
By አንባቢ
April 21, 2024

በፋና ገብረሰንበትና ዮናስ ታሪኩ
ቅዳሜ ሚያዝያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ሌሊት ኢትዮጵያ ከታላላቅ ጀግናዎቿ መካከል አንዱ የነበሩትን አስማማው ቀለሙን (ዶ/ር) አጥታለች፡፡ አስማማው የአገርን ቋሚ ጥቅምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የግል ፍላጐታቸውን ወደ ጐን በማድረግ ለረጅም ዓመታት መስዋዕትነት ከከፈሉ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ውስጥ አንዱ ነበሩ፡፡ አገራቸው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ፣ ቀጣናዊና ውስጣዊ ችግሮች በተፈተነችበትና ሰው በሚያስፈልጋት ዘመን ግንባር ቀደም በመሆን በታላቅ ሙያዊ አርበኝነት አገልግለዋል፡፡
ምናልባትም ወደር የማይገኝለት፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የአገር ደኅንነት ስትራቴጂና ፖሊሲ ቀረፃ፣ አተገባበርና ተቋም ግንባታ ላይ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በ1970ዎቹ የነበረውን ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የጂኦ-ፖለቲካ ምስቅልቅል በመተንተንና በመረዳት ተግተውም በመሥራት ኢትዮጵያም በቀጣናው የአቅሟን ያክል ሚናዋን እንድትወጣ ያስቻሉ ታላቅ ባለሙያ ነበሩ፡፡ በዚህም ሥራ አሁን የምናየውን በተለይም ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በኋላ የመጣውን የቀጣናውን አገሮች መዋቅራዊ ሁኔታ ካዋለዱ ጥቂት ግን ብዙም ያልተነገረላቸው ኢትዮጵያውያን ጀግኖች መካከል አንዱ ነበሩ።
ከሥራው ፀባይና ሁኔታ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ያለው የደኅንነት ሥራ ከ”ጆሮ ጠቢነት” እና “አሳባቂነት” አሳልፎ አለማየት፣ ለዘርፉ ሚና ማደግና ለአገር መታደግ ታላቅ ሚና የተጫወቱ እንደ አስማማው ዓይነት አርበኞችን እንዳናደንቅና እንዳናመሰግን አድርጎናል፡፡ በተጨማሪም በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ጊዜ የነበረው ፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ዕይታም ታክሎበት እሳቸውም ሆኑ ባልደረቦቻቸው እንደ ወንጀለኛ ታይተው ታስረዋል፣ ተንገላተዋል፣ ብሎም የሚገባቸውን ክብርና ዕውቅናም አለማግኘታቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ቢረፍድም የተወሰነ ደቂቃ ወስዶ አገራዊ አስተዋጽኦዋቸውንና ስኬታቸውን መዘከር ያስፈልጋል፡፡
በፍኖተ ሰላም አውራጃ፣ ምሥራቅ ጐጃም ነበር አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር) በ1932 ዓ.ም. የተወለዱት፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ ፈጠራና ራስን የመቻል ዝንባሌ ይታይባቸው ነበር፡፡ እንደ መታደልም ሆኖ በጊዜው የነበሩ ጐበዝ ተማሪዎች ተመርጠው በሚማሩበትና በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይገኝ በነበረው በዕደ ማርያም ትምህርት ቤት ለመማር ዕድሉን አግኝተው ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡ በመቀጠልም ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ገብተው በኢኮኖሚክስ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡
