
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰብሳቢነት ውሳኔውን ባስተላለፈበት ወቅት
ዜና በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት…
ቀን: April 21, 2024
- የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል
በፅዮን ታደሰ
የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን በቅርቡ ባቀረበው ረቂቅ ፖሊሲ የፍርድ ቤቶችን ሒደት በሚመለከት ልዩ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም የሚለው ምክረ ሐሳብ ውድቅ ተደርጎ፣ በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ልዩ ችሎት በማቋቋም እንዲታይ ተወሰነ፡፡
የባለሙያዎች ቡድን ባቀረበው ምክረ ሐሳብ ተጠያቂነት በየትኛው ፍርድ ቤት ይታይ ለሚለው አሁን ባሉት ተቋማት ልዩ ችሎትም ሆነ አዲስ ፍርድ ቤት በማቋቋም የተጠያቂነትን ሥራ ማከናወን አዳጋች ስለሚሆን አዲስ፣ ነፃና ገለልተኛ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡
ልዩ ፍርድ ቤቱ ዓለም አቀፍ ሕጎችንና መርሆዎችን እንዲሁም የአገር ውስጥ ሕጎችንና አሠራሮችን የሚከተል መሆን እንደሚገባ በማስታወቅ በተሳታፊዎች የተነሱ ሥጋቶችን ለመቅረፍ፣ ተጎጂዎችንና ተከሳሾችን በሒደቱ ላይ አመኔታ እንዲኖራቸው ለማድረግ ልዩ ፍርድ ቤት ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን በምክረ ሐሳቡ ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ረቂቅ ፖሊሲውን ባፀደቀበት ወቅት ተጠያቂነት በየትኛው ፍርድ ቤት ይታይ ለሚለው፣ ልዩ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም የሚለውን የቡድኑን ምክረ ሐሳብ ውድቅ አድርጎ በመደበኛ ፍርድ ቤት ልዩ ችሎት እንዲቋቋም በማለት ማፅደቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ቡድኑ ይፋ አድርጎት በነበረው ሪፖርት ላይ በግልጽ እንደ ተቀመጠው ልዩ ፍርድ ቤት ማቋቋም የሚለው አማራጭ አብላጫ ድጋፍ አግኝቶ የነበረ ሲሆን ልዩ ችሎት፣ ቅይጥ ፍርድ ቤትና ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤትን ያካተቱ የተለያዩ የድጋፍ ቁጥሮች የሚገልጹ አማራጮችም ቀርበው ነበር፡፡
የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የወንጀል ተጠያቂነትን በተመለከተ ጉዳቱ በደረሰበት አባል አገር ውስጥ ፍርድ ቤቶች ካሉና ማኅበረሰቡ በፍርድ ቤቶች ላይ አመኔታ ካለው፣ በገለልተኛ አገራዊ ፍርድ ቤቶች አማካይነትና አግባብነት ባላቸው አገራዊ ሕጎች መሠረት ሊሆን እንደሚገባ ይገልጻል፡፡
ነገር ግን አገራዊ ፍርድ ቤቶች አቅም የሌላቸው ከሆነ ወይም ኅብረተሰቡ አመኔታ ከሌለው ልዩ ፍርድ ቤቶችን፣ ልዩ ሰሚ አካላትን ወይም ጥምር ፍርድ ቤቶችን ማቋቋም እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡ ቡድኑም ይህንን መሠረት በማድረግ ልዩ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም ምክረ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡
ቡድኑ ካቀረባቸው 99 በመቶ ያህሉን ምክረ ሐሳቦች መንግሥት ተቀብሎ አፅድቆታል ያሉት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሪፖርተር ምንጭ፣ ይህም ትልቅ ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ተጠያቂነት በልዩ ፍርድ ቤት ይታይ ተብሎ የቀረበው ግን በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ልዩ ችሎት እንዲቋቋም በሚኒስትሮች ምክር ቤት መወሰኑንና የዳኞች አሿሿም፣ የሕዝብ ተሳታፊነትና ገለልተኝነት የሚሉ ሐሳቦች በቡድኑ ምክረ ሐሳብ መሠረት ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡
የወንጀል ምርመራና የክስ ተግባር ተቋማዊ አደረጃጀትን በሚመለከት ቡድኑ ያቀረበው፣ አሁን ካለው የዓቃቤ ሕግ ተቋማት ውጪ የምርመራና የክስ ሒደቶችን የሚያከናውን ልዩ ነፃና ገለልተኛ የዓቃቤ ሕግ ተቋም መቋቋም አለበት የሚለው ምክረ ሐሳብ ተቀባይነት ማግኘቱን ምንጩ ገልጿል፡፡
የእውነት ማፈላለግና የዕርቅ ተግባራት ተቋማዊ አደረጃጀትን በተመለከተ፣ አዲስ የሀቅ አፈላላጊ ኮሚሽን ማቋቋም አስፈላጊ ነው ተብሎ በቡድኑ የቀረበው ሐሳብም በተመሳሳይ ተቀባይነት አግኝቷል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ የኤርትራ ወታደሮች እንዴት ለፍርድ ይቀርባሉ ተብሎ ለሚነሳው ጥያቄ ወንጀሉ በኢትዮጵያ እስከተፈጸመ ድረስ የየትኛውም አገር ዜጋ ቢፈጽመው ተጠያቂነት ይኖርበታል ብለው፣ በሌሉበትም ቢሆን ችሎቱ እንዲካሄድ የፍርድ ሒደቱን ያከናውናል መባሉን ገልጸዋል፡፡