

April 21, 2024
- በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ2 ቢሊዮን ብር መጭበርበሩን ገልጿል
- ቀሲስ በላይ መኮንን በማጭበርበር ድርጊት ፍርድ ቤት ቀርበዋል
በዮሐንስ አንበርብር
የአገሪቱ ባንኮች ከአሠራር ጋር በተያያዙ ክፍተቶች በተለያዩ ሥልቶች ለሚፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶች በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ እየሆኑ መምጣታቸውን፣ ይህ ሁኔታም በቀጣይ የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ ውስጥ የበለጠ እንደሚጨምር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
ብሔራዊ ባንክ የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ጤናማነትን በመገምገም ሚያዝያ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ የአገሪቱ ባንኮች በበይነ መረብ ማጭበርበርያ ሥልቶች፣ ከባንኮች የውስጥ ሠራተኞችና ከሦስተኛ ወገን በሚደርሱባቸው የምዝበራ ድርጊቶች በከፍተኛ ደረጃ እየተጋለጡ መሆናቸውን አስታውቋል።

ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ማለትም እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በሐሰተኛ ሰነዶችና በሌሎች የማጭበርበር ድርጊቶች ባንኮች አንድ ቢሊዮን ብር ማጣታቸውን፣ ብሔራዊ ባንክ በግምገማ ሪፖርቱ ገልጿል። በዚህ መንገድ የተመዘበሩት የገንዘብ መጠንም ከቀዳሚው ዓመት በእጥፍ የጨመረ መሆኑን አስታውቋል።
የባንክ ማጭበርበሮች በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ሲደርሱ፣ ከአምናው በእጥፍ ማደጋቸው ተገልጿል። እነዚህ ጉዳዮች የተከሰቱትም በዋናነት ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶችንና ቼኮችን በመጠቀም ገንዘብ በማጭበርበር፣ ያልተፈቀደ የባንክ ዋስትና በማቅረብ፣ የተሰረቁ የኤቲኤም ካርዶችን በመጠቀም ገንዘብ በማውጣት ድርጊትና በሐሰተኛ የስልክ ጥሪዎችና አጭር የጽሑፍ መልዕክቶችን በመጠቀም እንደሆነ ብሔራዊ ባንክ ገልጿል። በተጠቀሱት የማጭበርበሪያ ሥልቶችም 20 ባንኮች ጉዳት እንደደረሰባቸው ሪፖርቱ አመልክቷል። በተጨማሪም በሰኔ ወር 2015 መጨረሻ ላይ ሦስት ባንኮች 200 ሚሊዮን ብር መዘረፋቸውን አስታውቋል።
የአገሪቱ ባንኮች ቅልጥፍናንና ፋይናንስ ተደራሽነትን የሚያጎለብቱ በቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረቱ አዳዲስ ምርቶችንና አገልግሎቶችን እያስተዋወቁ ቢሆንም፣ ከዚህ ጋር በተያያዙ የአሠራር ክፍተቶች በከፍተኛ ደረጃ ለአደጋ እየተጋለጡ መሆናቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።
በተጨማሪም ከሦስተኛ ወገኖች ጋር በሽርክና የሚሰጧቸው የአነስተኛ ብድር ቁጠባ (የዲጂታል ማይክሮ ክሬዲትና ቁጠባ) አገልግሎቶችን በከፍተኛ ደረጃ እያስፋፉ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ፣ የማጭበርበር ድርጊቶች እየጨመሩ ሊሄዱ እንደሚችሉ አሳስቧል።
በመሆኑም ከአሠራር ጋር የተያያዙ አደጋዎችን ለመከላከልና የመጭበርበር ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ፣ ውጤታማ የቁጥጥር ሥልቶችንና አሠራርችን በመተግበር ላይ እንዲያተኩሩ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
ብሔራዊ ባንክ እስከ 2015 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ያለውን የባንኮች ተጋላጭነት ሁኔታ ብቻ ያመላከተ ቢሆንም፣ በቅርቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባጋጠመው የሲስተም ችግር 801.4 ሚሊዮን ብር ተመዝብሮ 95 በመቶውን ማስመለሱ መግለጹ ይታወሳል።
ይህ በዚህ እንዳለ ማክሰኞ ሚያዚያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. ቀሲስ በላይ መኮንን የተባሉ ግለሰብ በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በአካል በመቅረብና ከአፍሪካ ኅብረት ኦፊሳላዊ የክፍያ ሰነድ ጋር ተመሳስለው የተዘጋጁ የተለያዩ ሐሰተኛ የክፍያ ሰነዶችን በመጠቀም፣ ከአፍሪካ ኅብረት የባንክ ሒሳብ ወደ ሌላ የባንክ ሒሳብ ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ (367 ሚሊዮን ብር የሚሆን) ለማዘዋወር ሲሞክሩ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል።
ግለሰቡ ያቀረቡትን ሐሰተኛ የክፍያ ሰነድ የተጠራጠሩት የባንኩ ሠራተኞች ለአፍሪካ ኅብረት የሥራ ኃላፊዎች ስልክ በመደወል ለባንኩ ስለቀረቡት የክፍያ ሰነዶችና እንዲከፈል ስለተጠየቀው የገንዘብ መጠን በማሳወቅ፣ የክፍያ ትዕዛዙ ትክክለኛነት እንደጠየቁ ለማወቅ ተችሏል። የአፍሪካ ኅብረት የሥራ ኃላፊዎችም የተጠቀሰውን የክፍያ ሰነድ እንደማያውቁትና ኅብረቱም የተባለውን የክፍያ ትዕዛዝ እንዳልሰጠ ማሳወቃቸውን የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል። ይህንንም ተከትሎ የክፍያ ሰነዱን ይዘው ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለማዘዋወር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአፍሪካ ኅብረት ቅርንጫፍ በአካል የተገኙት ቀሲስ በላይ፣ የኅብረቱ የፀጥታ ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር ካዋሉዋቸው በኋላ ለፌዴራል ፖሊስ አስረክበዋቸዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ተጠርጣሪውን ቀሲስ በላይ ሐሙስ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት አቅርቧቸዋል።
ፌደራል ፖሊስም ቀሲስ በላይ በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በአካል ቀርበው ሐሰተኛ የክፍያ ሰነዶችን በመያዝ፣ ለሦስት ግለሰቦችና ለአንድ የግል ድርጅት የባንክ ሒሳቦች በድምሩ ስድስት ሚሊዮን 50 ሺሕ ዶላር ሊያዘዋውሩ ሲሉ በአፍሪካ ኅብረት የፀጥታ ሠራተኞች ተይዘው ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ተላልፈው መሰጠታቸውን በመጥቀስ፣ የተጠረጠሩበትን የወንጀል ድርጊት ለችሎቱ በማስረዳት ተጨማሪ ምርመራ ለማከናወን የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።
ተጠርጣሪ ቀሲስ በላይ በበኩላቸው የተባለውን ድርጊት እንደፈጸሙ ያመኑ ቢሆንም፣ በወንጀል ድርጊት እንዳልተሳተፉ በመግለጽ ችሎቱ የዋስትና መብት እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።
ችሎቱ የግራ ቀኝ ክርክር ካዳመጠ በኋላ ተጠርጣሪው ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ በማለፍ፣ ለፖሊስ የሰባት ቀናት የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፈቅዷል።