እኔ የምለዉኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

አንባቢ

ቀን: April 21, 2024

በጌታቸው አስፋው

ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው ከሃያ በላይ የሚሆኑ ዋና ዋና የኢኮኖሚ አደጋዎች አሉ፡፡ ለጊዜው የግራ ቀኙን ጥቅምና ጉዳት ተመልክቼና መርምሬ ያወቅኳቸውን አንድ ሦስቱን በዚህ ጽሑፍ አካትቼ እንደሚከተለው እተነትናለሁ፡፡

  1. ኢኮኖሚውን በገንዘብ የማጥለቅለቅ (Financialization of the Economy) አደጋ፣
  2. የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት (Price Determination Mechanism) መዛባት አደጋ፣
  3. ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት (Rural-Urban Migration) አደጋ፡፡
  4. ኢኮኖሚውን በገንዘብ የማጥለቅለቅ (Financialization of the Economy) አደጋ

በተለምዶው የግብይት ሥርዓት ደንብ በገንዘብ የሚገዛውና የሚሸጠው ሸቀጥ ዕቃ ወይም አገልግሎት በጥቅሉ ምርት ነበር፣ ገንዘብ የተፈጠረውም ለዚህ ዓላማ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ገንዘብን በገንዘብ መሸጥና መግዛት ወይም አንድን ዓይነት ሰነዳዊ ገንዘብ ወደ ሌላ ዓይነት ሰነዳዊ ገንዘብ መቀየር፣ ከሁሉም በላይ አትራፊና መክበሪያ ዘዴ የብዙዎችም ዝንባሌ ሆኗል፡፡ ይህ ገንዘብን በገንዘብ በመሸጥና በመግዛት ኢኮኖሚውን በገንዘብ ማጥለቅለቅ (Financialization of the Economy) ይባላል፡፡ በኢትዮጵያ ይህ ሁኔታ ማቆጥቆጡ በአንዳንድ መገለጫዎችና ውጤቶች ይታያል፡፡ በቅድሚያ የገንዘብ አፈጣጠር ሒደትንና በጥሬነት ደረጃ (Liquidity Level)፣ የገንዘብ ዓይነቶችን በቅደም ተከተል ዘርዝሬ ወደ መገለጫዎቹና ውጤቶቹ እረማመዳለሁ፡፡

በቀድሞ ጊዜ የወረቀት ብርና ሳንቲም ወይም ምንዛሪ (Currency) ለማተም በወርቅ ዋጋ ደረጃ (Gold Standard) ተመጥኖ አቻ ወርቅ ማስቀመጥ የግድ ያስፈልግ ስለነበር፣ መንግሥት ከልክ በላይ ማተም አይችልም ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ሁሉም አገሮች ይህን አሠራር ትተው በዘፈቀደ ታትሞ በሚሠራጭበት በአማርኛ ስያሜ ያልተሰጠው በእንግሊዝኛው (Fiat Money) አካሄድ ተተካ፡፡ ይህን የወረቀት ብርና ሳንቲም በንግድ ባንኮች በማስቀመጥ በባንክ ቼኮች አማካይነት መገበያየትም ተጀመረ፡፡ የወረቀት ብርና ሳንቲሞቹ ከባንክ ተቀማጮች ጋር ባንድነት የግብይይት መሣሪያ ጥሬ ገንዘብ (Money) ተብለው ይጠራሉ፡፡ በቅርብ ዓመታትም በዘመናዊው ዲጂታል ግብይት አማካይነት የባንኮች ሚናና የጥሬ ገንዘቡ ዝውውር ፍጥነት ጨምሯል፡፡ በኢትዮጵያ ገና ተግባራዊ ባይሆንም የምናባዊ ጥሬ ገንዘብ (Virtual Money) ጽንሰ ሐሳብ እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ ከዚህም ባሻገር ዓለም አቀፉ የጥሬገንዘብ ጽንሰ ሐሳብ ከመንግሥት ብቸኛ አሠራጭ ባለሥልጣን መሆን ወደ የራሳቸውን የሥርጭት ማዕከል የፈጠሩ የቡድን ምናባዊ ጥሬ ገንዘብ ተገበያዮች ደረጃ ደርሷል፡፡ ክሪፕቶከረንሲ (Cryptocurrency) የተሰኘ ዲጂታል ገንዘብን መግዣና መሸጫ የጥሬ ገንዘብ ግብይይትን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡

የጥሬ ገንዘብ መጠን ኢኮኖሚው ውስጥ መብዛት በአጭር ጊዜ ምርትን ያሳድጋል፣ በረዥም ጊዜ ግን ውጤቱ የዋጋ ንረትን ማባባስ ነው ያሉ የኢኮኖሚ ሊቆች ነበሩ፡፡ የአጭር ጊዜም ሆነ የረጅም ጊዜ ውጤቱ የዋጋ ንረትን ማባባስ ነው ያሉ ሊቆችም ነበሩ፡፡ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በተለይ ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ መንግሥት በበጀት ማነስ ከሚጨነቅ፣ ግብር ከሚጨምር ወይም ብድር ውስጥ ሳይገባ የፈለገውን ያህል ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ (Currency) አትሞ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶቹን ማስፋፋት እንዳለበት የሚመክሩ ሊቆችም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ብቅ ብለዋል፡፡

በቆጣቢዎች ንግድ ባንኮች ውስጥ የተቀመጠ ምንዛሪ ለመዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች በብድር ጥሬ ገንዘብ (Credit Money) አማካይነት ሲሰጥ፣ ፕሮጀክቶችን ማስፈጸሚያ የገንዘብ ካፒታል (Financial Capital) ይሆናል፡፡ አዲስ የሚቋቋሙ ድርጅቶች መነሻ ካፒታል (Venture Capital) ሲፈልጉና የሚስፋፉ ነባር ድርጅቶች የካፒታል ገንዘብ ሲፈልጉ የባለቤትነት ድርሻ (Equity Capital) ወይም አክሲዮን (Share) ሸጠው ያሰባስባሉ፣ ወይም ንብረት (Collateral) በማስያዝ የብድር ካፒታል (Debt Capital) ያሰባስባሉ፡፡ አክሲዮኖችና የዕዳ ሰነዶች ለትርፍ በካፒታል ገበያ የሚሸጡና የሚገዙ ሰነዶች (Securities) ይሆናሉ፡፡ ስለሆነም በካፒታል ገበያ ውስጥ የሚሸጠውና የሚገዛው ገንዘብን በሌላ ገንዘብ ወይም አንድ ዓይነት ገንዘብን ለምሳሌ የባንክ ተቀማጭን በሌላ ዓይነት ገንዘብ ለምሳሌ በአክሲዮን ነው፡፡

በካፒታል ገበያ ውስጥ ስለሚፈጠረው ከፍላጎትና አቅርቦት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መሠረታውያን (Market Fundamentals) መኖር አስተሳሰብ ወጣ ያለ፣ ምርቱ በተፈጠረ ተጨማሪ እሴት መጠን ያልተለካ፣ በሰዎች ስግብግብነት ባህሪ በሚተመን የሰነዳዊ መዋዕለ ንዋይ ዋጋ ማውጣትን ታላቁ ማክሮ ኢኮኖሚስት ጆን ሜናርደ ኬንስ በእንስሳነት መንፈስ (Animal Spirit) ሥነ ልቦና የሚከናወን ንግድ በማለት ገልጾታል፡፡ ከኢኮኖሚስቶች በወረሱት አባባል የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም የካሲኖ ቁማር ጨዋታ ነው ይሉ ነበር፡፡ የኮሙዩኒዝም ጽንሰ ሐሳብን በተነተነው በካርል ማርክስ አስተምህሮ ገንዘብ እንደ የመገበያያ መሣሪያ ሲያገለግል፣ አምራች የራሱን ምርት ሸጦ ከሌላ ሰው የሚፈልገውን ምርት ለመግዛት ሲጠቀም ዑደቱ (ምርት-ገንዘብ-ምርት) ነው፡፡ የካፒታል ገበያ ገንዘብ ግን ገንዘብን አውጥቶ ገንዘብ ለማትረፍ ነው ዑደቱም (ገንዘብ-ምርት-ገንዘብ) ነው በማለት ተጨማሪ እሴት የሌለበት የሰው በሰው ብዝበዛ እንደሆነም አስረድቷል፡፡ 

አሁን ወደ መገለጫዎቹ ዝርዝር እንመለስ፡፡ ምንም እንኳ አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች በኢትዮጵያ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ከጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ጋር ያለው ጥምርታ ከ25 እስከ 28 በመቶ ብቻ በመሆኑ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለ የገንዘብ መጠን ዝቅተኛ ነው ቢሉም ይህ ጥሬ ገንዘብ ብሔራዊ ባንክ አትሞ የሚያሠራጨውን ብርና ሳንቲም፣ ንግድ ባንኮች ብርና ሳንቲሙን አርብተው እንደ የተንቀሳቃሽ፣ የቁጠባና የጊዜ ተቀማጭ የሚይዙትን ለዋጋ ትመናና ለሸመታ ክፍያ የሚያገለግሉትን የገንዘብ ዓይነቶች መገለጫ ብቻ የተመለከተ ነው፡፡ በእነዚህ ላይ ለሀብት ይዞታ ተብሎ የሚያዙት የተቀማጭ ሰርተፊኬት፣ የግምጃ ቤት ሰነድ፣ የመንግሥት ቦንድ፣ የግል ኩባንያዎች ቦንድ፣ የአክሲዮን ድርሻና የማዘጋጃ ቤት ዕዳ ሰነዶች፣ ወዘተ የመሳሰሉ ብዙ ተነጋጅ ሰነዳዊ የገንዘብ ሀብቶች ዓይነትና ቁጥር በበቂ ደረጃ መኖር ወይም መጨመር፣ በገንዘብ (Finance) ኢኮኖሚው መጥለቅለቁን የምናይባቸው አንዱና ሌላው ምልክት ነው፡፡