በተማሪዎች ንቅናቄ ጅማሬ ወቅትም በንቅናቄው ውስጥ የነበረውን ክፍተት ለመሙላት በተደረገ መመዳደብ ሁለት ሁለት ተማሪዎች የታጠቀውን ክፍል ተቀላቅለው ‘ከውስጥ መሥራት’ የሚል ስትራቴጂ ሲያዝም፤ እርሳቸው ወደ ፖሊስ/አባዲና ገብተው ረዥሙን የሥራ ሕይወታቸውን ካሳለፉበት የደኅንነት ሙያ ጋር በሒደት ተዋወቁ፡፡
በትጋታቸውና በብቃታቸው በንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ የነበሩት የፖሊስ አመራሮች ትኩረት የሳቡት አስማማው በድኅረ ምረቃ (በMSc in Resource Allocation) ከእስራኤል አገር ለተገኘው የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ዕድል ተመራጭ ሆነዋል፡፡ በትምህርት ቆይታቸውም የተሻለ አፈጻጸም በማሳየታቸው የእስራኤሉ ሞሳድ ከኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ተጨምሮበት ለልዩ ሥልጠና ተመረጡ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዋናው የደኅንነት ሙያቸውንም ጀመሩ፡፡
ወደ አገር ቤት ሲመለሱ ግን የአብዮቱ መፈንዳትና ከእርሳቸው ጋር ወደ ተለያዩ ወታደራዊ/ፖሊሳዊ ክፍሎች የተመደቡ የተማሪዎች ንቅናቄ (አየር ኃይል፣ ባህር ኃይል፣ የክብር ዘበኛ፣ ፖሊስ ወዘተ) እየተለቀሙ መያዝ ብሎም መገደል እና የቀይ/ነጭ ሽብር ደም መፋሰስ ምክንያት ቀጣዩ ትምህርታቸውን እንደመሸሻ እንዲጠቀሙ አስገደዳቸው፡፡ በቡልጋሪያም የዶክትሬት ትምህርታቸውን አጠናቀው፣ በሎንዶን በሚገኘው London School of Economics የድኅረ ዶክትሬት መርሐ ግብር ጨርሰው በ1970ዎቹ መጀመሪያ በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት ወደ አገር ቤት ተመለሱ፡፡
ለተወሰነ ጊዜ በኘላኒንግ መሥሪያ ቤት ከሠሩ በኋላም በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመድበው ሥራ ጀመሩ፡፡ በዚያው መሥሪያ ቤትም በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር እስከሆኑበት ጊዜ ድረስ አገልግለው፣ እስከ ምክትል ሚኒስትርነት ማዕረግ ደርሰዋል። በዚህም ጊዜ ጉልህ አስተዋጽኦ ካሳረፉባቸው ሥራዎች ውስጥ የስትራቴጂክ ጥናት ማዕከልን ማቋቋማቸውና የማስተማሪያ መንገዶችንና መጻሕፍትን የማደራጀት ልዩ መንገድ በመፍጠር ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህም ተቋም በአሁኑ ወቅት አድጐና ተስፋፍቶ የደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በቅቷል፡፡
