
ከ 6 ሰአት በፊት
ትርሐስ ተስፋይ ኑሮዋን በምዕራብ ለንደን ጥገኝነት ጠያቂዎች በሚኖሩበት ሆቴል ካደረገች አንድ ዓመት ሆኗታል።
በኢትዮጵያ የብስክሌት ሻምፒዮናዋ ትርሐስ በትግራይ ጦርነት ምክንያት ከአገሯ ተሰዳ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ ጥገኝነት ጠይቃለች።
በምትኖርበት የጥገኝነት ጠያቂዎች ሆቴል ሆናም በግንቦት ወር ለሚካሄደው የለንደን ትልቁ የብስክሌት ውድድር ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ ናት።
በዩናይትድ ኪንግደም የዜግነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት እስኪያገኝ ድረስ ጥገኝነት ጠያቂዎች በሚኖሩበት ሆቴል ውስጥ ሆና ነው ‘ራይድ ለንደን’ ለተሰኘው ትልቁ የብስክሌት ውድድር እየተዘጋጀች ያለችው።
በባለፈው ዓመት ውድድር ከ22 ሺህ በላይ ብስክሌተኞችን ያሳተፈው ‘ራይድ ለንደን’ የተሰኘው ውድድር ከፍተኛ ስፍራም የሚሰጠው ነው።
ትርሐስ በሆቴሉ ኑሮዋ በሳምንት ከመንግሥት የሚሰጣትን 10 ፓውንድ (700 ብር ገደማ) አብቃቅታ መኖር አለባት።
የ22 ዓመቷ ትርሐስ ሁኔታዎች ፈታኝ ቢሆኑባትም በመጪው ግንቦት 18/2016 ዓ.ም. ለሚደረገው የ‘ራይድ ለንደን’ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ቁርጠኛ ናት።
የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የጥገኝነት ጠያቂዎች ሆቴሎች የአገሪቱ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ያወጣውን የአመጋገብ ሥርዓት ‘ኢትዌል’ መስፈርቶችን ያሟላሉ ይላል።
ትርሐስ ሳይክል ለመጀመሪያ ጊዜ የነዳችው በ13 ዓመቷ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ሳይክል ተወዳዳሪ በሆነው ወንድሟ አበረታችነት ነበር የጀመረችው።
በሳይክል ውድድር ውጤታማ የሆነችው ትርሐስ በአፍሪካ ኮንቲኔንታል ሻምፒዮና ወርቅ በማሸነፍ እንዲሁም በተለያዩ የኢትዮጵያ ሻምፒዮናዎች ተሳትፋለች።
በጥቅምት 2013 ዓ.ም. በትግራይ የተቀሰቀሰው ደም አፋሳሽ ጦርነት ለመቶ ሺዎች እልቂት እና በርካታ የትግራይ ተወላጆች እንዲፈናቀሉ እና ከአገር እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል።
ትርሐስ ጦርነቱን ተከትሎ ከተፈናቀሉት መካከል አንዷ ናት።
ባለፈው ዓመት ወደ ዩኬ የገባችው የትርሐስ የአኗኗሯ ሁኔታ በዩኬ ሃውስ ኦፍ ኮመንስ (በላይኛው ምክር ቤት) መወያያ ሆኗል። አንዲ ስላውተር የተባሉት የፓርላማ አባል አመጋገቧ ላይ ያደረባቸውን ስጋት አቅርበዋል።
በዚህ ሆቴል ውስጥ ያለው ኑሮዋ “በጣም መጥፎ ከመሆኑ የተነሳ፣ እያሳመማት እንደሆነ እና መወዳደር አትችልም” ሲሉም አስረድተዋል።
- ኤርትራዊው ብስክሌተኛ ቢንያም ግርማይ ጂሮ ዲኢታሊያ ውድድርን በማሸነፍ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሆነ18 ግንቦት 2022
- ከዩኒቨርስቲ ትምህርት ብስክሌትን የመረጠው ኢትዮጵያዊ ብስክሌተኛ በዓለም አቀፍ ውድድር ላይ18 የካቲት 2024
- “የአፍሪካ የብስክሌት ንጉሥ” የተባለው ኤርትራዊው ቢኒያም ግርማይ15 ሀምሌ 2023

ትርሐስ ገና መጀመሪያ ላይ በመጣችበት ወቅት “በጥገኝነት ጠያቂዎች ሆቴል ውስጥ ያስቸገረኝ ምግቡ ነበር” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
“ምግቡ ሳምንት የቆየ ያህል የሻገተ ጣዕም እንዳለው እና በፕላስቲክ ገንዳ ይቀርባል” ብላለች።
አብዛኛውን ጊዜ የሚመገቡት ፓስታ፣ ማካሮኒ እና ሩዝ እንደሆነም እና “በሆቴሉ ውስጥ ለማረፍ እና ዘና ለማለት ፈታኝ እንደነበር” ገልጻለች።