የግል ባንኮችና የኢንሹራንስ ተቋማት መስፋፋት፣ ሕዝባዊ ኩባንያዎችና አንደኛ ደረጃ አክሲዮን ገበያዎች (Initial Public Offerings)፣ እንዲሁም ከብድር ጥሬ ገንዘብ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያላቸው በማስያዣነት ተመራጭ ሆነው ብር ያለገደብ የሚፈስላቸው እንደ ሪል ስቴት ልማት፣ የሆቴሎችና የዘመናዊ ታክሲ አገልግሎት፣ የቤት መኪናና ብድር መስፋፋትም፣ ከመገለጫዎቹ ሌላው ምልክት ነው፡፡ ሦስተኛው መገለጫ ምልክት የሁለተኛ ደረጃ ሰነዶች ገበያ ወይም የካፒታል ገበያ መፈጠርና መስፋፋት ነው፡፡

መገለጫዎቹን ተከትሎ ብዙ ውጤቶችም እናያለን፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የገንዘብ ኢኮኖሚው ከምርት ኢኮኖሚው ይበልጥ አትራፊ ስለሆነ መዋዕለ ንዋይ ወደ ገንዘብ ኢኮኖሚው መኮብለሉ፣ የገንዘብ ኢኮኖሚው ሠራተኞች ደመወዝ ከምርት ኢኮኖሚው ሠራተኞች ደመወዝ ስለሚበልጥ ከፍተኛ ባለሙያዎች ከምርት ኢኮኖሚው ወደ ገንዘብ ኢኮኖሚው መኮብለላቸው፣ ከጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ድርሻ የቁሳዊ ዕቃዎች ዘርፍ ድርሻ ቀንሶ የአገልግሎት ዘርፍ ድርሻ መጨመሩ፣ በከተማና በገጠር መካከል ያለው የገቢና የሀብት ልዩነትና የመልማት ደረጃ ልዩነት መስፋቱ፣ በባለድርጅቱና በደመወዝተኛው መካከል ያለው የገቢ መጠን ልዩነት መስፋት፣ በገንዘብ ኢኮኖሚው ዘርፍና በምርት ኢኮኖሚው ዘርፍ የተሰማሩት ሠራተኞች የገቢ መጠን ልዩነት መፈጠር ውጤቶች ናቸው፡፡

የእነዚህ ሁሉ ውጤቶች አንድምታ ደግሞ በኢኮኖሚው ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የዋጋ ንረትና የዋጋ መዋዤቅ መፈጠሩ፣ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የብር የሌሎች አገሮችን ምንዛሪ የመግዛት አቅም መዳከሙ፣ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ሥራ አጥነት በተለይም የተማሩ ወጣቶች ሥራ አጥነት መስፋፋቱ፣ የቤትና የመኪና ሀብት ዋጋ ውጣ ውረድ መዋዠቅ ወይም እንደ ፈላ ውኃ መፍለቅለቅ (Asset Price Bubble) የገንዘብ ቀውስና የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋትን መፍጠሩ ነው፡፡

የገንዘብ ግብይይት መሣሪያዎች (Financial Instruments) የገንዘብ ተቋማት ቁጥር፣ የገንዘብ ገበያዎች ዓይነትና ብዛት፣ እንደ ሌሎች አገሮች የሚገባውን ያህል ገና ያልዳበሩባት ኢትዮጵያ የዋጋ ንረት ጣሪያ ከነካ የካፒታል ገበያ ተቋቁሞ የተጠቀሱት ሲዳብሩ የዋጋ ንረቱ ሰማይ ሊነካ ነው፡፡