አስማማው ሥራቸው በዋነኝነት የቀጣናው በተለይም የጎረቤት አገሮችን ይሸፍን ስለነበረ በጊዜው የነበሩት ዋና ዋና የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ በነበሩት ሱዳንና ሶማሊያ ላይ በማተኮር ዘመኑ የሚጠይቀውን ሙያዊ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ዘግይታ በገባችበት የቀጣናው እርስ በርስ መጠላለፍ ዓውድ ወስጥ ለአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነትና ብሔራዊ ጥቅም መጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ አገር ከመከላከል አልፈው ወዳጆችን በማብዛት ጠላቶችን በመቀነስ በተለይም አገሪቱን ለመጉዳት ስትራቴጂ ነድፈው ታክቲክ ቀርፀው ጉዳት ለማድረስ ለተንቀሳቀሱ የቀጣናው ተዋንያን የሚገባውን አፀፋ ለመስጠት የሚያስችል መፍትሔ በማመንጨትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በደኅንነትና በዲፕሎማሲው ዘርፍ ወቅቱን የዋጀ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ለምሳሌ የ1969ኙን የሶማሊያ ወረራ ተከትሎ ወደ ሶማሊያ ተወስደው የነበሩ በሺ የሚቆጠሩ ሲቪልና የጦር እስረኞች ነፃ ለማውጣት ከተለያዩ የሶማሊያ እስር ቤቶች ስድስት ወር የፈጀ የመረጃ ማሰባሰብ (ስውር ስለላ) ሥራ ሠርተዋል።
አብዛኛው የደኅንነት ባለሙያ ሥራ በዝርዝር የማይነገር ቢሆንም ጥቂት ስለ ሶማሊያ ሥራቸው እንጨምር፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሲቪልና የጦር እስረኞች በመጥፎ ሁኔታ መያዝ አሸንፌያለሁ ላለው የኢትዮጵያ መንግሥት ከቤተሰቦች የማያቋርጥ ጫና አስከትሎ ነበር፡፡ ያለ ጥናት ዘው ብሎ ለማስለቀቅ የሚደረግ ጀብደኛ ሙከራ የሚኖረውን ኪሳራ የተረዱት አስማማው፣ የጥናትና ዝግጅት አስፈላጊነትን ለመንግሥት አሳምነው ኃላፊነቱን ተረከቡ፡፡ ወራት በፈጀ ጥናታቸው ወደ 120 ገጽ የሚሆን ዝርዝር የሆነ ዕቅድ አዘጋጅ1ተው ከጨረሱ በኋላ ሄዶ የሚተገብረው ሰው ሲጠፋ በወቅቱ የነበሩት የአገሪቱ መሪ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ‘ለምን አንተው አትተገብረውም’ ባሏቸው መሠረት ጥያቄውን ተቀብለው ገቡበት፡፡
በአንድ ወዳጅ አፍሪካዊ አገር ፓስፖርትና የጋዜጠኝነት ፈቃድ ወስደው “ፔድሮ” በሚል ስም ወደ ሞቃዲሾ አቀኑ፡፡ የተለያዩ ሲያድ ባሬን የሚያሞጋግሱ ጽሑፎች በሶማሊያ ጋዜጦች ካሳተሙ በኋላ በሶማሊያ ጦርና መንግሥት ውስጥ መረጃ የሚያቀብሏቸው ሰዎች መልምለው ወደ ተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎችም በመጓጓዝ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ሙሉ መረጃ አጠናቀሩ፡፡ በተለያዩ ማጐሪያ ካምፖች ውስጥ ስንት ኢትዮጵያውያን (በፆታ፣ የዕድሜና የጤና ሁኔታ… ወዘተ) እንደታሰሩና በምን ሁኔታ እንደሚጠበቁ (የወታደር ብዛት፣ መሣሪያ ያለበትን ሁኔታ) ሙሉ መረጃ በዋነኝነት አጠናቀሩ፡፡ ይህ መረጃ ወታደራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ ጠቃሚ ነበር፡፡ በ1981 ከሶማሊያ ጋር ያለን ግንኙነት መልሶ መጀመር የወታደራዊ ዕርምጃን አስፈላጊነት አስቀርተዋል:: ነገር ግን መረጃው በኋላ የእስረኞቹን መለቀቅ ሒደት አቅልሏል፡፡ በደኅንነት ሥራ ዘርፍ የት እንደሚገኙና ስንት እንደነበሩ ያጠኑት የደኅንነት ባለሙያ የዲፕሎማሲ ካባ ደርበው አምባሳደር ሲሆኑ፤ የእነዚህን ኢትዮጵያውያን መለቀቅ በዲኘሎማሲ ሥራ ለማሳካት ችለዋል፡፡
