
By አንባቢ
April 21, 2024

- ሐረር እና ‹‹405››
በአሸናፊ ካሳ
መግለጽ ከምችለው በላይ ተኩላለች። ወትሮም ለእንግዶቿ ምቾት የምትታትረው ሐረር አሁን ደግሞ መንገዶቻን አጽድታ ግድግዳዎቻን አድሳ ቀብታ መገለጫዎቿን አውጥታ ሰለትኹ (እንኳን ደህና መጣችሁ) ብላ ትቀብላለች። ማኅበረሰቡ፡ ሕፃናት፣ ትልቁ፣ ትንሹ፣ አሮጊት፣ ሽማግሌው፣ ወጣቱ እንስቶቹ ሁሉም ቀሽት ሁነው በፈናን ነው ሰለትኹ ሳላም የሚሉት።

አብዛኞቹ ፎቶ ጄኒክ ሲሆኑ በአንድ ብልጭታ አሪፍ ምስል ከደማቅ ፈገግታ ጋር ይወጣል።
ዘንድሮ ሐረር ሸዋል ዒድን ከ500 ዓመት በላይ ራሳ ፈጥራ በትውልድ ቅብብሎሽ አዝልቃ አድምቃ በማቆየቷ በዓለም አቀፉ የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት አስመዝግባ ለታላቋ ኢትዮጵያ መሰል ስብስቦቿን 16 በማድረስ የአፍሪካ ቀዳሚነቷ እንዲደምቅ አድርጋለች።
አቦ ሐረሪ፣ ኢትዮጵያ ታመሰግንሻለች!
ምስጋና ለጉዞ አዘጋጁ ቢኒ ፓሽን ኢትዮጵያና አንበሲት አጽናፍ ዓለሙ ይሁንና የምናፍቃት ሐረር ስትሞሸር ታደምኩ፡፡ አገሬንም እንደአዝማሪው ቆሜ መረቅኩ፣ በዚህም ፈናን ደስተኛ ሆንኩ።
ሻወል ኢስላም በሚከተለው ሒጅራ ዘመነ ቀመር ረመዳንን ወር ተከትሎ የሚመጣ ወር ስያሜ ሲሆን፣ ይህም ወር የመጀመርያዎቹ ስድስት ቀናት የረመዳን ወር በተለያዩ ምከንያቶች ሁሉንም ቀናት መጾም ላልቻሉ፣ ይበልጡንም እንስቶች በተፈጥሮ ሁኔታ እንደማካካሻ ወይም ማሟያ ተጨማሪ ተደርጎ የሚጾም ነው፡፡