ገንዘብ በምርት ኢኮኖሚው ደምሥር ውስጥ የሚዘዋወር ደም ስለሆነ፣ ለምርት ኢኮኖሚው ዕድገት በተለይም ለአዲስ ድርጅት ጅማሮ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን በደም ሥር ውስጥ ደም ሲበዛና ሲያንስ የደም ማነስና የደም ግፊት ይፈጥራል፡፡ ምርት የኢኮኖሚው የደም ሥር ሲሆን ገንዘብ ደሙ ነው፡፡ ከአሲዮኖቹ ግብይት ጀርባ ቁሳዊ ዕቃ ምርት ወይም ከዕዳ ሰነዶቹ ጀርባ በመያዣነት የተያዙ ሕንፃዎች ያሉባችው የእጅ አዙር የምርት ግብይይቶች ቢሆኑም፣ የገንዘብ ገበያው ከገበያ መሠረታውያን ወጣ ባለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመክበር በሚደረግ መስገብገብ መልክ መፈጸሙ ተጨማሪ እሴት የማይፈጥር ቁማር ያደርገዋል፡፡

ኢኮኖሚው ውስጥ ተጨማሪ እሴት ሳይፈጥሩ ገንዘብን በገንዘብ መነጋገድ ያተረፈው፣ ከከሰረው ገንዘቡን በውርርድ መሰል ጨዋታ መንጠቅ በሁለቱ መካከል ያለ ቁማር ቢሆንም፣ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ደረጃ ሲታይ ግን የሁለቱ ጨዋታ ሌላ በምርት ኢኮኖሚው ውስጥ ያለ ሦስተኛ ሰው ያመረተው ምርትን የራሱ ውስጣዊ ዋጋ በሌለው በወረቀት ገንዘብ ለመግዛት የሚያስችል አቅም ለማግኘት መወዳደር ነው፡፡ የካፒታሊዝም ዕድገት እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ አስፈላጊ ቢሆንም ሊያልፍባቸው የሚገባቸው ሌሎች ደረጃዎችን አልፎ ነው የመጣው ወይስ ሌሎች አገሮች እንደደረሱበት ደረጃ መድረስ አለብኝ በሚል የእንቁራሪት ዝላይ ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ 

  1. የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት (Price Determination Mechanism) መዛባት አደጋ

ኢሕአዴግ ከመግባቱ ከ1983 ዓ.ም. በፊት በማዕከላዊ ፕላን ብሔራዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የዋጋ ጥናት ኢንስቲተዩት የሚባል ጽሕፈት ቤት ነበር፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች አስተዳደርም የሠራተኛ የሥራ ዝርዝርና የደመወዝ ስኬል እንደ ሥራው ክብደት ያዘጋጅ ነበር፡፡ የዓለም ሥራ ድርጅት (International Labor Organization) እና በንጉሡ ዘመን ሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር፣ በደርግ ዘመን ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ይባሉ የነበሩ መሥሪያ ቤቶች የግል ክፍለ ኢኮኖሚ ሠራተኞች ደመወዝና የኑሮ ሁኔታ ያጠኑ ነበር፡፡ የአሁኑ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እነዚህን ሥራዎች ለመሥራቱ እንደ ማስረጃነት በፖሊሲ ደረጃ የወጣና የተተገበረ ነገር ቢኖር፣ ዘወትር የሚሰማው የሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽነን እሮሮ በቀረ ነበር፡፡ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ተምሳሌት የሆነችው አሜሪካ ዝቅተኛውን የደመወዝ ወለል መጠን በሕግ ስትደነግግ፣ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ጀማሪ የሆነችው ኢትዮጵያ መንግሥት እጁን ጣልቃ አያስገባም አይልም ነበር፡፡

የኢትዮጵያን ዋጋ አወሳሰን ሥርዓት ለመረዳት ጽንሰ ሐሳቦችን መነሻ በማድረግ አካሄዱን አናስስ፡፡ ዴቪድ ሪካርዶና ሌሎች ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ስለዋጋ ትመናና አወሳሰን ሲተነትኑ፣ ምርቱን ለማምረት በፈሰሰ ጉልበት ልክ ወይም በተጨማሪ እሴት (Value Added) ይለኩ ነበር፡፡ ለምሳሌም ሁለት ሸሚዝና አንድ ኮት ለማምረት እኩል ጊዜና የሰው ጉልበት ከፈጀ፣ አንድ ኮት በሁለት ሸሚዝ ዋጋ መሸጥ አለበት ይሉ ነበር፡፡ ይህ ከማምረቻ ወጪና ከአቅርቦት አንፃር የተተመነ የዋጋ ትንታኔ ነው፡፡ ይህ የተጨማሪ እሴት ግንዛቤ ዛሬም ድረስ ከፍተኛ ዋጋ ኖሮት የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት መጠን (Gross Domestic Product-GDP) የሚለካው በተጨማሪ እሴት አለካክ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ጥቅል ምርቱ በተጨማሪ እሴት መልክ ተለክቶ አምራቾቹ ካገኙት ገቢ ጋርና ሸማቾች ለሸመታ ካወጡት ወጪ ጋር እኩል ነው፡፡

