ዜናየመንግሥትና የሃይማኖት ተቋማትን ግንኙነት በግልጽ የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

ፅዮን ታደሰ

ቀን: April 21, 2024

መንግሥትና ሃይማኖት አንዱ በአንዳቸው ተግባርና እንቅስቃሴ ውስጥ ጣልቃ አይገቡም የሚለውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መሠረት በማድረግ፣ መንግሥት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት በግልጽ የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱ ተገለጸ፡፡ 

በሰላም ሚኒስቴር የሃይማኖት ጉዳዮች ዴስክ ተጠባባቂ ኃላፊ አቶ ሀለፎም ዓባይነህ፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያለው ድንጋጌ ሃይማኖትና መንግሥት አይደራረሱም ማለት እንዳልሆነና በጋራ የሚሠሩባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ ሆኖም በሕገ መንግሥቱ ያለው ድንጋጌ ጥቅል መርሆዎችን የያዘ በመሆኑ፣ ይህን ለማብራራት ሕግ በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ 

‹‹ባለድርሻ አካላት የተሳተፉባቸው ሦስት ጥናቶች ተካሂደው ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ከተወሰኑ ቤተ እምነቶች ጋር ውይይት ተጀምሯል፤›› ብለዋል፡፡ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ የተካተቱ ዝርዝር ጉዳዮች ምንድናቸው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ወደፊት ይፋ ሲደረግ ይገለጻል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 3፣ ‹‹መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤›› ሲል ይደነግጋል። በሌላ በኩል የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 5፣ ሃይማኖትና እምነትን የመግለጽ መብት በሕግ ሊገደብ እንደሚችል ይደነግጋል። በዚሁ አንቀጽ ላይ መንግሥት ሃይማኖትና እምነትን የመግለጽ መብት ላይ ገደብ ሊጥል እንደሚችልና ይህንን የሚያደርገው የሕዝብን ደኅንነት፣ ሰላም፣ ጤና፣ ትምህርት፣ የሞራል ሁኔታ፣ የሌሎች ዜጎችን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶችን፣ እንዲሁም መንግሥት ከሃይማኖት ነፃ መሆኑን ለማረጋገጥ ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል። 

ከአንድ ወር በፊት ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችና ከተለያዩ የሃይማኖት ተወካዮች ጋር በተናጠል ውይይት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በተለይ ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ከእስልምና ሃይማኖት አባቶች ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች መንግሥት በቅርቡ ሃይማኖትን የተመለከተ ሕግ እንደሚያወጣ መናገራቸው ይታወሳል። በተለይ ከእስልምና ሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት መስኪዶች የሚያደርጉት የአዛን ጥሪ፣ እንዲሁም በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሚከናወኑ ቅዳሴና አስተምህሮዎች ሌላውን ሰው ማወክ ስለሌለባቸው አስቡበት በማለት ስለሚወጣው ሕግ ይዘት ፍንጭ ሰጥተው ነበር። 

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንድ የሪፖርተር ምንጭ እንደገለጹት፣ በቅርብ ወራት ውስጥ ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ሕግ በሃይማኖት ተቋማት ድርጊትና እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት የሚገኙበት ቅጥር ግቢ ውስጥ የሕዝብ ደኅንነትን፣ ሰላምን፣ የሞራል ሁኔታንና የትምህርት ሥርዓቱን የሚያውኩ ተግባራት ለመከላከል ገደብ የሚጥሉ ድንጋጌዎችን እንደሚይዝ ገልጸዋል። በዋናነትም የሃይማኖት ተቋማት ቅጥር ግቢ ውስጥ የጦር መሣሪያ ወይም መሰል ያልተፈቀዱ ጉዳት የሚያደርሱ ቁሶችን ይዞ መግባትና መሸሸግ እንደሚከለከሉ ምንጩ ገልጸዋል። 

ለዚህም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የትጥቅ ትግል የሚያራምዱ ኃይሎች የሃይማኖት ተቋማትን መሸሸጊያ ማድረጋቸው መነሻ መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በሃይማኖት ተቋማት የተመሠረቱ ትምህርት ቤቶች የአገሪቱን የትምህርት ሥርዓት ማክበር እንዳለባቸው፣ በትምህርት ተቋማት ውስጥ ሃይማኖትን የመግለጽ መብትና የሃይማኖት መገለጫ አልባሳት አጠቃቀም ላይ ገደብ የሚጥል ድንጋጌ እንደሚይዝ ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር በተገናኘም የሃይማኖት ተቋማት ሃይማኖታዊ ተግባርና አስተምህሮዎች የፖለቲካ ግጭት መንስዔ እንዳይሆኑ፣ የሌሎች ዜጎችን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶችን እንዳይጋፉ ወይም እንዳያውኩ ለማድረግ እምነትን የመግለጽ መብት ላይ ገደብ የሚጥሉ ድንጋጌዎች እንደሚኖሩ ምንጩ አብራርተዋል፡፡