በጊዜው የነበሩ ሌሎች የአገር ውስጥ ደኅንነት ሥራዎች በተለይም በቴክኖሎጂ ማዘመንና በኢኮኖሚያዊ አሻጥር መከላከል ላይ የተለያዩ ሚናዎችን ተወጥተዋል፡፡ የ1981 ዓ.ም. የኢትዮጵያና ሶማሊያ የዲኘሎማሲ ግንኙነት መልሶ ከተጀመረ በኋላም አምባሳደር ሆነው በሶማሊያ የተለያዩ ውጤታማ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ በጥቅሉ በጊዜው የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ከሱዳንና ሶማሊያ የተቃጣበትን የማዳከም ፖሊስ በመመከት ከፊት ሆነው መርተዋል፡፡
የአስማማው (ዶ/ር) ታላቅ ሙያዊ አስተዋጽኦ አሻራ አሁን በምናየው ቀጣናዊ የጂኦ-ፖለቲካ አሠላለፍ በጉልህ ይታያል፡፡ በሙያ ዘመናቸው በቀጣናው ላይ ያለውን የኃይል ፉክክር የመኖርና ያለመኖር ተጋድሎ አገሪቱ በውስጣዊ ፈተና ውስጥ እንኳን ሆና በአሸናፊነት እንድትወጣ በንፅፅር ከተቀናቃኝ ጎረቤቶቿ ጎልታ እንድትወጣ ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ የደኅንነትና የውጭ ግንኙነት የታሪክ ፍሰት ውስጥ የጉልህ ግለሰቦች ሚናና አሻራ በግልጽ የሚታይበት ገጽ ለመጥቀስ ከተፈለገ የአስማማው አሻራ በአፍሪካ ቀንድና በኢትዮጵያ ቁመና ላይ ጎልቶ ይታያል፡፡
በ1983 ዓ.ም. የቀድሞው (የደርግ) ባለሥልጣናት ሲታሰሩም ለእስር ተዳርገው ከ12 ዓመታት በላይ ያለፍርድ ቢቆዩም የራሳቸውን ሞራል ጠብቀው ሌሎችንም አግዘዋል፡፡ በእስር ቆይታ ጊዜያቸውም በካይረፕራክቲክ (Chiropractic) የጤና እንክብካቤ ሙያ ራሳቸውን አስተምረው ብዙዎችን አግዘዋል፡፡ ከእስር በነፃ ከተሰናበቱም በኋላ በጤናና በባንኪንግ ዘርፍ ላይ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ከ2010 ዓ.ም. በኋላም ወደሚወዱት የሙያ ዘርፍ ተመልሰው በደኅንነት ጉዳዮች ላይ የማማከርና የማስተማር አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
በአጭሩ አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር) ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ አገራቸውንና ሕዝባቸውን በቋሚነት በመማር፣ አዲስ ዕውቀትና ክህሎት በማዳበር አገልግለዋል፡፡ በዚህም ረጅምና ፈታኝ ሕይወት ባለቤታቸው ወ/ሮ ሰብለ ሰኢድ ጠንካራ አጋር ሆነው አብረዋቸው ተጉዘዋል፡፡ በትዳር ዘመናቸውም ሦስት ወንድ ልጆችን አፍርተው ለወግ ማዕረግ አብቅተዋል፡፡
የዚህ አጭር ጽሑፍ አዘጋጆች የአስማማው ቀለሙ (ዶ/ር) የሕይወትና የሙያ ተሞክሮ የሚገባውን ትኩረት ቢያገኝና ተሰንዶ ቢቀመጥ ለተተኪ አገር ወዳድ ዜጎች ብዙ ቁም ነገር የሚያስጨብጥና አርዓያ የሚሆን ነው ብለው ያምናሉ። በመስኩ ያሉ ባለድርሻ አካላትና ተመራማሪዎች ከአስማማው ቀለሙም ሆነ ከሌሎች የአገር አገልጋይ ባለሙያዎች ተሞክሮ ዜጎች ትምህርት ይቀስሙ ዘንድ፣ ትኩረት ሰጥተው በመሰነድና በማሳተም የበኩላቸውን እንዲወጡም በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ያቀርባሉ።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊዎቹ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም ፕሮፌሰሮች መሆናቸውን እየገለጽን፣ ጽሑፉ የጸሐፊዎችን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