ዋናው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግር ተጨማሪ እሴት ያልፈጠረ የገቢ ዓይነትና መጠን መኖሩና ይህ ተጨማሪ እሴት ያልፈጠረ ገቢ ለሸመታ ወጪ ሊውል ሲታሰብ፣ ምርት ባለመኖሩ ገበያ ውስጥ በሚፈጠር ሽሚያ ዋጋ መናሩ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ሕግ አስከባሪ የአገልግሎት ተጨማሪ እሴት ካልፈጠረ፣ በመቀጠሩ ብቻ ገቢ ካገኘ ተጨማሪ እሴት ሳይፈጥር ገበያውን የሚያስወድድበት ገቢ አግኝቷል ሊባል ይቻላል፡፡ አርቲስቱ፣ ባለሀብቱ፣ ትልቅ ሰው ነኝ ባዩ፣ ወዘተ ለግላቸው የሚቀጥሩት ጡንቸኛ ጠባቂ ገቢ ያገኛል፡፡ ለሰውየው እንጂ ለማኅበረሰቡና ለአገር  የሚፈጥሩት ጠቃሚ ተጨማሪ እሴት የለም፡፡ በገቢያቸው ለመሸመት ገበያ ሲወጡም በእነሱ የተፈጠረ ተጨማሪ እሴትና ምርት ስለሌለ ዋጋ ይወደዳል፡፡

ስለዚህ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ችግር ለማወቅ የመጀመሪያው ዕርምጃ የተጨማሪ እሴት ትርጉምን ማወቅ ነው፡፡ አገልግሎታቸው ገቢ ማስገኘት የሚገባቸው ተጨማረ እሴት የሚፈጥሩ ሥራዎችና ምርቶችንና እሴት የማይፈጥሩ ሥራዎችና ምርቶችን መለየትና ተጨማሪ እሴት ለፈጠሩት ዋጋ መተመን ነው፡፡ ተጨማሪ እሴት እንዴት ይለካል? አንዲት እናት እንጀራ ጋግረው በሃያ ብር ቢሸጡ የእሳቸው ተጨማሪ እሴት ሃያ ብር አይደለም፡፡ ከሃያ ብር ውስጥ ጤፉን ያመረተው የገበሬው ተጨማሪ እሴትና ጤፉን የፈጨው ወፍጮ ቤት ተጨማሪ እሴት ተቀንሶ የውኃው፣ የምጣድና የእሳቱ፣ ወዘተ ወጪዎችም ተቀንሰው ምናልባት የእሳቸው ተጨማሪ እሴት አንድ ብር ቢሆን ነው፡፡ ከመርካቶ ወደ ፒያሳ ዘይት ወስዶ የሸጠ ነጋዴ ተጨማሪ እሴት ከዘይቱ ሽያጭ ዋጋ ላይ ዘይቱን የገዛበትና ለመጓጓዣ ያወጣው ወጪ፣ እንዲሁም ከፒያሳው የሱቁ ኪራይ የዘይቱን ድርሻ ወጪ አስልቶ በመቀነስ ነው፡፡

ከክላሲካል ኢኮኖሚስቶች በኋላ ከመጡት ታዋቂ የኒኦ ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች አንዱ የሆነው አልፍሬድ ማርሻል ዋጋ የሚወሰነው ከማምረቻ ወጪና እሴት ከመፍጠር አንፃር ብቻ ሳይሆን፣ ዕቃው ለሸማቹ ከሚሰጠው ጠቀሜታ (Utility) አንፃርም እንደሆነ ለማመልከት፣ ከአንድ መቀስ ሁለት ምላጮች ውስጥ ቆራጩ ይህ ነው ብለን መለየት አንችልም በሚል ምሳሌ የአቅርቦትና የፍላጎት በጋራ ዋጋ ወሳኝነትን አስረድቷል፡፡ አዳም ስሚዝና ሌሎች ኒኦ ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ቀጣይ ጠቀሜታ (Marginal Utility) እና ቀጣይ ምርታማነት (Marginal Productivity) የተሰኙ ለዋጋ ትመናና ለግብይይት እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ጽንሰ ሐሳቦችንም ነድፈዋል፡፡ 

