ስደተኞች

ከ 5 ሰአት በፊት

በአሜሪካ እና ሜክሲኮ ድንበር ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ድንበር የሚያቋርጡ ሰዎች ቁጥር በካሊፎርኒያ ግዛት በኩል ጭማሪ አሳየ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መድረሻቸውን አሜሪካ ማድረግ የፈለጉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ከሜክሲኮ በቴክሳስ ግዛት በኩል ወደ አሜሪካ ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

አሁን ደግሞ በካሊፎርኒያ ግዛት በኩል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ወደ አሜሪካ ድንበር ለመሻገር ሲሞክሩ ቢቢሲ ተመልክቷ።

አብዛኛዎቹ ከኢኳዶር፣ ኮሎምቢያ፣ ቻይና፣ ብራዚል እና ሩዋንዳ የሆኑት ስደተኞች በሳን ዲዬጎ የድንበር በር ወደ አሜሪካ ለማቋረጥ ተሰባስበው ይታያሉ።

መነሻቸውን ከአፍሪካዊቷ ጊኒ ያደረጉ ስደተኞች በአገራቸውን ያለውን ፖለቲካዊ አለመረጋገት ለመሸሽ ቀድመው ወደ ቱርክ ኢስታንቡል ከዚያ ወደ ኮሎምቢያ ከበረሩ በኋላ ከኮሎምቢያ ወደ አሜሪካ በእግር መጓዛቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አሜሪካ እና ሜክሲኮ 3ሺህ 140 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ድንበር ይጋራሉ። በዚህ ድንበር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ወደ አሜሪካ እየገቡ ሲሆን የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ይህን ፍልሰት ለማስቆም በቂ እርምጃ አልወሰደም ተብሎ ይተቻል።

የአሜሪካ የኢሚግሬሽን እና የድንበር ደኅንነት ጉዳይ የቀጣይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መከራከሪያ ዋነኛ አጀንዳ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

እስካሁን ድረስ ስደተኞች ሲያቋርጡ የነበረው በቴክሳስ ግዛት በኩል ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሪዞና እና ካሊፎርኒያ ስደተኞች ድንበር ማቋረጥ የሚሹባቸው ግዛቶች ሆነዋል።

ቴክሳስ ውስጥ በሚገኙ የድንበር መሻገሪያዎች በቀን እስከ 2ሺህ300 ስደተኞች ወደ አሜሪካ ድንበር ሲሻገሩ ቆይተዋል።

በሳን ዲዬጎ ደግሞ በቀን እስከ 1ሺህ ሰዎች እየገቡ እንደሆነ የአካባቢው ባለስልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አሜሪካ በስደተኞች የመጥለቅለቋ ጉዳይ የመሠረተ ልማት ግልጋሎቶችን ከማጨናነቁ አልፎ የአካባቢው ባለስልጣናት እና ነዋሪዎችን እያመረረ ይገኛል።

በቅርቡ ዎል ስትሪት ጆርናል የሰራው የሕዝብ አስተያየት በአሪዞና፣ ጆርጂያ፣ ሚሺጋን፣ ኔዛዳ፣ ኖርዝ ካሮላይና፣ ፔንስለቬኒያ እና ዊስኮንሲን ግዛቶች ለምርጫ የተመዘገቡ መራጮች ዋነኛ ጉዳያችን የኢሚግሬሽን ጉዳይ ነው ብለዋል።

በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውስጥ ወሳኝ በሆኑት በእነዚህ 7 ግዛቶች የሚኖሩ ድምጽ ሰጪዎች የአገሪቱ የኢሚግሬሽን ፖሊሲ እና የድንበር ደኅንነት በትክክለኛው አቅጣጭ እየተጓዘ አይደለም ብለው ያምናሉ።

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ የሚሻገሩ ስደተኞችን ለማቆም የድንበር አጥር እስከመገንባት የደረሰ እርምጃ ሲወስዱ ቆይተዋል።

በቀጣይ ምርጫ ሪፓብሊካኖችን ወክለው እንደሚቀርቡ የሚታመነው ትራምፕ አሁን ላይ በአሜሪካ-ሜክሲኮ ድንበር ላይ ለተፈጠረው የስደተኞች ፍልሰት ቀውስ የባይደን አስተዳደርን አጥብቀው ይተቻሉ።