብዎት።”

ሰር ሳልማን በአጥቂው ስለት በተደጋጋሚ ተወግተው በደም ተዘፍቀው ወለል ላይ ተዘርግተው ሳለ እንዴት ስለግል ንብረቶቻቸው “እንደ ጅል እንዳሰቡ” አይዘነጉትም።

የለበሱት እጅግ ውድ የሆነው ሱፋቸው ይበላሽ ይሆን፣ የቤታቸው ቁልፎች እና ክሬዲት ካርዶ ከኪሳቸው ይወድቁ ይሆን ብለው ተጨንቀው እንደነበር ያስታውሳሉ።

“አጋጣሚው በጣም አስቂኝ ነው። ነገር ግን ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳስበው ላለመሞት እንዳስብ ያደረጉኝ አንዳንድ ጥቂት ነገሮች ነበሩኝ። ‘የቤቴን ቁልፎች ያስፈልጉኛል፤ የክሬዲት ካርዶቼን እፈልጋቸዋለሁ’ ያልኩባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ” ብለዋል።

አክለውም “ትኖራለህ፣ ትኖራለህ፣ ትኖራለህ” እያለ የሚነግራቸው “የመትረፍ ደመ ነፍስም” ነበራቸው።

ሰር ሳልማን ሩሽዲ ከባለቤታቸው ራቼል ኤሊዛ ግሪፍትስ ጋር
የምስሉ መግለጫ,ሰር ሳልማን ሩሽዲ ከባለቤታቸው ራቼል ኤሊዛ ግሪፍትስ ጋር

ከጥቃቱ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ሰር ሳልማን ሩሽዲ አምስተኛ ሚስታቸውን አግብተዋል። ባለቤታቸው አሜሪካዊቷን ገጣሚ እና ደራሲ ራቼል ኤሊዛ ግሪፍትስ ናቸው።

ባለቤታቸው ስለ ጥቃቱ ሲሰሙ “መጮህ ጀመረኩኝ። ይህ በሕይወቴ ውስጥ በጣም የከፋው ቀን ነው አልኩኝ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሐኪሞች ዐይኑን ቆቦች ሲሰፉ ከሳልማን ሩሽዲ ጎን መገኘታቸውን ገልጸዋል።

“ዐይኖቹን እወዳቸዋለሁ። ከቤት ሲወጣ ከሁለቱ ዐይኖቹ ጋር ነበር። ቀጥሎ ዓለማችን ተለወጠች። አሁን ዓለም አተያዩ በመለወጡ ምክንያት አንድ ዐይኑን የበለጠ እወደዋለሁ” ብለዋል።

“በዚህ ግጭት ውስጥ ሁለት ኃይሎች ነበሩ። አንዱ የአመጽ፣ የአክራሪነት፣ የትምክህተኝነት ሲሆን ሌላው ደግሞ የፍቅር ኃይል ነበር። በእርግጥም የፍቅር ኃይል በባለቤቴ ኤሊዛ ምስል ውስጥ ተካትቷል” ብለዋል ደራሲው።

“በመጨረሻም የሆነውን ነገር የምረዳው የፍቅር ኃይል ከጥላቻ ኃይሎች የበለጠ ጠንካራ መሆኑን ነው።”

ሰር ሳልማን በርካታ ሰዎች የሚታደሙባቸው ዝግጅቶችን እንደገና እንደሚያዘጋጁ ተናግረዋል። ነገር ግን ወደፊት “ይበልጥ ጥንቃቄ” ያደርጋሉ። “የደኅንነት ጥያቄው የመጀመሪያው ጉዳይ ይሆናል። በደኅንነቴ ጉዳይ ካልረካሁ በዝግጅቱ አልሳተፈም።”

አክለውም “ነገር ግን የተገደበ ሕይወት እንዲኖረኝ አልፈልግም” ሲሉ ተናግረዋል።