ይህም የዕቃ ዋጋ የሚወሰነው በማምረቻ ወጪና በአቅርቦት ብቻ ሳይሆን፣ ለሸማቹ በሚሰጠው ጠቀሜታና ፍላጎትም እንደሆነ ያረጋግጥልናል፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጥ ጠቀሜታ እንኳ ገና ያልተሟላ ስለሆነ፣ ገበያ ውስጥ ገንዘብ በጨመረ ቁጥር የማምረት አቅም ሳይፈጠር ወይም ምርታማነትና አቅርቦት ሳያድግ ገቢ ሲያድግ ጠቀሜታው ወደ የመግዛት አቅምና ለመግዛት መፍቀድ ፍላጎት እየተቀየረ የዋጋ ንረት ወደ ሰማይ ተተኩሷል፡፡ ብዙ ሰዎች አንዳንድ ኢኮኖሚስቶችም ጭምር የመግዛት አቅምን ያገናዘበ ፍላጎት የመግዛት አቅምን ካላገናዘበ መሻት ጋር አምታተው በኢትዮጵያ ፍላጎት በዛ አቅርቦት አነሰ ይላሉ፡፡

ነገር ግን ፍላጎት ማለት በገበያ በተተመነ የምርት ዋጋ ለመግዛት አቅም መኖርና ፈቃደኛ ሆኖ ለመክፈል ዝግጁነትን የሚያመለክት ከሆነ፣ የራሱን ምርት አምርቶ ለሌላ ሸማች ተጨማሪ እሴት ያልፈጠረ ሰው ገቢ ከየት አግኝቶ ነው በተጠየቀው ዋጋ የመግዛት አቅም የኖረው ብለው አዋቂ ኢኮኖሚስቶች ይጠይቃሉ፡፡ መልሱንም ያውቃሉ፡፡ ምርት ሳያመርቱ ወይም ካመረቱትና ከፈጠሩት ተጨማሪ እሴት በላይ በሌላ አነጋገር ከምርታማነታቸው በላይ ገቢ ያገኙ ሰዎች አሉ ማለት ነው፡፡ ሥራ የማይሠሩ ልጆችና ተረጂ ሰዎች ሸቀጥ መሸመቻ የገንዘብ አቅም የሚያገኙት፣ ተጨማሪ እሴት ፈጥሮ ገቢ ካገኘ ዘመድ የተላለፈላቸውን ገቢ (Transfer Income) ተጠቅመው ስለሆነ ተጨማሪ እሴትና ገቢ፣ እንዲሁም ወጪ እኩል መሆን አለባቸው የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ አያፋልስም፡፡ በብሔራዊ ኢኮኖሚ ደረጃም በተጨማሪ እሴት የተለካ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ከብሔራዊ ገቢና ከብሔራዊ ወጪ ጋር እኩል ነው ያልነውን ከላይ የቀረበ የኢኮኖሚ ልኬትም አይቃረንም፡፡

ነጋዴው ዋጋ አስወደደብኝ ብሎ የሚጠይቀውን ሸማች አንተስ ፍላጎትህንና የመግዛት አቅምህን ወይም ነጋዴው በጠየቀው ዋጋ ለመግዛት ያስቻለ ፈቃደኝነትህን፣ ወይም ገቢ ገንዘብ ከየት አገኘህ ብሎ መጠየቅ ይቻላል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሚሊዮኖች ከእንጀራና ወጥ ምሳና እራት ወደ ሽንብራና ባቄላ ቆሎ ምሳና እራት ቁልቁል ሲወርዱ፣ ሺዎች ለአንድ ምሳ ወይም እራት ሺዎችን ከፍለው ወደ መመገብ ከፍ ብለዋል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የግል አውቶሞቢሎች ዋጋ ከመቶ ሺዎች ወደ ሦስትና አራት ሚሊዮን ብር ቢገቡም፣ በአዲስ አበባ የባለመኪኖች ቁጥር እጥፍ ድርብ ሆኗል፡፡ ለሚሊዮኖች የቆሎ ምሳና እራት መግዣ ገንዘብ ማግኘት ሲያቅትና ወደ ልመናም ሲዳረጉ ለሺዎች ለመኪና ሚሊዮኖችን መክፈል የሚያስችል የመግዛት አቅምና ፍላጎት ተፈጥሯል፡፡

በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ሦስት አካላት አሉ፡፡ ፈላጊና ሸማቹ ምን እንዲመረትላቸው ለይተውና ወስነው አቅራቢና አምራቾቹን አዛዥ ሲሆኑ፣ አምራቾቹ የሸማቾቹን ገንዘብ በፈቃደኝነት ከኪሳቸው ለማውጣት ሲሉ የሸማቾቹን ፈቃድ ፈጻሚ ታዛዥ ናቸው፡፡ መንግሥት በሚሰበስበው ግብር ልክ ባለሙያዎችን ቀጥሮ ሸማቾቹና አምራቾቹ የነፃ ገበያ ሕግና ደንብ አክብረው እንዲገበያዩ ፖሊሲዎችን ከመንደፍ አንስቶ፣ ለሸማቾቹም ለአምራቾቹም የመሠረተ ልማት ዝርጋታና ማኅበራዊ አገልግሎትን የመስጠት ኃላፊነትን የሚሸከም አጋዥ ነው፡፡