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ከምዕራብ ለንደን ‘ዌልካም ኮሚኒቲ’ ማዕከል እንዲሁም ለትርፍ ያልተቋቋመው ‘ቲም አፍሪካ ራይዚንግ’ የተባለው የሳይክል ተወዳዳሪዎች ቡድን ድጋፍ እያደረገላት ይገኛል።
የማኅበረሰብ ማዕከሉ ለስደተኞች እና ለጥገኝነት ጠያቂዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋን በማስተማር እንዲሁም ምግብ ይሰጣቸዋል። በተጨማሪም ከማኅበረሰቡ ጋር በቀላሉ እንዲዋሃዱ እና መገለልም እንዳይኖር ምክር ይለግሳል።
ለትርሐስም የመወዳዳሪያ ቁሳቁሶችን የሰጣት ሲሆን፣ እሷም በቀን ከአምስት እስከ ስድስት ሰዓታት በመለማመድ ላይ ትገኛለች።
“ማኅበረሰቡ ለእኔ ብስክሌት ለመስጠት ገንዘብ ሲያሰባስብልኝ በጣም ደስተኛ ነበርኩ” ትላለች ትርሐስ።
“መጀመሪያ ወደ ማዕከሉ የመጣሁት ለመማር ነበር። ነገር ግን ሲጠይቁኝ ብስክሌተኛ እንደሆንኩ ነገርኳቸው። ላደረጉልኝ ነገር ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ።”
የማዕከሉ ዳይሬክተር ጆአን ማክልነስ ትርሐስ በኢትዮጵያ የብስክሌት ውድድር ሻምፒዮን መሆኗን ሲሰሙ በሁሉም ላይ ደስታ መፈጠሩን ይናገራሉ።
“ትርሐስ በጣም ቆራጥ እና ተወዳጅ በመሆኗ ለመርዳት በጣም ቀላል ነው” ይላሉ።
“በማዕከሉ የተራራ ላይ ብስክሌቶች አሉን እሷም በእነዚህ በተሰጡን የተራራ ብስክሌቶች ልምምድዋን መሥራት ጀመረች። ነገር ግን የፕሮፌሽናል ብስክሌት እንደሚያስፈልጋት ተገነዘብን” በማለት ያስረዳሉ።
የፕሮፌሽናል ብስክሌት ለመግዛት የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ ተጀምሮ ከሳምንት ገደማ በኋላ ማዕከሉ የሚያስፈልጋትን ብስክሌት ለትርሐስ ገዛላት።
“ካላት ደረጃ በታች እንዲሁም ለመነሻ ውድድር የሚሆን ብስክሌት ነው። ነገር ግን መለማመድ የምትችልበት ነው” ይላሉ ዳይሬክተሯ።

ማዕከሉ ለትርሐስ 5 ሺህ ፓውንድ ማሰባሰብ የቻለ ሲሆን፣ ይህም ለልምምድ፣ ለምግቧ እና ለውድሩ ጉዞ የሚሆናት ነው።
“በእነዚያ ሆቴሎች ውስጥ ሰዎች በርካታ ጊዜያቸውን ሲያሳልፉ ታያለህ። እዚህ ሲመጡ ተስፋ ሰንቀው ቢሆንም፣ ከወራት ወደ ወራት ከአስከፊ አመጋገብ በኋላ ተስፋቸው ይሟሽሻል። ሥራ መሥራት አትችልም። የምታገኘው 8.86 ፓውንድ ነው። ወጥተው እንኳን ቡና መጠጣት አይችሉም። የትም መሄድ አይችሉም። በርካታ ሰዎች ድብርት ውስጥ ይገባሉ” ሲሉ ያስረዳሉ።
“ነገር ግን ትርሐስ አንድ ሰው የጂም ካርድ እያመጣላት አምስት፣ ስድስት ሰዓታት በብስክሌት ማሽኑ ላይ እየሠራች ነበር የምታሳልፈው። የአካል ብቃት እንቅስቃሴዋን ከመጠበቅ ዝንፍ አላለችም። በሚያስደንቅ ሁኔታ ቁርጠኛ ናት እናም ይህም አበረታች ነው” ይላሉ።
የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለጥገኝነት ጠያቂዎች መጠለያ የሚሰጠው ምግብ የአገሪቱ የብሔራዊ የጤና አገልግሎት የአመጋገብ ሥርዓት ‘ኢትዌል’ መመዘኛዎችን የሚያሟላ እንደሆነ ይከራከራል።
በተጨማሪም የሁሉንም ባህል እና የአመጋገብ ፍላጎትን መሠረት ባደረገም መልኩ ይሰጣል ይላል።
“በእነዚህ ሆቴሎች ውስጥ ስለሚሰጡ ማንኛውም አገልግሎቶች ስጋቶች በሚነሱበት ጊዜ እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱ ከአቅራቢዎች ጋር አብረን እንሠራለን” ሲሉ የመሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
አክለውም “ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢደርስም ለጥገኝነት ጠያቂዎች ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን፤ ያለኛ ድጋፍ ምንም አይኖራቸውም” ብለዋል።
ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚስተናገዱበት መጠለያ እንዲሁም በቀን ሦስት ጊዜ ምግብ፣ መክሰስ እና ሳምንታዊ አበል እንደሚሰጣቸውም አስረድተዋል።