ፎቶ ሚካኤል መታፈሪያ
በሀረሮች ግን በርካታ ማኅበረሰብ እንደመደበኛ ጾም ለሱና ወይም ለበረከት ይጾመዋል። ይህ ሻዋል ወር ጾም መጠናቀቅያ ቀናት ማክተሚያ ወይም ማብቂያ ሲባል ጾሙ እንደተጠናቀቀ ምሽቱን ደማቅ የሆነው የሸዋል ዒድ ሥነ ሥርዓት እስከ እኩለ ሌሊት በተለያዩ ክዋኔዎች ባህላዊና ታሪካዊ መዘከሮች ለየት ባለው ዜማና ከበሮ የታጀበ መንዙማና ባህላዊ ሙዚቃ ከውዝዋዜ ጋር ይታይበታል።
ይህ ሁነት ሁሉም የሚከውነውና የሚሳተፍበት፣ ለዚህም በተለይ ሴቶች ያማሩ ደማቅ የባህል አልባሶቻቸውን ለብሰው ሽቶአቸውን ነስንሰው እጆቻቸውን ሂና ተቀብተው የሚታዩበት፣ ወንዶችም ተሽቀርቅረው ከች የሚሉበት ነው።
የሸዋል ዒድ በዓል ጅማሮ ወደ 16ኛው ክፍለ ዘመን የሚሻገር ሲሆን፣ ይህም ኢብን ኢብራሂም አልጋዚ ‹‹ሐበሻን በማቅናት ዘመቻው›› ድል ተነስቶ በጎንደር ዘንታራ ደጎማ በረመዳን ወር ከተሰዋ በኋላ ባለቤቱ ባቲ ድል ወንብራ ሐዘን ገብቷት ታላቁን ዒድ አልፈጥርን በሐዘን አሳልፋለች፡፡ በሸዋል ወር 6ቱ ቀናት የሱና (በረከት) ጾምን ስታጠናቅቅ ወዳጅ ዘመድ ለየት ያለ ድንገቴ (ሰርፕራይዝ) በማዘጋጀት የሻዋልን ጾም መክተም (መጠናቀቅያ) ላይ ሀሴት እንድታደርግ በደስታ በጭፈራ እንኳን አደረሰሽ ያሉበትን ቀን፣ በየዓመቱ የተለያየ ዝግጅት እየተደረገ ጣፋጭና ለየት ያሉ ምግቦች እየቀረቡ በሐረር ከተማ በውበት ለኢትዮጵያ መኩሪያ ሆኖ ይከበራል።
ዘንድሮ ደግሞ ተለይቷል፣ ዓለምም ዕውቅና ሰጥቷቷል።
የሐረርን ስያሜን በተመለከተ ከተለያየ ጉዳዮች ጋር ይያዛል። እኔ ጸሀፊው በፊት የማውቀው አሁን ላይ በግድግዳዋ ላይ ተጽፎ በፎቶ ላይ ከሥር የሚገኘው፣ ሐረር ማለት በጥንት አብጀድ አረብኛ 405 ማለት ነው። ይህ እንደምንድነው ቢሉ ልክ የግዕዙ ፊደላት አቻ ቁጥር መጠን እንዳላቸው ሀ ቁጥሩ 5፣ ረ ደግሞ 200 ሲሆን፣ በዚህም ሐረር ሲገለጽ 5+200+200 = 405 ይሰጣል። ይህ 405 ደግሞ በሸህ አባድር አማካይነት ከየመን ሂጃዝ ለዳዋ የመጡ ሰዎች ወይም ሰሀቦች ብዛት ቁጥር መሆኑን በከተማዋ የሚገኙ አስረጆች ይገልጻሉ።
ይህንንም ስያሜ ቀድማ በሸህ አብድረህማን እስልምናን ተቀብላ ግን በተግባር ጥሩ ያልነበረችውን በእስልምናው ሥርዓት አጽንታ እንድትዘልቅ በ12ኛው ክፍለ ዘመን እነ ሸህ አባድር ላደረጉት አስተዋጽኦ መሪ አስተዳዳሪ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡
ሐረር በከተማዋና በዙርያዋ በርካታ ታሪካዊ ባህላዊና ተፈጥራዊ መስህቦች ሲኖራት፣ በይበልጥ ግን ቅን የሆነው ማኅበረሰብ የእንግዳ መስተንግዶና ገበያዎቹ መገለጫዎች ሁነዋል። ሐረር ሰው ብቻ አይደለም፣ የዱር የተባሉት ጅቦች ከሰው ልጅ ጋር ተከባብረው በፍቅር ይኖሩባታል፡፡ ለዚህም በሚከበርበት ወቅት በቅቤ የጠገበ ገንፎ ‹‹የጅብ ገንፎ›› ተብሎ ለጅቦቹ ይቀርብላቸዋል።
በእስልምና 4ኛ ቅዱስ ስፍራ እንደሆነች የምትገለጸው ሐረር፣ በአነስተኛ ቦታ ላይ በርካታ መስጅድ፣ ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች፣ ብሎም ዕድሜ ጠገብ ቂራት (መጻሕፍት) የሚገኝባት ታላቅ የኢስላማዊ ቅርስና ባህል ማዕከል ናት።
በርካታ የሚታይ ነገር ስላላት በዓለም አቀፍ ዕውቅና አግኝታ አምራና ተውባ የተሞሸረችውን ሐረርን ጎብኟት፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