ይህ የአዛዥ ሸማች የታዛዥ አምራች የአጋዥ መንግሥት የሥራና ኃላፊነት ግንኙነት ተፋልሶ ነው፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ይህን ያህል የተወላገደው፡፡ አንድ ሰው አዛዥ ሸማች ብቻ ሳይሆን ታዛዥ አምራችም፣ ታዛዥ አምራች ብቻ ሳይሆን አዛዥ ሸማችም ስለሆነ በገበያ ውስጥ እንደ ሸማችም እንደ አምራችም ከሌሎች ሰዎች ጋር ውድድር ይጠብቀዋል፡፡ አጋዡ መንግሥትም በሚሰበስበው የግብር ገቢ ለሠራተኛ ቅጥርና ለዕቃዎች ግዥ ወጪ ስለሚፈጽም የአገልግሎት ገዥም ሻጭም ነው፡፡ ኢኮኖሚያችን የተመሰቃቀለው ይህ የአዛዥ ሸማችነት፣ የታዛዥ አምራችነትና የአጋዥ መንግሥት ግንኙነት ተስተጓጉሎ ነው፡፡ የሸማችነትና የአምራችነት ውድድሩ ሕግና ደንብን የተከተለ እንዲሆን በአጋዥነት መሳተፍ ያለበት መንግሥት ኃላፊነቱን ካለመወጣቱም ባሻገር፣ የነፃ ገበያ ሸቀጥ መሆን የሚገባውን የመሬት አገልግሎት አንቆ ይዞ ውድድሩ ፈሩን እንዲስት አድርጓል፡፡ የከተማም ሆነ የገጠሩ ሕዝብ በጨመረ ቁጥር ውድድሩ ከሐዲዱ የባሰ እየራቀ ሽሚያና ማኅበራዊ ቀውስ እስከማስከተል ደርሷል፡፡ ኢትዮጵያ ልትወጣበት ያልቻለችው ዓይነት ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡

  1. ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት (Rural-Urban Migration) አደጋ

ብልፅግና የኢሕአዴግ መንግሥት ከሚከተለው ደሃ ተኮር ልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ ፍልስፍና ገሸሽ ብሎ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ገበያው ያዘዘውን እንዲያመርት የፕራግማቲክ ሊበራል ኢኮኖሚ እንዲፈጠር አግዛለሁ ቢልም፣ ያገዘው ነገር ባለመኖሩ ነፃ ገበያው ሕግና ደንብ የሌለው ልቅ ሆኗል፡፡ ልማቱ በገጠር መቋረጡ በራሱ የገጠር ሰዎች የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ከተማ እንዲፈልሱ የሚያደርግ ሲሆን፣ የተፈጠረው የሰላም መታጣትም ሰዎች ወደ ከተማ እንዲሸሹ አድርጓል፡፡ ወደ ከተማ የሚፈልሱትም በገጠር ለዓይናቸው እንኳ ዓይተው የማያውቋቸውን ሸቀጦች ለማግኘት በኢመደበኛና አንዳንዴም በሕገወጥ ድርጊቶች ስለሚሰማሩ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች ኑሮ ተመሰቃቅሏል፡፡ የደሃ ምግብ ይሰኙ የነበሩት ሽሮና ጎመን፣ ሻይና ቡና፣ ለኑሮ የማትመች አንድ ክፍል ቤት ኪራይና የተለበሰ ጨርቅ ሳይቀሩ ዋጋቸው ባለፉት አምስት ዓመታት እስከ አሥር እጥፍ ጨምሯል፡፡ ከዚህም አልፎ በየከተሞቹ ልመናና የወጣት ምሁራን ግልጽና ሥውር ሥራ አጥነት ተንሰራፍቷል፡፡

በከተሞች የሠራተኛው ደመወዝና የግል ሥራ ገቢ ምርትን የመሸመት አቅም ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ ዝቅ ብሏል፡፡ በአዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በወር በስምንት መቶ ብር የተቀጠሩ የአካባቢው ገጠር ሠራተኞች ገቢ በትይዩ ገበያ የዶላር ምንዛሪ ሒሳብ ሲተመን ሰባት ዶላር ብቻ ነው፡፡ ወደፊት በምንዛሪ ምጣኔ መስተካከል ሳቢያ የብር ዋጋ የባሰ ሲቀንስ የሠራተኞቹ ወርኃዊ ደመወዝ ወደ ሦስትና አራት ብር ዝቅ ይላል፡፡ ሀብታሞች በሚናጥጡት ልክ የከተማ ደሃዎች ይቆረቁዛሉ፡፡

በገጠር የሕዝብ ቁጥር ከመጨመር ጋር ተያዞ የሚታረሰው መሬት መጥበብ ተፈጥሯል፡፡ የገጠር ሥውርና ግልጽ ሥራ አጥነትም እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ መሠረተ ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ማዳረስ አልተቻለም፡፡ ለከተሞች የዋለ ገንዘብ ለገጠሩ የቀረ የዕጦት ዋጋ (Opportunity Cost) በመሆኑ፣ በምናያቸው የከተሞች ሕንፃዎች ልክ፣ በምናያቸው የከተሞች መብለጭለጭ ልክ ገጠሮች የኑሮ መሠረታዊ አስፈላጊ ነገሮችን እያጡ ነው፡፡ ወደ ከተሞችና ወደ ውጭ አገሮች ኩብለላውና ፍልሰቱ ከእነዚህ ጋር የተገናኘ ነው፡፡

የከተማና የገጠሩን ደምረን ስናይ ከ60 ዓመታት በፊት የደቡብ ኮሪያና የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፍስ ወከፍ ገቢ እኩል ነበር፡፡ ዛሬ የደቡብ ኮሪያ ሕዝብ ነፍስ ወከፍ ገቢ ከ30 ሺሕ ዶላር በላይ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ከአንድ ሺሕ ዶላር በታች ነው፡፡ ባለሥልጣናትና ዓለም አቀፍ ተቋማት በቧለማሎች አስለክተናል በሚሉት የቁጥር ማስረጃ አረጋግጠናል ቢሉም፣ ጥቅል የምርት መጠንና ነፍስ ወከፍ ገቢያችን በትክክል ቢለካ የዚህን ግማሽም እንደማይሆን በመግለጫዎችና በምልክቶች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር  ባቀረብኩት ጽሑፍ አረጋግጫለሁ፡፡ ዛሬ አንድ ሺሕ ሁለት መቶ ዶላር ነው ተብሎ የሚነገረን ነፍስ ወከፍ ገበያችን በ56 ብር ምንዛሪ ምጣኔ ወደ የእኛው ብር ሲቀየር 67 ሺሕ ብር ነው፡፡ ነገ የብር ምንዛሪ ምጣኔው 120 ብር ሲሆን ምንም ዓይነት ተጨማሪ እሴት ሳይፈጠር በገንዘብ ተመን ለውጥ ብቻ ነፍስ ወከፍ ገቢያችን ወደ 144 ሺሕ ብር ያድጋል፡፡ ይህ ነው በባለሥልጣኖቻችን የሚነገረን የኢኮኖሚ ዕድገት መለኪያ 

ኢኮኖሚስቶች በተመጣጠነና ባልተመጣጠነ የዕድገትና ልማት ዘዴ፣ በገጠር ልማትና በከተማ ልማት የዕድገትና ልማት ዘዴ ስለዕድገትና ልማት፣ ስለሥልጣኔና ስለጥገኝነት የዕድገት ዓይነቶች የተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦች ነድፈዋል፡፡ አገሮችም በባለሙያዎቻቸው ጥናትና ትንታኔ አማካይነት የሚስማማቸውን መርጠው ይተገብራሉ፡፡ የኢትዮጵያውያን ስደትና ወደ ከተሞች ፍልሰት ምክንያትም የዕድገት ዘዴዎቹ በባለሙያዎች ባለመተንተናቸውና ፖለቲከኞች በዘፈቀደ ስለሚፈጽሙት ነው፡፡ የጋራ አገር ለመገንባት መታሰቡ ቀርቶ በግል ለመበልፀግ መሻማቱ ነግሷል፡፡ አንዳንድ ኢኮኖሚስቶችም በልማታዊ መንግሥት የኢሕአዴግ መንግሥት ዘመን ኢሕአዴግን መስለው፣ በሊበራል መንግሥት የብልፅግና ዘመን ብልፅግናን መስለው በሞቀበት ጣዱኝ ሆነው ለአገር የሚያስቡ እየመሰሉ በግል ለመክበር ኢኮኖሚው በገንዘብ የሚጥለቀለቅበትን፣ የዋጋ ንረት የሚጨምርበትን፣ ገጠሩ ሳይለማ ከተሞች ብቻ የሚበለፅጉበትን፣ ይልቁንም ነፃ ገበያ መርህ የተከተለ ምክር እየለገሱ ነው፡፡ ለዚህ ነው በእነዚህ ሦስት አደጋዎች ምክንያት ብቻ ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት የሚያሠጋው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየለጽን፣ በአሜሪካ አድራሻቸው getachewastaw240 @ gmail. com ማግኘት ይቻላል፡፡